የጀርመን መራጮች ማንን ሊመርጡ ተዘጋጁ?
ሐሙስ፣ የካቲት 6 2017በጀርመን አገር አቀፍ ምርጫ ሊከናወን ከሁለት ሳምንት በታች ቀርቶታል ። በተለይ የፍልሰተኞች ጉዳይ ዋነኛ መነጋገሪያ በሆነበት የዘንድሮ ምርጫ መራጮች በምሥራቁ የጀርመን ክፍል አስተያየታቸው ምን ይመስላል? ከዚህ ከዶይቸቬለ የአፍሪቃው ክፍል የዘንድሮ ምርጫ ቅድመ ሁኔታን እንዲመለከቱ ከተላኩ የአፍሪቃው ክፍል ጋዜጠኞች መካከል ባልደረባችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔርም ይገኝበታል ።
ወደ ስቱዲዮ ከመግባቴ በፊት ዮሐንስን በስልክ አነጋግሬዋለሁር ። እስካሁን በቅድመ ምርጫው የተመለከቷቸው ከተሞች እና የሕዝቡን ስሜት በማብራራት ይጀምራል ።
በርካታ የደሕንነት ሥጋት ያለባቸው መራጮች የቀኝ አክራሪዎችን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን መታዘቡን ዮሐንስ ገልጧል ። በጀርመን ሙይንሽን ከተማ በተሰበሰበ ሕዝብ መካከል በዛሬው ዕለት አንድ አሽከርካሪ ባደረሰው ጥቃት 28 ሰዎች መጎዳታቸው ፖሊስ ተገለፀ ።
የሙይንሽን የእሳት አደጋ መከላከያ ቡድን እንደገለፀው አንድ አሽከርካሪ መኪናውን ወደ ሕዝቡ አቅጣጫ በመንዳቱ በጀርመን ደቡባዊ ግዛት የባቫሪያ ዋና ከተማ በሆነችው ሙይንሽን በትንሹ 28 ሰዎች አቁስሏል ። አደጋውን ያደረሰው የ24 ዓመት አፍጋኒስታዊ ጥገኝነት ጠያቂ እንደሆነ እና ከጥቃቱ በኋላ ወዲያውኑ በፖሊስ መያዙን የሙይንሽን ፖሊስ ዛሬ ከስዓት በኋላ ዐሳውቋል ። ጀርመን ውስጥ በውጭ አገር ተወላጆች በቅርቡ የተከሰቱ ተደጋጋሚ የስለት እና የተሽከርካሪ ጥቃቶች የፍልሰትን ጉዳይ ዐቢይ የምርጫ ርእስ አድርጎታል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
ሸዋዬ ለገሠ