የዩክሬይን የድሮን ጥቃት፡ ቢያንስ13 የሩስያ ጄቶች ወድመዋል
ሰኞ፣ ግንቦት 25 2017ማስታወቂያ
ዩክሬን በሩሲያ ቦምብ ጣይ ጀቶች ላይ ጥቃት ፈፀመች። ትናንት እሑድ የዩክሬን ደህንነት አገልግሎት አራት የሩስያ ወታደራዊ አየር ማረፊያዎችን በተመሳሳይ ጊዜ ለማጥቃት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መጠቀሙን የፈረንሳዩ የዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። አንድ የዩክሬን የፀጥታ እና የመከላከያ ምክር ቤት አባልን ጠቅሶ የፈረንሳዩ የዜና አገልግሎት እንደዘገበዉ ትናንት እሑድ የዩክሬይን ድሮኖች «ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች» በፈፀሙት ጥቃት በትንሹ 13 የሩሲያ ተዋጊ ጀቶች ወድመዋል። በዚሁ ጥቃት ሌሎች በርካታ አዉሮፕላኖች መጎዳታቸዉን እና በአጠቃላይ ዩክሬን ከ 40 በላይ የሩሲያ አውሮፕላኖችን ማዉደሟን ባለሥልጣኑ አክለዋል። ሩስያ ዩክሪን ላይ ጥቃት በምትፈፅምባቸዉ ቦንብ ጣይ ጀቶች ላይ ጥቃት የፈፀሙት የዩክሬይን ድሮኖች፤ ከዩክሬን ድንበር 4,000 ኪሎ ሜትር ዘልቀዉ ሩስያ ክልል ገብተዉ እንደሆነ ተዘግቧል። ይህ ዩክሬይን ሩስያ ላይ የሰነዘረችዉ ከፍተኛ ጥቃት የተሰማዉ፤ ሁለቱ ሃገራት ቱርክ ላይ ዛሬ አዲስ የሰላም ድርድር ለማድረግ ዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት መሆኑ ነዉ።