የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የገነተልዑል ሕንጻን እድሳት
ዓርብ፣ መጋቢት 12 2017
አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስድስት ኪሎ ግቢ የሚገኘውን የገነተልዑል ሕንጻን ሊያድስ መሆኑን ተነገረ ፡፡ ጥንታዊው የገነተልዑል ህንፃ እስካሁን ድረስ፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቤተመጻሕፍትን፣ የዩኒቨርሲቲው የሴኔት መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የአስተዳደር ቢሮዎችን እና የኤትኖግራፊክ ሙዝየምን በመያዝ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱንየገለፀው ዩኒቨርሲቲው፣ አሁን ህንፃው ታሪካዊነቱን በጠበቀ መልኩ ይታደሳል ብሏል።
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የገነተልዑል ቤተመንግሥታቸው፣ ለዩኒቨርሲቲነት እንዲያገለግል በስጦታ ያበረከቱት በ 1950ዎቹ የተሞከረባቸውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል። ይኸው የገነተልዑል ቤተመንግሥት፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምነት ተቀይሮ፣ በመጀመሪያ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ከዛም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለሀገሪቱ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የዲጂታላይዜሽንና የመሠረተልማት ምክትል ፕሬዝደንት፣ ወንደሰን ሙሉጌታ በሰጡን ቃለመጠይቅ፣ የገነተልዑል በየጊዜው መጠነኛ የሚባሉ እድሳቶች ሲደረጉለት እንደነበር ገልፀው፣ አሁን ግን በጥናት ላይ የተመሰረተ የተሟላ እድሳት ይደረግለታል ሲሉ ተናግረዋል።
በእድሳት ጥናቱ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር ምሁራንና ሌሎችም የሚመለከታው አካላት ተሳትፈዋል ያሉት ወንደሰን ሙሉጌታ፣ እድሳቱ የገነተልዑል ሕንጻን ታሪካዊነት በሚያስጠብቅ መንገድ እንደሚከናወን አብራርተዋል
የእድሳት ንድፉን የሠራው አማካሪ ድርጅት፣ መቼ ምን ዓይነት ግብአት መጠቀም እንዳለበት የሚገልፅ፣ ዝርዝር ጥናት ማቅረቡን የገለፁት ምክትል ፕረዝደንቱ፣ ታሪኩን የሚገልፁና የሚያፀባርቁ በርካታ መረጃዎችም ተሰብስበው በሥራው ሒደት ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለዋል። እድሳቱ በጣሊያን መንግሥት ድጋፍ እንደሚከናወን የተናገሩት ኃላፊው፣ ለሕንጻው አጠቃላይ እድሳትና ከዛም በኋላ ለሚደረጉ የቁሳቁስ ማሟላት ሥራዎች፣ የአራት ሚሊዮን ዩሮ በጀት እንደተያዘ አስታውቀዋል። በራስገዝ ሂደት ላይ ያለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከዚህ ከገነተልዑል ሕንጻ በተጨማሪ፣ በግቢው ውስጥ የሚገኙትን የሕግ ትምህር ቤት እና የኬኔዲ ቤተመጽሐፍት ሕንጻዎችንም በቅርቡ ማደሱን ወንደሰን ሙሉጌታ ተናግረዋል።
ሃና ደምሴ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ