መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ እና ተቃዋሚው ፍሬድሪሽ ሜርስ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንትን ተቹ
ቅዳሜ፣ የካቲት 8 2017የጀርመን መራኄ-መንግሥት ኦላፍ ሾልስ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ጄድ ቫንስ አውሮፓ ለቀኝ አክራሪዎች በሩን እንዲከፍት ያቀረቡትን ጥሪ በመቃወም በጀርመን “ዴሞክራሲ ውስጥ የውጪ ጣልቃ ገብነትን” እንደማይቀበሉ ተናገሩ።
የተቃዋሚው ክርስቲያን ዴሞክራቶች መሪ ፍሬድሪሽ ሜርስ እንደ ሾልስ ሁሉ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ትላንት አርብ በሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ያሰሙትን ንግግር ኮንነዋል።
ጄድ ቫንስ በንግግራቸው የአውሮፓ መሪዎች ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ሳንሱር ያደርጋሉ ሲሉ ከሰው ነበር። አማራጭ ለጀርመን (AfD) የተባለውን ቀኝ አክራሪ የጀርመን ዋና ዋና ፓርቲዎች ይገፋሉ የሚል ክስም የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት አቅርበዋል።
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ግን በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት እና ምርጫ ውስጥ “የውጪ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት አንቀበልም“ ብለዋል።
“ይህ በተለይ በወዳጆች እና በአጋሮች መካከል ተገቢ አይደለም” በማለት በሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ላይ ዛሬ ቅዳሜ ባሰሙት ንግግር የጄድ ቫንስን ክስ “አጥብቀን እንቃወማለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
የተቃዋሚው ክርስቲያን ዴሞክራቶች መሪ ፍሬድሪሽ ሜርስ በበኩላቸው ከዶቸ ቨለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አሜሪካ “በይፋ በምርጫ ጣልቃ እየገባች ነው” ሲሉ ኮንነዋል።
“አሜሪካ የምትሰጠው የጸጥታ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ ነው። አሜሪካኖች የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው” ሲሉ ፍሬድሪሽ ሜርስ ተናግረዋል።
የአውሮፓ መንግሥታት ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን እየደፈጠጡ፤ መራጮችን ገሸሽ እያደረጉ ነው በማለት የወነጀሉት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ዴሞክራሲን ያፈርሳሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረው ነበር።
የቫንስ ንግግር “የሚረብሽ” እንደሆነ የገለጹት ፍሬድሪሽ ሜርስ ግን “የዴሞክራሲ ተቋማትን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን ለጀርመን ማስረዳት የአሜሪካ መንግሥት ሥራ አይደለም። በራሳችን አካሔድ እንቀጥላለን” በማለት እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።
ጀርመን ከአስር ቀናት በኋላ ምርጫ ለማካሔድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። እስካሁን በተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች ወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት (CDU) ሊያሸንፍ እንደሚችል ይጠቁማሉ።