የሾልስና የማክሮ ንግግር በፓሪስ
ረቡዕ፣ ጥር 14 2017
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስና የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈረመውን የኢሊሴን ውል 62ተኛ ዓመት እና የአኸን ስምምነትን 6ኛ ዓመት በጋራ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ፓሪስ ውስጥ አክብረዋል። ሁለቱ መሪዎች በወቅታዊ የአውሮጳና የዓለም ጉዳዮች ላይም ተነጋግረዋል። ሆኖም ንግግራቸው በአዲሱ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ዘመነ ሥልጣን አውሮጳ ሊገጥመው የሚችለው ፈተና ላይ ያተኮረ ነበር ።ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮና ፣ መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ዛሬ ፓሪስ ዉስጥ ባደረጉት ንግግር የትራምፕን መርሕ ለመቋቋም አዉሮጳ ጠንካራ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለበት መስማማታቸውን ዛሬ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ዉይይት ከመከላከያዉ ጉዳይ ይልቅ አዉሮጳ ከአሜሪካ ጋር ለሚኖራት የንግድ ግንኙነት ልዩ ትኩረት መስጠታቸዉ ተዘግቧል። የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ የትራምፕ መርሕ ለአዉሮጳ ፈታኝ እንደሚሆን አሳዉቀዋልም።ጀርመንን ጨምሮ አብዛኞቹ የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግሥታት ሕብረቱ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር አዲስ የንግድ ስምምነት እንዲዋዋል ይፈልጋሉ። ፈረንሳይ ግን አዲስ ስምምነት ከመፈራረም ይልቅ የትራምፕ መስተዳድር በአዉሮጳ ሸቀጦችና ኩባንዮች ላይ አዲስ ታሪፍ ከጣለ፣ አዉሮጳም በአሜሪካ ሸቀጦችና ኩባንዮች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ መዉሰድ አለባት ባይ ናት። ሁለቱ መሪዎች ዛሬ ፓሪስ ውስጥ ስላካሄዱት ጋዜጣዊ መግለጫ የፓሪስዋን ዘጋቢያችንን ሃያማኖት ጥሩነህን በስልክ አነጋግረናታል።
ሃይማኖት ጥሩነህ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ