የጊምቢ ወረዳ ተፈናቃዮች ባለፉት ሁለት ወራት ድጋፍ እንዳላገኙ ገለፁ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 23 2017በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች ባለፉት ሁለት ወራት ሰብአዊ ድጋፍ እንዳላገኙ አስታውቋል፡፡ በየወሩ የ15 ኪ.ሎ ድጋፍ ለተፈናቀሉ ዜጎች በነፍሰ ወከፍ ይቅርብ እንደነበር የገለጹት አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡት ነዋሪዎች ከመጋቢት ወር ወዲህ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳልመጣላቸው ተናግረዋል፡፡ የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ወይም የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት በበኩሉ ለተፈናቀሉ ዜጎች በዚህ ሳምንት እርዳታ መላኩን ገልጸው እርዳታ በወረዳዎች በኩል እንደሚከፋፈል አመልክተዋል፡፡
የጊምቢ ወረዳ ተፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ ጥያቄ
ከጊምቢ ከተማ 40 ኪ.ሜ ገደማ ርቀት ላይ በሚትገኘው ቶሌ በተባለች ቀበሌ በሁለት ቦታዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ በየወሩ ይሰጣቸው የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ ከመጋቢት ወር ወዲህ በመቋረጡ ለችግር መጋለጣቸውን ነው በቶሌ የሚገኙ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ የተናገሩት፡፡ ከዚህ ቀደም በአካባቢአቸው ይስተዋል የነበረው የጸጥታ ችግር መሻሻሉን የገለጹት ነዋሪው በአሁኑ ወቅት ሰብአዊ ድጋፍ እሳቸውን የሚገኙበትን ጣቢያ ጨምሮ ጮቆርሳ የሚባል ቦታ የሚገኙ በርካቶች ለሁለት ወራት ድጋፍ እንዳላገኙ አመልክተዋል፡፡
ከጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በሰላም ችግር ወደ ደብረ ብርሀን ሸሽተው ከነበሩበት ሰዎች መካከል በ2 ዙር በመጋቢት 2015 ዓ.ም ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ወደ አካባቢው የተመለሱ ሲሆን በተከሰተው ጸጥታ ችግር መኖርያ ቤታቸው የወደመባቸው 90 አባወራዎች ቤት የተሰራላቸው ሲሆን ሌሎች መጠነኛ ጥገና የተደረገላቸው ሰዎችም ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተነግረዋል፡፡ ሌሎች ንብረታቸው ሙሉ በመሉ የወደመባቸው ሰዎች ደግሞ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
እርዳታ ሳያገኙ ሁለት ወር እንዳለፋቸው የተናገሩት ሌላው ነዋሪም በተመሳሳይ የክረምት ወር መግባትን ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭትም እየጨመረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃ 15 ኪ.ግ ድጋፍ በየወሩ ይሰጥ እንደነበር የተናገሩት ነዋሪው ለሁለት ወራት ያህል ሰብአዊ ድጋፍ እንዳላገኙ አብራርተዋል፡፡
‹‹ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ልክናል›› የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ
የምዕራብ ወለጋ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ወይም ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ ሰብአዊ ድጋፍ የሚከፋፈለው በወረዳዎች በኩል መሆኑን ገልጸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ መላኩን አስታውቋል፡፡ የምዕራብ ወለጋ ዞን ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘርይሁን ተክሌ በዚህ ሳምንት ሰብአዊ ድጋፍ መላካቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ በቅርቡ ዱቄት ተጭነዋል፡፡ ባጠቃላይ 2 መቶ ኩንታል እርዳታ መጥቶልናል፡፡ ለተፈናቀሉ ዜጎች የተላከው ድጋፍ በወቅቱ ደርሷል ወይ የሚለውን ግን ቦታው ላይ በሚገኙ ሰዎች ክትትል በማድረግ እንዲያሳውቁ እናደርጋለን›› ብሏል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ በዞኑ ስር በሚገኙ በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶች ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው ቆይተዋል፡፡ ከ2015.ዓ.ም አጋማሽ አንስቶ ደግሞ በርካቶች ወደየ አካባቢአቸው መመለሳቸውን የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ታምራት ዲንሳ
ፀሀይ ጫኔ