የዶይቸቬለ ዋናው ስቱዲዮ የቀን ተቀን አሠራርን በጥቂቱ እናስቃኛችሁ
እሑድ፣ መጋቢት 28 2017ዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል ለስድሳ ዓመታት በፊት ከአመሻሹ 11 ሰአት ላይ፥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ ሥርጭቶቹን በቀጥታ ለአድማጮች ያደርሳል ። የየቀኑ የአንድ ሰአት ሥርጭቶቹን ወደ አድማጮቹ ከማድረሱ አስቀድሞ በርካታ ሒደቶችን ያሳልፋል ። በዶይቸ ቬለ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ከተለያዩ ቦታዎች የሚሰበሰቡ መረጃዎች ወደ አድማጭ ከመድረሳቸው በፊት የሚያልፉበትን ሒደት ይዘረዝራል ። «መረጃዎች ከተለያዩ አካባቢዎች ይሰበሰባሉ፥ ይህን የሚያደርገው በየሳምንቱ የሚመደብ ኤስ አር የምንለው ወይንም አዘጋጁ ነው ። ከወኪሎቻችን፤ ከዓለም አቀፍ የዜና አገልግሎቶች፤ እና ከዚህ ከቤቱ የምንለው ከዶይቸ ቬለ የተለያዩ ክፍሎች የሚጻፉ ወይንም የሚደርሱ መረጃዎችን ያሰባስባል ። ከዚያ በኋላም የትኛው ለዚያ ቀን እና ለዚያ ጊዜ ተስማሚ ነው የሚባለው ይመረጣል፤ በምን መንገድ ይሠራል የሚለው እንደገና በውይይት ይወሰናል ። ይኼ ውይይት የሚደረገው ኤዲቶሪያል በምንለው ኮንፈረንስወይንም ስብሰባ ላይ ነው ።»
ዋናው ስቱዲዮ ጀርመን ቦን ከተማ ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች በተለያየ ጊዜያት የኤዲቶሪያል ስብሰባ ያደርጋሉ ። ስብሰባውን የክፍሉ ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ ወይም ተወካይ ይመራዋል ። በኤዲቶሪያል ስብሰባ የዳበረው የዘገባ ርእሰ ጉዳይን የሳምንቱ ተረኛ የሆነ ወሳኝ አርታዒ ከወኪሎች ጋር ይነጋገራል፤ ዘገባዎችን በጥንቃቄ ተመልክቶ ለአድማጭ ያደርሳል ። የዋናው ስቱዲዮ ባልደረቦች በሳምንት አንዴ በዙር የሥርጭት ወሳኝ አርታዒነት ኃላፊነት ይደርሳቸዋል፥ በጀርመንኛ ምኅጻሩ SR ሽሉስ ሬዳክሲዮን ይባላል እዚህ ኃላፊነቱ ።
ዶይቸ ቬለ የ60ኛ ዓመቱን የሚመለከት ዝግጅት ባቀናበረበት በዚህ ሳምንት የሳምንቱ ወሳኝ አርታዒነት ወይንም SR ተራ የደረሳት ባልደረባዬ ሸዋዬ ናት ። የሳምንት ወሳኝ አርታዒ የመሆን ተራ ሲደርስ በርካታ ኃላፊነቶች ተደራርበው ለዚያ ሥራ የተመደበው ሰው ላይ እንደሚያርፍ ገልጣለች ። «ሁሉ ኃላፊነት አንተ ነው ያለው» ያለችው ሸዋዬ፦ በጠዋት ከወኪሎቻችን ከሚላኩ ጥቆማዎች አንስቶ በተለያየ መንገድ የሚገኙ መረጃዎችን ተከታትሎ ወቅታዊነቱን ሳይለቅ እንደሚወሰድ ጠቁማለች ። የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሚና ከፍ በማለቱም የድምፅ፣ የፎቶ እና የቪዲዮ መረጃዎች ዘርፉ በሚፈልገው መልኩ ይሰናዳል ። በእነዚህ የሥራ ሒደቶች ሁሉ ኃላፊነቱ የሚያርፈው የሳምንቱ ተረኛ የሆነ ወሳኝ አርታዒ ላይ ነው ።
በዚህ መልኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በየአገራቱ ከሚገኙ ወኪሎች ዋናው ስቱዲዮ የሚደርሱ ዘገባዎች ለዜና እና ለዜና መጽሔት በሚመች መልኩ ተሰናድተው ወደ አድማጮች ይደርሳሉ ። ኂሩት መለሰ ይህ ዘገባ በተቀናበረበት ቀን የዕለቱን ዓለም አቀፍ ዜና እያሰናዳች ነበር ። የዜና ተረኛ ያዘጋጀውን «የዕለቱ አርታዒ ዜናውን ይመለከታል፤ ያርማል፤ ያስተካክላል» በማለት ከምንም በላይ ለዜና ቅድሚያ የሚሰጠው ለኢትዮጵያ እንደሆነ ገልጣለች ። ከዚያ በመቀጠልዓለም አቀፍ ዜናዎች ይከተላሉ ።
የዕለቱንን የዜና መጽሔት ጨምሮ ሌሎች ሥርጭቱ የሚሆኑ ዘገባዎችን በቀጥታ ሥርጭቱ የማስተናበር እና የመምራት ተራው የደረሰው ለባልደረባዬ አዜብ ታደሰ ነበር ። «ከኢትዮጵያ የሚደርሱንን የተለያዩ ዘገባዎች ተቀብዬ በማዳመጥ የሚታረመውን አርሜ ጽሑፉንም አስተካክዬ ድረ ገጻችን ላይ እከታለሁ» ያለችው አዜብ በቃለ መጠይቁ ወቅት ከወኪሎች የተላኩ መረጃዎችን አሰናድታ ጨርሳለች ። እናም ለድረ ገጻችን በሚመች መልኩ የተሰናዳውን ጽሑፍ ወደ ድረገጹ ከመላኳ በፊት የዕለቱ ተረኛኃላፊ አርታዒ የተዘጋጀውን ይመለከታል ።
ዶይቸቬለ ከራዲዮ ባሻገር ሥርጭቶቹን በአጠቃላይ በፌስቡክ፤ ዩቱዩብ እና ቴሌግራምን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችም ማሠራጨት ጀምሯል ። በቀጥታው ሥርጭታችን እንገናኝ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ