የየካቲት 24 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ የካቲት 24 2017በጃፓን ቶኪዮ ማራቶን እንደተጠበቀው ሁሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ፉክክር አሸንፈዋል ። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ አምስተኛ ዙር የእግር ኳስ ግጥሚያ ዛሬ ማታም ይኖራል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽ እና ተከታዩ ባዬር ሌቨርኩሰን ተጋጣሚዎቻቸውን ሲያሸንፉ፤ ላይፕትሲሽ ሽንፈት ገጥሞታል ። በደርሶ መልስ ግጥሚያ ሁለት እኩል የተለያዩት ሉሲዎቹ በመለያ ምት አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ሁለተኛ ዙር አልፈዋል ። በፊፋ የሙስና ቅሌት ከዓመታት በፊት ክስ የተመሰረተባቸው ሚሼል ፕላቲኒ እና ሴፕ ብላተር ዛሬ ዳግም ፍርድ ቤት ቀርበዋል ።
አትሌቲክስ
ፈጣን በነበረው የጃፓን ቶኪዮ ማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በሴትም በወንድም ድል ተቀዳጅተዋል ። በወንዶች ፉክክር (2:03:23) በመሮጥ አንደኛ የወጣው ኢትዮጵያዊው አትሌት ታደሠ ታከለ የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቋል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ደረሰ ገለለታ በሃያ ስምንት ሰከንዶች ብቻ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃ በማግኘት የብር ሜዳሊያ ተሸልሟል ። ኬኒያዊው አትሌት ቪንሰንት ኪፕኬሞይ (2:04:00) ሮጦ ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሙሉጌታ አሠፋ ኬንያዊው ቲቱስ ኪፕሩቶን በመከተል የአምስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ።
ብርቱ ፍክክር በተስተዋለበት የሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር፦ አንደኛ የወጣችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱቱሜ አሠፋ (2:16:31) በመሮጥ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልማለች ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሐዊ ፈይሳ (2:17:00) ኬኒያዊቷ አትሌት ሞሴቲ ዊንፍሪድን (2:16:56) በመከተል የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልማለች ። ሐዊ ከሱቱሜ በ29 ሰከንድ ከሞሴቲ ደግሞ በአራት ሰከንድ ነው የተበለጠችው ።
በዚሁ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ጎይተቶም ገብረሥላሴ እና ደጊቱ አዝመራው የ7ኛ እና 8ኛ ደረጃ አግኝተዋል ። የየካቲት 17 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የኢትዮጵያ ማራቶን ዱላ ቅብብል ሻምፒዮና
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚዘጋጀውን የኢትዮጵያ ማራቶን ዱላ ቅብብል ዘንድሮ 129ኛ የዓድዋ ድል በዓል በሚከበርበት ቀን ዋዜማ በአድዋ ከተማ አከናውኗል ። በዝግጅቱ ሥፋራ የታደመው የመቐለው ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ቀጣዩን ዘገባ ልኮልናል ።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚዘጋጀው የማራቶን ሪሌ ሻምፒዮና፥ ዘንድሮ ለ20ኛ ግዜ የተካሄደው ባለፈው ቅድሜ በዓድዋ ከተማ ነበር ። 129ኛ የዓድዋ ድል በዓል በሚከበርበት ቀን ዋዜማ በተካሄደው ውድድር የበዓሉ ድምቀት ሆኖ አልፏል ። በዚህ 20ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር ከሦስት ክልሎች ማለትም፦ ጋምቤላ፣ ሶማልያ እና ትግራይ እንዲሁም ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሸገር ሲቲ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ ቡና የተወከሉ አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከፍተኛ ፉክክር የታየበትም ነበር ።
በውድድሩ በተጠናጠል 10፣ 7 ነጥብ 1 እና 5 ኪሎ ሜትር ወንድ እና ሴት አትሌቶች እየተቀያየሩ ውድድሩ ያካሄዱ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 42 ኪሎሜትር የሚሸፍን ነበር ። በዚህ ውድድር ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቀዳሚነት ያሸነፈ ሲሆን፥ ሸገር ሲቲ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቅቀዋል ።
በዓድዋ ከተማ በነበረው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር ተገኝተን ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት አትሌት ስለሺ ሥኅን፥ ሻምፒዮናው ብርቱ ፉክክር የተደረገበት እና የዓድዋ ድል በዓልን ያደመቀ ስፖርታዊ ሁነት ነበር ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል ።
ከዚህ በተጨማሪ፦ የበርካታ ታላላቅ አትሌቶች መፍለቅያ በሆነችው ትግራይ ክልል ሻምፒዮናው መካሄዱ ለተተኪዎች መነቃቃት የሚፈጥር ነው ያሉት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ቢንያም ምሩፅ ይፍጠር በበኩላቸው፥ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረረባቸው በትግራይ የሚገኙ የአትሌቲክስ ማእከላት ለማገዝ ጥረቶች መቀጠላቸው ተናግረዋል ።
በ20ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ውድድሩ በቀዳሚነት ያጠናቀቀች ሲሆን፥ የሸገር ሲቲ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ እና የንግድ ባንክ አትሌት ዐሳየች ዐይቼው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነዋል ። የየካቲት 10 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
እግር ኳስ
ለአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ውድድር የዩጋንዳ አቻቸውን በመልሱ ግጥሚያ 2 ለ0 ያሸነፉት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ በቀጣይ ዙር ታንዛንያን ይገጥማሉ ። ሉሲዎቹ በዩጋንዳ 2 ለ0 ተሸንፈው ነበር አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የመልሱን ጨዋታ ያደረጉት ። በመልሱ ጨዋታም ቀዳሚውን ግብ አረጋሽ ካልሳ 66ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥራለች ። ተቀይራ የገባችው እፀገነት ግርማ ደግሞ መደበኛው የጨዋታ 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው ስድስተኛ ደቂቃ ላይ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ አሳርፋለች ።
የደርሶ መልስ ጨዋታው በድምሩ ሁለት እኩል በመጠናቀቁ በተሰጠው መለያ ምትም፦ ኢትዮጵያ ዩጋንዳን 5-4 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ሁለተኛ ዙር አልፋለች ። ቀጣዩ ጨዋታ በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 10 ቀን ታንዛኒያ ውስጥ ይካሄዳል ። የመልሱ ግጥሚያ ደግሞ በሳምንቱ ጥቅምት 18 ኢትዮጵያ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለታል ።
ኤፍ ኤ ካፕ ሩብ ፍጻሜ
ሰሞኑን የኤፍ ኤ ካፕ ውድድሮች የተደረጉባቸውን ኳሶች የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ከጥራት በታች ናቸው ሲሉ ተቹ ። «የአርሊንግ ኦላንድን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተጨዋቾችንም ብትመለከቱ የሚመቷቸው ኳሶች ከማእዘን በላይ ነው የሚያልፉት» ብለዋል ። እውነታውን ለበርካታ ዓመታት መናገራቸውን እንደቀጠሉበት የገለጡት ፔፕ፦ የሻምፒዮንስ ሊግ እና ፕሬሚየር ሊግ ኳሶችን ጥራት አወድሰዋል ። የኤፍ ኤ ካፕ ኳሶች ግን «ለመቆጣጠር የማይመቹ» እንደሆኑ በመግለጥ የሚቀራቸው ነገር አለ ብለዋል ። የኤፍ ኤ ካፕ አዘጋጆች ሁሉም የእግር ኳሶች በፊፋ የጥራት መስፈርት የሚቀርቡ መሆናቸውን በመግለጥ የፔፕ ጓርዲዮላን ትችት የየሰዉ ፍላጎት የተለያየ ነው በማለት አጣጥሏል ። እንዲያም ሁኖ ግን ቡድናቸው ማንቸስተር ሲቲ ፕሌይማውዝ አርጊልን 3 ለ1 አሸንፎ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል ። የየካቲት 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ከፉልሀም ጋር አንድ እኩል የተለያየው ማንቸስተር ዩናይትድ በመለያ ምት 4 ለ3 ተሸንፎ ከውድድሩ ተሰናብቷል ። ከሁለቱም ቀይ ካርድ በታየበት ግጥሚያ ብራይተን ኒውካስትልን ትናንት 2 ለ1 አሸንፎ ወደ ሩብ ፍጻሜው አልፏል ። በሌሎች ቅዳሜ በተከናወኑ ግጥሚያዎች፦ ከዎልቭስ ጋር አንድ እኩል ያጠናቀቀው በርመስ በመለያ ምት 5 ለ4 አሸንፏል ። ፕሬስተን በርንሌይን 3 ለ0 ረትቷል ። ሚልዋልን 3 ለ1 ያሸነፈው ክሪስታል ፓላስ እና ካርዲፍ ሲቲን 2 ለ0 ድል ያደረገው አስቶን ቪላ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፋቸው ካረጋገጡ ቡድኖች መካከል ናቸው ። በሩብ ፍጻሜው ፉልሀም ከክሪስታል ፓላስ፣ በርመስ ከማንቸስተር ሲቲ፣ ፕሬስተን ከአስቶን ቪላ ይጋጠማሉ ። ዛሬ ማታ ከሚኖረው የኖቲንግሀም ፎረስት እና ኢፕስዊች ታወን ግጥሚያ አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ብራይተንን ይገጥማል ። የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች በአጠቃላይ ከ26 ቀናት በኋላ ይከናወናሉ ።
ባየርን ሙይንሽን እና ቡንደስ ሊጋ
ከ125 ዓመታት በፊት የቡና መጠጫ ቤት ውስጥ የተመሰረተው ባየርን ሙይንሽን በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ታሪክ እጅግ ስኬታማው ቡድን ነው ። በ125 ዘመኑ ባየርን ሙይንሽን ሠላሳ ሦስት የቡንደስሊጋ እንዲሁም 20 የጀርመን ካፕ ዋንጫዎችን ሰብስቧል ። ስድስት የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን በማንሳትም ባዬርን ሙይንሽንን ጀርመን ውስጥ የሚስተካከለው የለም ። የአውሮጳ ዋንጫ የአሸናፊዎች አሸናፊ እንዲሁም የአውሮጳ ሊግ ዋንጫንም ከፍ አድርጓል ። ሁለት ዓለም አቀፍ ዋንጫዎችን እና ሁለት የፊፋ የቡድኖች ዓለም ዋንጫዎችንም በማሸነፍ ስሙ የሚጠቀስ ገናና ቡድን ነው ። ትንሽዬ ቡድን ሁኖ ባየርን ግዛት ውስጥ ከተመሰረተ 125ኛ ዓመቱ የተቆጠረው ይኸው ቡድን የዓለማችን ገናና ቡድን መሆን ችሏል ።
ዘንድሮም የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ ለማንሳት በአሸናፊነቱ እየገሰገሰ ነው ። ቡንደስሊጋውን በ61 ነጥብ የሚመራው ባዬርን ሙይንሽን ሽቱትጋርትን 3 ለ1 አሸንፏል ። በ53 ነጥብ ተከታዩ ባዬርን ሌቨርኩሰን ቅዳሜ ዕለት አይንትራኅት ፍራንክፉርትን በሜዳው 4 ለ1 ድል አድርጓል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ42 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ማይንትስ እና ፍራይቡርግ በ41 እና 40 ነጥብ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ተከታታይ ናቸው ። ላይፕትሲሽ በ38 ነጥብ 6ኛ ሁኖ ይከተላቸዋል፥ በሬድ ቡል አሬና ስታዲሙ ደጋፊው ፊት በማይንትስ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሳንክት ፓውሊን በሜዳው 2 ለ0 አሸንፎ ተመልሷል ። ቦሁም፣ ሆልሽታይን ኪዬል እና ሐይደንሀይም ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ።
የፊፋ የሙስና ቅሌት ክስና የቀድሞ አመራር ማስተባበያ
የዓለም ከፍተኛ የእግር ኳስ የቀድሞ አመራር ሴፕ ብላተር እና ሚሸል ፕላቲኒ ከማጭበርበር ክስ ነጻ ከተባሉ ከ2 ዓመት ከመንፈቅ በኋላ ስዊትዘርላንድ ውስጥ ዛሬ ዳግም ፍርድ ቤት ቀረቡ ። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) የቀድሞ ፕሬዚደንት ሴፕ ብላተር እና የአውሮጳ የእግር ኳስ ማኅበር (UEFA)ፕሬዚዳንት የነበረው ሚሼል ፕላቲኒ በማጭበርበር ክስ ከተመሰረተባቸው 10 ዓመታት ተቆጥሯል ።
ዛሬ ድጋሚ ፍርድ ቤት የቀረቡት የ89 ዓመቱ ሴፕ ብላተር እና የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ታዋቂ ተጫዋች የ69 ዓመቱ ሚሸል ፕላቲኒ ምንም የፈጸምነው ስህተት የለም ብለዋል ። የስዊትዘርላንድ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ነጻ ቢያሰናብታቸውም የአገሪቱ አቃቤያነ ሕግ ግን ሁለቱን የቀድሞ የእግር ኳስ ባለሥልጣናት በ2.21ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ማጭበርበር እንዲቀጡ ይፈልጋሉ ።
ሴፕ ብላተር ረዳታቸው ሁኖ ላገለገለው ሚሼል ፕላቲኒ የዛሬ 14 ዓመት 2 ሚሊዮን የስዊስ ፍራንክ በባንክ ልከዋል በሚል ነው የተከሰሱት ። ፊፋን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር እስከ 2015 ድረስ ለ17 ዓመታት በፕሬዚደንትነት የመሩት ሴፕ ብላተር፦ ክፍያው ተገቢ ነው ብለዋል ። ሚሼል ፕላቲኒ ከ1998 እስከ 2002 ድረስ ላበረከተው የማማከር አገልግሎቱ በየዓመቱ 300.000 የስዊስ ፍራንክ የተከፈለው እንጂ ማጭበርበር አይደለምም ሲሉ ሞግተዋል ። አቃቤያነ ሕግ ግን ሁለቱ ግለሰቦች በ20 ወራት እስራት እና ለሁለት ዓመታት እገዳ እንዲቀጡ እፈልጋለሁ ብለዋል ። ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት የዛሬ ሦስት ሳምንት ቀጠሮ ሰጥቷል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ