የጀርመን ምርጫ ዐበይት ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?
እሑድ፣ የካቲት 16 2017አጭር ነገር ግን ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት የጀርመን የምረጡኝ ዘመቻ የአቅጣጫ ለውጥ የሚለው ሐረግ ተደጋግሞ ተደምጧል። የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት (CDU) እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት (CSU) እህትማማች ፓርቲዎችን በመወከል ለመራኄ መንግሥትነት የተሚወዳደሩት ፍሬድሪሽ ሜርስ “ለሦስት ዓመታት በጀርመን ግራ ዘመም ፖሊሲ ሥራ ላይ ለማዋል ሞክራችኋል። የአጠቃላይ ምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን እንደዚያ እያደረጋችሁ መቀጠል አትችሉም” ሲሉ ከሁለት ሣምንታት በፊት ተናግረው ነበር።
ሜርስ በጀርመን ምክር ቤት ይህን ያሉት ከጎርጎሮሳዊው 2021 ጀምሮ ጥምር መንግሥት መሥርተው ሀገሪቱን ለመሩት የሶሻል ዴሞክርቶች (SPD)፣ አረንጓዴዎቹ እና ነጻ ዴሞክራቶች (FDP) ነበር። ሁለት ግራ ዘመም ፓርቲዎች ነጻ ገበያን ከሚያቀነቅነው ፓርቲ ጋር የመሠረቱት ጥምር መንግሥት ባለፈው ኅዳር ከወራት ውዝግብ በኋላ ፈረሷል። በዚህ መሠረት ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ምርጫ ይካሔዳል።
ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ የተጋረጠበት አደጋ
ጥምር መንግሥቱን ከመሠረቱ ፓርቲዎች መካከል አረንጓዴዎቹ ከሕዝብ በተሰበሰበ አስተያየት በጎርጎሮሳዊው 2021 ከነበራቸው የሚቀራረብ ድጋፍ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይጠበቃል። የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ እና የነጻ ዴሞክራት ፓርቲዎች ግን አሽቆልቁሏል። ነጻ ዴሞክራቶች ምክር ቤት ለመግባት ከሚያስፈልጋቸው 5 በመቶ ድምጽ በታች ሊያገኙ ይችላሉ። የመራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ በአንጻሩ መራር ሽንፈት ሊገጥመው ይችላል። ከ20 በመቶ በታች ድምጽ ማግኘት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አስከፊው ውጤት ነው። ከሕዝብ በተሰበሰበ አስተያየት መሠረት ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ይህን ማሳካት የሚችል አይመስልም።
ፓርቲው ከተሸነፈ ኦላፍ ሾልስ በባለፉት 50 ዓመታት የጀርመን ታሪክ ለአጭር ጊዜ የመሩ መራኄ መንግሥት ይሆናሉ። በድጋሚ መመረጥ የተሳናቸው የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ብቸኛ መራኄ መንግሥትም ያደርጋቸዋል።
ወግ አጥባቂዎቹ እህትማማቾች ይመራሉ፤ ቀኝ አክራሪው ይከተላል
ከሕዝብ በተሰበሰበ አስተያየት መሠረት ፍሬድሪሽ ሜርስ ቀጣዩ መራኄ መንግሥት የመሆን የተሻለ ዕድል አላቸው። ሜርስ ለ16 ዓመታት ጀርመንን የመራው እና ከጎርጎሮሳዊው 2021 ጀምሮ ጠንካራ ተቃዋሚ ለመሆን የበቃውን የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ጥምረት ይመራሉ።
ቀኝ አክራሪው አማራጭ ለጀርመን (AfD) በምርጫው 20 በመቶ ድምጽ ሊያገኝ እንደሚችል ከሕዝብ የተሰበሰበ አስተያየት ይጠቁማል። ይህ ከአራት ዓመታት በፊት ፓርቲው ከነበረው ድምጽ በሁለት እጥፍ የላቀ ነው።
የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ (SPD) አስደንጋጭ ሁኔታ ሲያሽቆለቁል አማራጭ ለጀርመን እንዴት የተሻለ ውጤት ለማግኘት በቃ? ፍሬድሪሽ ሜርስ የኢኮኖሚውን ውድቀት በምክንያትነት ያቀርባሉ።
ፍሬድሪሽ ሜርስ “የሀገራችን፤ የጀርመን ፌድራል ሪፐብሊክ ኢኮኖሚ በአውሮፓ ኅብረት በመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛል።ኢኮኖሚያችን እየቀነሰ ነው። ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት ቁልቁል ሔዷል። ይህ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ባለው የጀርመን ታሪክ ተፈጥሮ አያውቅም” ሲሉ ተናግረዋል። ሾልስ እና አረንጓዴዎቹን ፓርቲ ወክለው ለመራኄ መንግሥትነት የሚወዳደሩት የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሐቤክ “እውነታውን አላስተዋሉም” እያሉ ሜርስ ተችተዋል።
ጦርነት፣ የኃይል ቀውስ እና የዋጋ ግሽበት
ሜርስ እንደ መራኄ መንግሥት ዕጩነታቸው በምረጡኝ ዘመቻው በኃይል ሲተቹ ኦላፍ ሾልስ በፊናቸው በመከላከሉ ላይ ተጠምደዋል። ከቀደሙት ዓመታት በተሻለ ደፋር እና በራሳቸው የሚተማመኑ ሆነው ቢታዩም በተደጋጋሚ ፖሊሲዎቻቸውን መከላከል እና አስፈላጊነታቸውንም ለማብራራት ተገደዋል።
በጀርመን የኃይል ቀውስ የፈጠረው መንግሥታቸው ሳይሆን ሩሲያ በዩክሬን የምታካሒደው ወረራ ነበር። “ሩሲያ ዩክሬንን አጠቃች። በመቶ ሺሕዎች የተገደሉበት እና የቆሰሉበት አስከፊ ጦርነት በመሀል አውሮፓ ለሦስት ዓመታት እየተካሔደ ነው። እዚህም የዚህ ጦርነት ዳፋ እየተሰማን ነው። በየቀኑ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦታችን ተቋርጧል። ኢኮኖሚው ዛሬም ከመዘዙ ጋር እየታገለ ነው። ከ1970ዎቹ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ገጥሞናል። በቁጥጥር ሥር ለማዋል ታግለናል” ብለዋል።
ሾልስ እንዳሉት በአሜሪካ እና በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ “የሚያበሳጩ” ጥያቄዎች ምክንያት ሁኔታው በመጪዎቹ ዓመታትም የሚሻሻል አይደለም።
ትልቁ ጉዳይ፦ ፍልሰት
በምረጡኝ ዘመቻው ወቅት ደካማው ኢኮኖሚ ዋንኛ መነጋገሪያ የነበረ ቢሆንም በባቫሪያ ግዛት በምትገኘው አሻፍንቡርግ የተገን ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ስደተኛ ከፈጸመው የስለት ጥቃት በኋላ ፍልሰት ትኩረት ተሰጥቶታል። ከጥቃቱ በኋላ ፍሬድሪሽ ሜርስ የጀርመን የፍልሰት ፖሊሲን ለማጥበቅ ከቀኝ አክራሪው ፓርቲ ጋር በመሆን የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤት አቅርበው ነበር።
በጥር መጀመሪያ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት የውሳኔ ሐሳብ በቀኝ አክራሪው ፓርቲ እገዛ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ነበር። የአማራጭ ለጀርመን የምክር ቤት አባላት ቡድን ጸሀፊ ቤርድ ባውማን “እዚህ አሁን አዲስ ምዕራፍ ይጀምራል” ሲሉ ፓርቲያቸው ጉዳዩን ለማስፈጸም ለአጣማሪነት በመብቃቱ ደስታቸውን ገልጸው ነበር።
ከአክራሪ ቀኝ አክራሪ ጋር ትብብር አይኖርም
በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ቀኝ የተደረገውን ማዘንበል በመቃወም በሀገሪቱ ምክር ቤት በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ሰልፍ አድርገዋል። በተለይ ሾልስ ቁጡ ነበሩ። “ከቀኝ አክራሪ ጋር ብትሰሩ ትርጉም የለውም። በጀርመን አይሆንም። የጀርመን ሪፐብሊክ ከ75 ዓመታት በፊት ከተመሠረተ ጀምሮ በሁሉም ዴሞክራቶች ዘንድ ግልጽ መግባባት አለ። ከቀኝ አክራሪዎች ጋር በምክር ቤቶቻችን የጋራ ጉዳይ አይኖረንም። ነገር በተጋጋለበት ቅጽበት ይህን የሪፐብሊካችን መሠረታዊ መግባባት ሽረዋል” ሲሉ ተችተዋል።
ከዚያ በኋላ ትችት የበረታባቸው ሜርስ ከአማራጭ ለጀርመን ጋር ትብብር እንደማይኖር ለመግለጽ ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ከመጠቀም አልተቆጠቡም። የቀኝ አክራሪዎቹ ዓላማ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረትን ለማፍረስ ነው ሲሉ ተችተዋል። ሜርስ እንዳሉት በምንም አይነት ሁኔታ እህትማማቾቹ ፓርቲዎች ከአማራጭ ለጀርመን ጋር ጥምረት አይመሠርቱም።
ማን ጥምር መንግሥት ሊመሠርት ይችላል?
የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ብቻቸውን መንግሥት መመሥረት አይችሉም። ከምርጫው በኋላ ቢያንስ አንድ አጣማሪ ያስፈልጋቸዋል። ምክር ቤት የሚገቡ ፓርቲዎች ቁጥር በጨመረ ቁጥር መንግሥት መመሥረት የበለጠ አስቸጋሪ ይሆናል። እስካሁን የተሰበሰቡየሕዝብ አስተያየቶች ግራ ዘመሙ ፓርቲ ምክር ቤት ሊገባ እንደሚችል ይጠቁማሉ። ዛራ ቫግነርክኔሽት ጥምረት (BSW) የተባለው ፓርቲ እና ነጻ ዴሞክራቶች በአንጻሩ ይንገዳገዳሉ።
ነጻ ዴሞክራት ፓርቲ ምክር ቤት ከገባ ጥምር መንግሥት ለመመሥረት ሦስት ፓርቲዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ። ነጻ ዴሞክራት ፓርቲ ከአረንጓዴዎቹ ጋር ጥምር መንግሥት እንደማይመሠርት ወስኗል። የቀረው አማራጭ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ከሶሻል ዴሞክራቶች እና ከነጻ ዴሞክራቶች መጣመር ነው። ምክር ቤት የሚገቡ ፓርቲዎች ቁጥር አነስተኛ ከሆነ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ከሶሻል ዴሞክራቶች ጋር ሊጣመሩ ይችላሉ። ወይም ሁለቱ እህትማማች ፓርቲዎች ከአረንጓዴዎቹ ጋር ተጣምረው መንግሥት ሊመሠርቱ ይችላሉ።
የተገለለው አማራጭ ለጀርመን
አማራጭ ለጀርመን በመወከል ለመራኄ መንግሥትነት የሚወዳደሩት አሊስ ቫይድል ግን እንዲህ አይነት ጥምረት አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ ፖሊሲዎች እንዲቀጥሉ መንገድ ይከፍታል ሲሉ ይነቅፋሉ።
“የምታሳኩት በአንጌላ ሜርክል እና በአረንጓዴ እና ቀይ ጥምረት ወደ ጽንፍ የተወሰደውን ሀገራችንን የማፍረስ ሥራ ነው። ይህም ይቀጥላል” ሲሉ ኮንነዋል። ቫይድል ይዘገያል እንጂ ፓርቲያቸው የሚፈልገው ለውጥ እንደሚመጣ እርግጠኛ ናቸው።
አማራጭ ለጀርመን የፍልሰት ፖሊሲን እንዲደግፍ ከተሞከረው ጥረት በኋላ ሶሻል ዴሞክራቶች እና አረንጓዴዎቹ፤ ከየክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ያላቸው ግንኙነት ጥሩ አይደለም። በስተመጨረሻ ጥምር መንግሥቱ እያንዳንዱ ፓርቲ ፖለቲካዊ አጀንዳዎቻቸውን ምን ያክል መግፋት ይችላሉ በሚለው ላይ ይወሰናል።
በምረጡኝ ዘመቻው ቸል የተባለው የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ
ሶሻል ዴሞክራቶች ማኅበራዊ ፖሊሲን ያስቀድማሉ፤ አረንዴዎቹ የአካባቢ ጥበቃ የበለጠ ያሳስባቸዋል። አረንጓዴዎቹን ወክለው ለመራኄ መንግሥትነት የሚወዳደሩት ሮበርት ሐቤክ ማሳሰቢያ አላቸው።
“ሮበርት ሐቤክ ጀርመን የካቲት 23 የአካባቢ ጥበቃ ግቦችን እንደማያሳካ ይፋ የሚያደርግ መንግሥት ከመረጠች አውሮፓም የአካባቢ ጥበቃ ዓላማውን ማሳካት አይፈልግም። ከዚያ የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ያበቃለታል። የትኛውም ቻንስለር፣ ማንኛውም የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር፣ ማንኛውም ኮሚሽነር ወደ ሕንድ፣ ኢንዶኔዥያ ወይም ቻይና ሔዶ ሰዎች ድንጋይ ከሰል ማቃጠል አቁሙ፤ የበለጠ ታዳሽ ኃይል ተጠቀሙ ማለት አይችልም” በማለት አስጠንቅቀዋል።
ፍሬድሪሽ ሜርስ ድርድሮቹ ቀላል እንደማይሆኑ ያውቁታል። ከምርጫው በኋላ ግን የጀርመን ችግሮችን የመፍታት “ፖለቲካዊ ኃላፊነት” አለ። ይህ የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ተቀባይነት እንዲያገኝ የረዳውን የመራቢያ መሠረት ለማክሰም “ከመጨረሻዎቹ ዕድሉች አንዱ” እንደሆነ ገልጸዋል።