የዩናይትድስቴትስ የፌዴራል ፍርድ ቤት ውሳኔ እና የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 15 2017የአሜሪካ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ ትናንት በዋለው ችሎት፣ የአሜሪካ ድምፅ እና ሌሎች የዓለምአቀፍ ሚዲያ ተቋማት ከእገዳው በፊት ወደነበሩበት ቁመና እንዲመለሱ አዘዙ። በዚህም መሰረት ጉዳዩ በይግባኝ መታየት ቢቀጥልም እንኳን የመጨረሻ እልባት እስከሚያገኝድረስ አስተዳደራዊ ዕረፍት የተሰጣቸው ቋሚና የኮንትራት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ተወስኗል። የተቋሙ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች ውሳኔውን በደስታ ተቀብለውታል። ያም ሆኖ የትራምፕ አስተዳደር ይግባኝ ማለቱ የሚጠበቅ ስለሆነ እሰጣገባው በዚህ የሚያበቃ እንደማይሆን ነው የተገለጸው።
የአሜሪካ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ በትላንትናው እለት በዋለው ችሎት፣ የአሜሪካ ድምፅ እና ሌሎች የዓለምአቀፍ ሚዲያ ተቋማት ከእገዳው በፊት ወደነበሩበት ቁመና እንዲመለሱ አዘዙ። በዚህም መሰረት ጉዳዩ በይግባኝ መታየት ቢቀጥልም እንኳን የመጨረሻ እልባት እስከሚያገኝድረስ አስተዳደራዊ ዕረፍት የተሰጣቸው ቋሚና የኮንትራት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ተወስኗል። የተቋሙ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች ውሳኔውን በደስታ ተቀብለውታል። ያም ሆኖ የትራምፕ አስተዳደር ይግባኝ ማለቱ የሚጠበቅ ስለሆነ እሰጣገባው በዚህ የሚያበቃ እንደማይሆን ነው የተገለጸው።
የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮን አካቶ የያዘውን የአሜሪካ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ተቋም ሰራተኞች ከስራ መታገድና፣ በስሩ ያሉት የመገናኛ ብዙሃን ድምጽ መዘጋቱን ተከትሎ ነው የተቋሙ ሰራተኞች የትራምፕ አስተዳደርን የከሰሱት ። ይሄው ክስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተለያያ የሃገሪቱ ተቋማትና ህጎች ላይ ከወሰዷቸው እርምጃወች ጋ ተያይዘው ከሁሉም አቅጣጫ ወጥረው ከያዟቸው የፍርድ ቤት እሰጣ ገባወች ውስጥ አንዱ ነው። እናም በትላንትናው እለት በዋለው ችሎት ጉዳዩ የሚያየው የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ላይ እግድን ጥሎ ተቋሙ ስራውን ካቆመነት እንዲቀጥል፣ የተጣለበትንም ሃላፊነት እንዲወጣ፣ የተቋሙ ጋዜጠኞችም የኤዲቶርያል ነጻነታቸው ከጣልቃ ገብነት የጸዳ እንዲሆን ወስኗል። ይሄንኑ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ጭብጥ የሕግ ባለሞያና ጠበቃ ቃለአብ ካሣዬ እንዲህ ይገልጹታል።
የዶናልድ ትራምፕን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮን ከስርጭት አስወጣ
ይህንኑ ውሳኔ የተቋሙ ሰራተኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሞያ ማህበሩ አባላት እንደ ትልቅ ድል ቆጥረው በታላቅ ደስታ ነው የተቀበሉት ። በዋና ከሳሽነት ስማቸው የተጠቀሰው የአሜሪካ ድምጽ የኋይት ሃውስ ቢሮ ሃላፊ ፓትሲ ዊዳኩስዋራ በዚሁ የፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ትግላቸው በዚህ እንደማያበቃ ጠቁመዋል።
ከሶስት አስርተ አመታት በላይ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ አገልግሎትና የአፍሪካ ዴስክ ሃላፊነት የሰሩት አቶ ንጉሴ መንገሻም መጀመሪያውኑ ተቋሙ መዘጋቱ አፍሪካን ጨምሮ በመላው አለም የሚገኙ አድማጮቹን፣ ብሎም ራሱን የአሜሪካንን መንግስት ጭምር የጎዳ እንደሆነ ጠቁመው፣ በውሳኔው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የተቋቋመው በኮንግረስ ውሳኔ መሆኑን ያወሱት አቶ ንጉሴ፣ጣብያው ያለው አዎንታዊ ሚና በሁሉም የመንግስት ተቋማት ዘንድ የታወቀ በመሆኑ በጀት እንኳን በሁለቱም ፓርቲወች የጋራ ስምምነት እያገኘ የቆየ መሆኑን አስታውሰዋል። ከዚህ ቀደም እንደነበረ ማንኛውም የአሜሪካ አስተዳደር ለትራምፕ አስተዳደርም የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ያስታወሱት የቀድሞው የጣብያው ሃላፊ አቶ ንጉሴ መንገሻ መንግስት የአሜሪካ ድምጽን የዘጋበት ሁኔታና ምክንያት አሁንም ድረስ ግልጽ እንዳልሆነላቸውና በምንም መልኩ ቢታይ ተጨባጭነት የሌለው መሆኑን ነው የገለጹት ።
የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጡት ዳኛው ሮይስ ላምበርት በውሳኔ ትዕዛቸው ላይ መንግስት ጣብያውን በዘጋበትና ሰራተኞቹን ባገደበት ውሳኔው በርካታ የፌደራል ህጎችን የጣሰ መሆኑን ገልጸው፣ በጋዜጠኞቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ ግብታዊና በምንም አይነት ጥናት ላይ ያልተመሰረተ መሆኑን አውስቷል። በዚህም መሰረት የፍርድ ቤት ሂደቱ ቢቀጥልም ሰራተኞቹ የትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ተፈጻሚ ከሆነባት እና ቢሯቸው ድርሽ እንዳይሉ ከታዘዙባት እለት በፊት ወደነበረው መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ያስገድዳል።
በሌሎች ውሳኔወቻቸውም በተለያዩ ፍ/ቤቶች ክሶች ላይ የሆኑት ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና አስተዳደራቸው ሁሉንም ክሶች ይግባኝ እያለ እስከ ሃገሪቷ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድረስ ይዞ የመጓዝ ጋህሪው የተለመደ ሆኗል። ከዛም አልፎ በተለይ ከስደተኞች ጉዳይ ጋ በተያያዙ ውሳኔወች፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዛቶችን ያለመፈጸምና የፍትህ ስራዓቱን ሂደቶች የመገዳደር ባህሪያት እንዳሉት የገለጹት የህግ ባለሞያና ጠበቃ ቃለአብ ካሳዬ በዚሁ የአሜሪካ ድምጽ ጉዳይ ላይ የተሰጠውን ውሳኔ ያለማክበር ሁኔታ ቢፈጠር ፍ/ቤቱ የተከሰሱትን መስርያ ቢት ሃላፊወች በግል የመቅጣትን አማራችሊጠቀም እንደሚችል ጠቁመዋል።
አበበ ፈለቀ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ