የጀርመን ምክር ቤት ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ያረቀቁትን ስደተኞችን የሚያግድ ሕግ ውድቅ አደረገ
ዓርብ፣ ጥር 23 2017የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት (CDU) እና የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት (CSU) የተባሉት ወግ አጥባቂ እሕትማማች ፓርቲዎች ያረቀቁትን ስደተኞችን የሚያግድ ሕግ ውድቅ አደረገ ። ሁለቱ ፓርቲዎች ያረቀቁት ሕግ በጠባብ ልዩነት ወድቋል። ከጠንካራ ክርክር በኋላ በተሰጠው ድምጽ 350 የምክር ቤት አባላት ሲቃወሙት 338 ደግፈውት ነበር። አምስት የምክር ቤት አባላት ደግሞ ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል።
ረቂቁ ወደ ጀርመን የሚገቡ ስደተኞች በየትዉልድ ሐገራቸዉ ያሉ የቅርብ የቤተሰሰብ አባላት (ባል፣ ሚስት፣ ልጅ ወዘተ) ወደ ጀርመን እንዳያስመጡ የሚያግድ ነዉ። ረቂቁ፣ ሕገ-ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን ወደ የመጡበት ለመመለስ ፖሊስ ተጨማሪ ሥልጣን እንዲሰጠዉ፣ ስደተኞች ወደ ጀርመን እንዳይገቡ ፖሊስ በየድንበሩ፣ በየአዉሮፕላን ማረፊያ እና ባቡር ጣቢያዎች ላይ የሚያደረገዉ ፍተሻ እና ቁጥጥር እንዲጠናከር ይጠይቃል።
የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት መሪ ፍሬድሪሽ ሜርስ ረቂቁ በጀርመን ምክር ቤት (ቡንደስታግ) እንዲፀድቅ አማራጭ ለጀርመን (AFD) የተባለዉን የቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ ድጋፍ እንደሚቀበሉ ማሳወቃቸዉ ከፍተኛ ቁጣ እና ተቃዉሞ ገጥሞት ነበር። ረቂቁ ዛሬ ጧት ለጀርመን ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ ነበር። ይሁንና ፍሬድሪሽ ሜርስ አማራጭ ለጀርመን (AFD) የተባለውን ቀኝ አክራሪ ፓርቲ ድጋፍ የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስን አስቆጥቷል።
በዚህም ምክንያት በሥልጣን ላይ ያለዉ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (SPD) እና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ መሪዎች ደንቡን ካስረቀቁት ከፍሬድሪሽ ሜርስ ጋር በዝግ የሚያደርጉት ክርክር በመቀጠሉ ረቂቁ ለምክር ቤት የሚቀርብበት ጊዜ ተራዝሞ ማምሻውን ነው ድምጽ የተሰጠበት።
ቀደም ሲል ረቂቅ ደንቡን እንደሚደግፍ አስታዉቆ የነበረዉ ለዘብተኛዉ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (FDP) አቋሙን ለዉጦ ረቂቁ ዳግም በኮሚቴ እንዲጠና ጠይቋል። ረቂቁን በመቃወም በየከተማዉ የሚደረገዉ የአደባባይ ሠልፍም እንደቀጠለ ነዉ። የቀድሞዋ መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ረቂቁን ተቃውመዋል።
ጀርመን ዉስጥ በመጪዉ የካቲት አጠቃላይ ምርጫ ይደረጋል። እስካሁን ይፋ በሆነዉ የሕዝብ አስተያየት መሠረት ወግ አጥባቂዉ የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት (CDU) ከፍተኛ ድምጽ ያገኛል ተብሎ ይገመታል። አማራጭ ለጀርመን (AFD) ደግሞ ሁለተኛዉን ከፍተኛ ድምፅ ሊያገኝ ይችላል።