የዩናይትድ ስቴትስ፣ የዩክሬንና የአዉሮጳ መሪዎች የሠላም ውይይት
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13 2017የዩናይትድ ስቴትስ፣ የዩክሬንና የአዉሮጳ ሐገራት መሪዎች የሩሲያ እና የዩክሬይን ጦርነት አስቁሞ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና ለዩክሬይን ደህንነት ዋስትና መስጠትን በተመለከተ ትናንት ኋይት ሀውስ ዉስጥ ተወያይተዋል።ጉባኤተኞቹ በሁለቱ ሐገራት መሪወች መሐከል ቀጥታ ውይይት እንዲደረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል። የጀርመኑን መራሔ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስን ጨምሮ የአውሮፓ መሪወች ከውይይቱ በፊት የተኩስ ማቆም ስምምነት ሊደረግ ይገባል የሚል አቋም አንፀባርቀዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ዘለንስኪ እና አውሮፓ በዋሽንግተን የሰላም ውይይት አደረጉ። በዚሁ በኋይት ሃውስ ውስጥ በተደረገው ውይይት የራሽያን እና የዩክሬይን ጦርነት አስቁሞ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እና ለዩክሬይን ደህንነት ዋስትና መስጠትን የተመለከቱ ውይይቶች ተደርገዋል። በውይይቱ ማጠቃለያም በሁለቱ ሃገራት መሪወች መሃከል የሁለትዮሽ ውይይት እንዲደረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል። የጀርመኑን ቻንስለር ፍሬድሪክ መርስን ጨምሮ የአውሮፓ መሪወች ከውይይቱ በፊት የተኩስ ማቆም ስምምነት ሊደረግ ይገባል የሚል አቋም ይዘዋል፣
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በአውሮፓ መሪዎች ታጅበው ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የተገናኙበት፣ ከወትሮው የተለየ ትኩረት የተሰጠው ውይይት ነው። ባለፈው አርብ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋ በአላስካ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ የተደረገው የትላንትናው የኋይት ሃውስ ውይይት የሰለሙን ተስፋ ወደ ተጨበጠ እርምጃ ለማሻገር ያለመ እንደሆነ ተነግሮለታል። ሁሉም ተስፋ ያደረጉበት ቢሆንም የተኩስ አቁም ስምምነትን፣ ዘላቂ ሰላም ማስፈንን፣ የደህንነት ዋስትናንና የዩክራይንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በተመለከተ ራሽያ፣ ዩክሬይንና አሜሪካ ያላቸው አቋም ማሰናሰል፣ ብሎም ከራሽያ ጋ ተወያይቶ ሰላም ማምጣት ይቻል አይቻል እንደሆነ ማንም እርግጠኛ አልነበረም።
ውይይቱ፣ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪም ሆነ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከስድስት ወራት በፊት ኋይት ሃውስ ውስጥ ከነበራቸው በእሰጣ ገባ የተሞላ ውይይት በተለየ በምስጋና እና በመልካም ቃላት የታጀበ ጅማሮ ነበረው።
ከዘለንስኪ ጋር ያሉት የአውሮፓ መሪዎች፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኤማኑዌል ማክሮን፣ የጀርመን ቻንሰለር ፍሪድሪክ መርስ፣ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እና የፊንላንድ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ስቱብ አንድ ላይ ታድመው ከዩክሬይን ጋር ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል። የዩክሬይን ጥቅም እና ደህንነት ይከበር ዘንድም አውሮፓ እና አሜሪካ የማያወላዳ ድጋፍ ለመስጠት ቃል እንዲገቡ አጽኖት ሰጥተዋል።
የውይይቱ ዋና ግብም ዘለንስኪና ፑቲንበቀጥታ የሚገናኙበት የሁለትዮሽ ውይይት መድረክ ማመቻቸት፣ ያም በተሳካ ሁኔታ ከተካሄደ፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የታከሉበት የሶስትዮሽ ውይይት የማድረግ ራዕይን የሰነቀ ነው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ የመጀመርያው ውይይት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመው፣ ይሄው ጥረት ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ሳይሆን ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ እንደሆነ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ይህንኑ የውይይት እቅድ በቀና መንገድ የተቀበሉት ቢሆንም፣ ውይይቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መካሄድ እንዳለበት አሳስበዋል። የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ መርስን ቸምሮ የአውሮፓ ሃገራት መሪዎች መጀመርያ የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይደረግ የሚካሄድ ውይይት ዘላቂ ሰላም ያመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።
ዘለንስኪ የዩክሬይንን መከላከያ የሚያጠናክር፣ በአውሮፓውያን የሚደገፍ ከፍተኛ የመሳርያ ግዢ ከአሜሪካ የሚካሄድበትን ሃሳብ አርበዋል።
በቀጣይነትም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የሚመሩት የአሜሪካና የአውሮፓ ግብረ ሃይል ለዩክሬይን ሊሰጥ የሚችለውን የደህንነት ዋስትና እቅድና አማራጮችን ለማቅረብ ስራ ይጀምራል። ከዚህ በተጨማሪ የሰላም ጥረቱና ውይይቶችም ጎን ለጎን ይቀጥላሉ። ዘለንስኪና ፑቲን በቀጥታ እንዲገናኙ የታሰበበት ውይይትን ቀንና ቦታ የመወሰን ስራም እንደሚደረግ ይጠበቃል።
የትላንትናው ውይይቱ የተጨበጠ ውጤትን ባያመጣም በተስፋ ተሞልቶ አብቅቷል። የቀጣዮቹ ውይይቶች ውጤት ይስመር አይስመር የሚወሰነው ደግሞ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ወይም በዩክሬይን ጥረት ብቻ ሳይሆን በራሽያ እውነተኛ ፍላጎትና ተግባራዊ እርምጃ ላይ ጭምር ነው።
አበበ ፈለቀ
ነጋሽ መሐመድ
ልደት አበበ