የጀርመን ምርጫ 2025 ፋይዳ ተግዳሮቶቹና አስተምህሮቱ
እሑድ፣ የካቲት 16 2017ጀርመን ዛሬ 21ኛውን አጠቃላይ ምርጫ እያካሄደች ነው ። ከመደበኛው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ አስቀድሞ በተካሄደው በዚህ ምርጫ ጀርመናውያን ተወካዮቻቸው እንዲሆኑ ለመረጧቸው እጩዎች ድምጻቸውን ሲሰጡ ውለዋል። ከጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የተቋቋመው የጀርመን ጥምር መንግስት ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የማይዘልቅ ጋብቻ እየተባለ ሲተች ነበር። በጀርመን መንግሥት ታሪክ በአመዛኙ የማይገናኝ አቋም ያላቸው ሦስት ፓርቲዎች የመሰረቱት ተጣማሪ መንግስት እንደተፈራው ከሦስት ዓመት በላይ አልዘለቀም። አንድ የስልጣን ዘመን ሊደፍን አንድ ዓመት ያህል ሲቀረው ህልውናው አበቃ።
የጀርመን ገንዘብ ሚንስትር ተባረሩ፣ ተጣማሪዉ መንግሥት ፈረሰ
በዚህ ሰበብ ከጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም. መጨረሻ አንስቶ ጀርመንን ሲመራ የቆየው፣ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ SPD፣ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲና የነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ በምህጻሩ FDP ጥምር መንግሥት በጎርጎሮሳዊው ህዳር 2024 ዓ.ም. ከፈረሰ በኋላ አዲስ ምርጫ መጥራት ግድ ሆነ። ጥምሩ መንግሥት በፈረሰ በሦስተኛው ወር ምርጫ እንዲካሄድ ተወሰነ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ነበር ጎርጎሮሳዊው የካቲት 23 ቀን 2025 ዓ.ም. ማለትም ዛሬ ምርጫው የተደረገው ።
ወቅቱን ያልጠበቀው ይህ ምርጫ ከተጠራ ወዲህ ፖለቲከኞች የመራጩን ህዝብ ድጋፍ ያስገኙልናል ያሏቸውን ጉዳዮች እያጎሉ ሲቀሰቅሱ ከርመዋል። በተለይ በፍልሰት ጉዳዮች ላይ የተነሱ ውዝግቦችና ተቃውሞዎች ጎልተው ወጥተዋል። የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትም በጉልህ ታይቷል። ጀርመናውያን በተለያዩ ወሳኝ በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተከፋፈለ አቋም መያዛቸው የምርጫውን ውጤት አጓጊ አድርጎታል። የዛሬው እንወያይ በጀርመን ምርጫ ሂደት ፣ ፋይዳ ተግዳሮቶቹና አስተምህሮቱ ላይ ያተኩራል።
የመታመኛ ድምጽ የተነፈጉት መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና መጪው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ
በዚህ ውይይት ላይ የሚሳተፉ ሦስት እንግዶችን ጋብዘናል። እነርሱም ከጀርመን ፍራንክፈርት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የሕግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ። ከበርሊን የኤኮኖሚ ባለሞያ፣ ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ እንዲሁም የዶቼቬለ የብራሰልስ ዘጋቢ ገበያው ንጉሴ ናቸው። እንግዶቻችን በውይይቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆናችሁ ስለተገኛችሁልን አመሰግናለሁ።
ሙሉውን ውይይት ለማዳመጥ ከታች የሚገኘውን የድምጽ ማዕቀፍ ይጫኑ
ኂሩት መለሰ