የትራምፕ ታክስ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከውን ሐዋላ ወደ ኢ-መደበኛው ገበያ ሊገፋ ይችላል
ረቡዕ፣ ግንቦት 27 2017ከአዲስ አበባ ባልቲሞር ከገባች ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ያስቆጠረችው ቅድስት ሁለት ልጆቿን እና እናቷን ለመደጎም በወር ቢያንስ 250 ዶላር ለመላክ በራሷ ላይ ግዴታ ጥላለች። ለዚህ ዘገባ ሲባል ስሟ የተቀየረው የ37 ዓመቷ የሕግ ምሩቅ በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የነበራትን ሥራ ጥላ አሜሪካ ከገባች ወዲህ ቃሏን ለመጠበቅ ውሎዋ ከአንዱ ሥራ ወደ ሌላው “መባከን” ሆኗል።
ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ስትጓዝ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝታ ስትደላደል ልጆቿን ለመውሰድ እያለመች ነበር። ነገር ግን ሁሉም ነገር እንዳሰበችው አልተፋጠነም። በሒደት ላይ ያለው የተገን ማመልከቻ መቼ እልባት እንደሚያገኝ ስትጠየቅ “ያስፈራል” ትላለች። ከዚያ ባሻገር ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ “አንድ፣ ትልቅ፣ ቆንጆ” የሚል ሥያሜ የሰጡት የሕግ ረቂቅ ውስጥ የተካተተው የሐዋላ ታክስ ቅድስትን በቀጥታ የሚመለከት ነው።
በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ የሀገሪቱን ሴኔት ይሁንታ የሚጠብቀው የሕግ ረቂቅ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የውጪ ሀገር ሰዎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሐዋላ ሲልኩ 3.5 በመቶ ታክስ እንዲከፍሉ ያስገድዳል። ሕጉ ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ቅድስት ለቤተሰቦቿ ለምትልከው 250 ዶላር 8.75 ዶላር አካባቢ ታክስ መክፈል ይኖርባታል።
“ገንዘብ አጥተው ይመስልሀል?” አለች ቅድስት ስለ የሕግ ረቂቁ ስትጠየቅ። በቴነሲ ግዛት ሜምፊስ ከተማ የሚኖሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዘሪሁን ተስፋዬ የአሜሪካ የሐዋላ ታክስ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር “የመንግሥትን ገቢ ማሳደግ እና ወጪውን መቀነስ” ዕቅድ አንድ አካል እንደሆነ ያስረዳሉ። ሕጉ ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ቅድስትን ጨምሮ በአሜሪካ የሚኖሩ እና ዜግነታቸውን ያልቀየሩ ኢትዮጵያውያን ታክስ ለመክፈል ይገደዳሉ።
በአሜሪካ ምን ያክል ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ በትክክል አይታወቅም። የአሜሪካ መንግሥት የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ሰነድ 364, 645 ገደማ ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዩናይትድ ስቴትስ እንደሚኖሩ ያሳያል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኢንቨስትመንት ፎረም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ አሰፋ ግን ቁጥሩ እስከ አንድ ሚሊዮን እንደሚገመት ተናግረዋል። ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ቁጥር በአሜሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የሚኖሩ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ አቶ ዮሐንስ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሲወዳደር በአሜሪካ የሚኖረው “በገንዘብ አንደኛ ነው” የሚሉት አቶ ዮሐንስ “ብዙ ሐብት ወደ ኢትዮጵያ በሐዋላ እና በኢንቨስትመንት በኩል የሚያስገባ ዲያስፖራ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ሐዋላ ግን ሙሉ በሙሉ በሕጋዊው መንገድ የሚያልፍ አይደለም። አቶ ዘሪሁን እንዲያውም ኢ-መደበኛው ሐዋላ “ከፍተኛውን ድርሻ” እንደሚይዝ ያምናሉ። “የሚሠሯቸው ሥራዎች ሕጋዊ ካልሆኑ፤ ያንን ገንዘብ ያመጡበት መንገድ የማይገለጽ ሆኖ ሲገኝ እንዲሁም አላስፈላጊ ክፍያዎችን እና ውጣ ውረዶችን ለማስቀረት ሲሉ ኢ-መደበኛ የሆነውን የገንዘብ አላላክ ይጠቀማሉ” ሲሉ አቶ ዘሪሁን ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ አብራርተዋል። አቶ ዘሪሁን እንደሚሉት “ሕጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ እና ገንዘባቸው የሚመዘገብ፤ የሚታወቅ ሰዎች የበለጠ ገንዘብ ለመላክ እንዲያስችላቸው ኢ-መደበኛ የሆነውን መንገድ ይጠቀማሉ።”
ሐዋላ ላኪዎች ከባንኮች እና ሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊዎች ይልቅ የጎንዮሽ ገበያውን እንዲመርጡ የሚገፋፉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ቀዳሚው በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለው የተመን ልዩነት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት (IMF) የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር በሐምሌ 2016 ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር የውጪ ምንዛሪ ግብይት በባንኮች እና በደንበኞቻቸው እንዲወሰን በማድረጉ በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለው የተመን ልዩነት በከፍተኛ ደረጃ ጠቧል።
ይሁንና አሁንም በሁለቱ ተመኖች መካከል ከፍተኛ ልዩነት ይታያል። በብሔራዊ ባንክ አማካኝ ዕለታዊ የምንዛሪ ጠቋሚ መሠረት ዛሬ የአንድ ዶላር ምንዛሪ 134 ብር ገደማ ቢሆንም በትይዩው ገበያ እስከ 156 ብር መድረሱን ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሐዋላ 5.1 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ፍጹም አረጋ አስታውቀዋል። ከዚህ ውስጥ ምን ያክሉ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የተላከ እንደሆነ ዶይቼ ቬለ ከአምባሳደር ፍጹም ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የዘጠኙ ወራት ሐዋላ አምባሳደር ፍጹም በ2016 ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል ካሉት 4.4 ቢሊዮን ዶላር በ700 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ከፍ ያለ ነው።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ በሐምሌ 2016 ተግባራዊ የተደረገው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ባስከተለው አዎንታዊ ተጽዕኖ ምክንያት ሐዋላ ካለፈው ዓመት አኳያ በ2017 ቢያንስ በ25 ፐርሰንት ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረው ነበር።
አቶ ዮሐንስ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ቡና፣ ሰሊጥ እና ጫት ከመሳሰሉ ሸቀጦች የወጪ ንግድ የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ በሕጋዊ መንገድ ከሚገባው ሐዋላ “በልጦ አያውቅም።” በትይዩው ገበያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ሐዋላ ከመደበኛው “ዕኩል ወይም የሚበልጥ” እንደሆነ የዓለም ባንክ ጥናት ማሳየቱን የሚናገሩት አቶ ዮሐንስ የውጪ ምንዛሪ ግብይት በባንኮች እና በደንበኞቻቸው ድርድር እንዲወሰን መደረጉ አዎንታዊ ለውጥ እንዳመጣ ያስረዳሉ።
የውጪ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲወሰን መደረጉ “በጣም ጥሩ ጅማሮ ነው። ብሔራዊ ባንክ መደነቅ አለበት” የሚሉት አቶ ዮሐንስ “አተገባበሩ ዕንከን አልባ ነው” ሲሉ ያሞካሹታል። ነገር ግን “የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር፤ መሸጥ እና መግዛት ላይ የሚቀሩ ገደቦች አሉ። እነዚህ ገደቦች ለባንኮቹ arbitrage ይፈጥራሉ” ሲሉ ተናግረዋል። በባንኮች ዘንድ ይታያል የሚሉት የውጪ ምንዛሪን መሸሸግ፤ ይፋዊ ያልሆነ ተጨማሪ ክፍያ የማስከፈልን የመሳሰሉ ጉዳዮች አቶ ዮሐንስ መሻሻል አለባቸው ከሚሏቸው መካከል ናቸው።
ለትይዩው ገበያ ህልውናም ሆነ መፋፋት ዋነኛው ምክንያት በኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ ሚዛን መካከል ያለው መዛነፍ በመሆኑ ብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ላይ ያደረገው ለውጥ መሠረታዊ ልዩነት ለማምጣቱ አጠያያቂ ነው። የእርምጃው አንድ አመክንዮ የብር የመግዛት አቅም ሲዳከም የወጪ ንግድ ይጠናከራል፤ ሀገሪቱ የምትሸምተው በአንጻሩ ይቀንሳል የሚል ነው።
በውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጡ ምክንያት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት “የውጪ ንግድ በዚህ ዓመት ቢያንስ በ100 ፐርሰንት ያድጋል” ብለው ይጠብቃሉ። አቶ ዘሪሁን ግን ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የውጪ ሀገራት የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለውን የምንዛሪ ተመን ባለፉት አስር ገደማ ወራት ከ130 በመቶ በላይ ያዳከመው እርምጃ “ምንም ዐይነት ዝግጁነት” በሌለበት ገቢራዊ የሆነ እንደሆነ ይተቻሉ።
ብርን በኃይል ያዳከመው ውሳኔ “ምንም ዐይነት የኢኮኖሚ አወቃቀር ለውጥ ባልነበረበት” ሥራ ላይ ሲውል ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “ዱብ ዕዳ” እንደሆነበት ተናግረዋል። እርምጃው “የብርን የመግዛት አቅም የበለጠ እያደቀቀው ይመጣና ኢ-መደበኛው የበለጠ እንዲበረታታ ያደርገዋል። ወይም ኢ-መደበኛው ላይ ሰዎች የበለጠ እንዲሳተፉ ያደርጋቸዋል” ሲሉ አቶ ዘሪሁን አስረድተዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያው “መንግሥት መጀመሪያውኑ እንዲህ ዓይነት የብርን የመግዛት አቅም የሚያዳክም እርምጃ ሲወስድ ጥንቃቄ አላደረገም” ሲሉ ተችተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ሐዋላን ለመቅረጥ የተነሱት ኢትዮጵያ በውጪ ሃገራት ከሚኖሩ ዜጎች ጠቀም ያለ ገንዘብ ለማግኘት በምትሻበት ወቅት ነው። ከመንግሥት በተጨማሪ በገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ የተሠማሩ ባንኮች፣ ኢትዮ-ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ድርጅቶች እንዲሁም ፈቃድ የተሰጣቸው የሐዋላ ድርጅቶች ዲያስፖራው ገንዘብ ሲልክ ከኢ-መደበኛው ይልቅ ሕጋዊውን ሥርዓት እንዲከተል ጉርሻ መስጠትን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎች ገቢራዊ በማድረግ ላይ ናቸው።
የገንዘብ አስተላላፊ ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ ለሚላክ ሐዋላ የሚያስከፍሉት ከሌሎች አኅጉሮች አኳያ “በጣም ውድ” ነው። የዓለም አቀፍ ልማት ባለሙያው አቶ ዮሐንስ “በዚያ ላይ ታክስ ሲጨመርበት የበለጠ ውድ ይሆናል” የሚል ሥጋት አላቸው። ይህ ላኪዎችን ወደ ኢ-መደበኛው ገበያ እንደሚገፋ ያስረዱት አቶ ዮሐንስ “በሕገ-ወጥ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎችም ይነሳሉ። ዕድል ነው የተፈጠረላቸው። ያለ ታክስ የሚልኩበት ዕድል ካለ 3.5 በመቶ ቀላል አይደለም። ለፍተው ያገኙት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ማንም ሰው ገንዘቡን መላኪያ ርካሽ መንገድ ነው የሚፈልገው” ሲሉ “ትልቅ ተጽዕኖ” እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በሚላከው ሐዋላ ኢ-መደበኛው የገንዘብ ዝውውር “የበላይነት ይዞ የሚገኝ ነው” የሚል ዕምነት ያላቸው አቶ ዘሪሁን የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሕግ ጸድቆ ሥራ ላይ ቢውል ተጽዕኖ የሚያርፈው “በጥቂቶች” ላይ እንደሚሆን ይናገራሉ። ይሁንና 3.5 በመቶ የሐዋላ ታክስ፤ በአገልግሎት ክፍያ እና የኢ-መደበኛው ከፍ ያለ የምንዛሪ ተመን ላይ ሲታከል ላኪዎችን ከመደበኛው ሥርዓት እንደሚያሸሽ ይስማማሉ።
“የኢትዮጵያ መንግሥትም የፖለቲካ ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ ያደረጋቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንዲያውም የበለጠ ኢ-መደበኛውን የገበያ ሥርዓት የሚያበረታታ ሆኖ ትመለከተዋለህ” የሚሉት አቶ ዘሪሁን እንዲያም ሆኖ “ሀገር ውስጥ ሐዋላ መግባቱን አያቆምም። የሚገባበት መንገድ ግን አሁንም ኢ-መደበኛው ነው የሚሆነው” ሲሉ ይናገራሉ።
“አብዛኛው ሐዋላ የሚሔደው ለመሠረታዊ ፍጆታ ነው። ከሰሀራ በርሐ በታች ወደሚገኙ ሃገራት በአንድ ጊዜ የሚላከው ሐዋላ ወደ 200 ዶላር ነው” የሚሉት አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው ገንዘቡ መድሐኒት፣ ልብስ እና ምግብ የመሳሰሉንት ለመግዛት የሚውል፤ ቤተሰብ የሚደገፍበት እንደሆነ ተናግረዋል። ሐዋላ ብርቱ ኢኮኖሚያዊ ጫና ያስከተለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተቀሰቀሰበት ወቅት ላኪ “ተቸግሮም ቢሆን ቀነሰ እንጂ አላቆመም። ምክንያቱም ቤተሰቡ ይጎዳል። ስለዚህ ብሩ መሔዱ አይቀርም” የሚሉት አቶ ዮሐንስ መንገዱ ግን ከሕጋዊው ሥርዓት የተለየ እንደሚሆን ከአቶ ዘሪሁን የተስማማ ሐሳብ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም በበርካታ ሃገራት ላይ ታሪፍ ጥለዋል። መንግሥታቸው የሚሰጠውን ርዳታ ቀንሰዋል። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID)ን አወቃቀር እና አሠራር ቀይረዋል። እነዚህ እርምጃዎች በዓለም ዙሪያ ድሕነትን ሊያባብሱ እንደሚችሉ እንደ አቶ ዮሐንስ ያሉ የዓለም አቀፍ ልማት ባለሙያዎች ይሠጋሉ።
የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሐዋላ ታክስ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሕገ-ወጥ የሚባለውን ስደት ለመቀነስ ከያዘው አጀንዳ የማይጣጣም፤ለአሜሪካም የማይጠቅም እንደሆነ አቶ ዮሐንስ ይተቻሉ። ውሳኔው ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር ምዕራባውያን ሃገራት የዘረጓቸውን አሠራሮች የሚያዳክም ጭምር ነው።
ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ የሚደረጉ ጥረቶች ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ አቶ ዮሐንስ ተስፋ አላቸው። ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ ግፊት ከሚያደርጉ መካከል የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ይገኙበታል። የሜክሲኮ ፕሬዝደንት በይፋ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን የሀገራቸው ምክር ቤት አባላት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በማምራት የሕግ ረቂቁ እንዳይጸድቅ ግፊት የማድረግ ዕቅድ አላቸው። አቶ ዘሪሁን ግን እነዚህ ጥረቶች የሚሳኩ አይመስላቸውም።
አርታዒ ሸዋዬ ለገሠ