የጀርመን ምርጫ፤ የአውሮጳ ኅብረት መሪዎች፤ ፍሬድሪክ ሜርስን እንኳን ደስ ያሎት ብለዋል
ሰኞ፣ የካቲት 17 2017የጀርመን ምርጫ ዉጤት እና የአዉሮጳ ህብረት አባላት ግብረ መልስ
„የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ ውጤትን ተከትሎ በአብዛኛዉ ሁለት አይነት አስተያየቶች ናቸዉ የተንፀባረቁት። የአዉሮጳ ህብረትን የሚደግፉት እንደ ፈረንሳይ የመሳሰሉ መንግስታት አብዛኞቹ ሃገራት ፍሬድሪክ ሜርስ የሚመሩት የክርስትያን ዴሞክራት ህብረት / የመሐል ቀኙ ፓርቲ ማሸነፉን አወድሰዋል። ብሪታንያም ብትሆን የክርስትያን ዴሞክራት ህብረት ማሸነፉን በበጎ ነዉ የተመለከቱት። አብረዉ ለመስራትም ዝግጁ መሆናቸዉን ገልፀዋል። በህብረቱ ሌሎች ጥቂቶች የቀኝ አክራሪዉን ፓርቲ፤ አማራጭ ለጀርመን (AFD)በጀርመን ፓርላማ ለመጀመርያ ጊዜ በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥርን በማግኘቱ ደስታቸዉን የገለፁ አሉ። ለምሳሌ የሃንጋሪዉ ጠቅላይ ሚኒስትር እንኳን ደስ አሎት ብለዉ የደስታ መግለጫን የሰጡት ለቀኝ አክራሪዉ ፓርቲ መሪ ነዉ። የጣልያንዋ ጠቅላይ ሚኒስትርም እንዲሁ። ስለዚህ በአጠቃላይ የአዉሮጳ ኅብረት አቀንቃኙ ክፍል ፤ የጀርመንን መሐል ቀኝ ፖርቲ ተመርጦ ወደ ስልጣን መምጣት ፤ አብሮ ለመስራት በበጎ ነዉ ደስታቸዉን የገለፁት። „
በአዉሮጳ ህብረት ጀርመን መንግሥት መስርታ እስክትመጣ እየተጠበቀ ነዉ? እንደሚታወቀዉ አዉሮጳ ዉስጥ ብዙ አጀንዳ አለ። የዩክሬይን ሩስያ ጦርነት፤ የስደተኞች ጉዳይ፤ በትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ አዉሮጳ ህብረት ግንኙነት?
„ ጀርመን ለአዉሮጳ ህብረት ሞተር ነች ይባላል። ጀርመን በኢኮኖሚዉም ፤ በህዝብ ብዛቱም። በህብረቱ ዉሳኔ የሚሰጠዉም በህዝብ ብዛት እና በኤኮኖሚ አቅምም ነዉ። ስለዚህ በህብረቱ ጀርመን ቀዳሚዉን ስፍራ ይዛ ትገኛለች። የአዉሮጳ ህብረት ጥንካሪ ከጀርመን ጥንካሪ ጋር የተያያዘ ነዉ። በመራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ መስተዳድር ጀርመን በህብረቱ የተፈለገዉን ያህል ጠንካራ አልነበረችም። ፈረንሳይም አሁን ባለዉ ሁኔታ ፕሬዚዳንት ማክሮ ጠንካራ አይደሉም። እነዚህ ሁለቱ የአዉሮጳ ህብረት ኃያል አገሮች ጠንካራ ባለመሆናቸዉ፤ በአዉሮጳ ህብረት ላይም ተሰሚ ሊሆኑ አልቻሉም። ስለዚህ አሁን የአዉሮጳ ህብረት ከፍተኛ ፈተና ላይ ነዉ ያለዉ፤ የደህንነት ፈተና አለበት ፤ የስደተኞች ወይም የፍልሰተኞች ፈተና አለበት፤ የኤኮኖሚ ፈተና አለበት፤ በተለይ በዩክሪን ያለዉ ጦርነት፤ ጦርነቱ እንዴት ያብቃ እርዳታዉ እንዴት ይቀጥል የሚለዉ ሁሉ መልስ የሚጠብቅ ነዉ። የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር እና የህብረቱ ግንኙነት። ስለዚህ በአዉሮጳ ህብረት በአሁኑ ወቅት ጠንካራ የሆነ አመራር ያስፈልጋል። አሁን አዲሱ የጀርመን አስተዳደር ጠንካራ ሆኖ ይወጣል ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጦታል። „
ሙሉዉን ቃለ ምልልስ እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!
ገበያዉ ንጉሴ / አዜብ ታደሰ
ዮኃንስ ገብረእግዚአብሔር