መቅዲሾ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ነገ መቅዲሾ ይሄዳሉ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ነገ መቅዲሾ ይሄዳሉ ሲል የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምንጮችን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። እንደ ዘገባው ዐቢይ ነገ ወደ መቅዲሾ የሚሄዱት ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ነው። በቆይታቸውም በመቅዲሾ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድ ጋር ይነጋገራሉ። ጉብኝቱም ከዚህ ቀደም ሁለቱ ወገኖች የተፈራረሙትን የአንካራ ስምምነት ከፍጻሜ የማድረስና ተግባራዊም የማድረግ ሰፊ ጥረት አካል መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት ሶማሊያ ግዛቴ ናት ከምትላት ከሶማሌላንድ የባህር በር ለማግኘት በተፈራረመችው የመግባባያ ሰነድ ምክንያት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ውጥረት ተፈጥሮ ነበር።
ባህርዳር 14 ሰዎች በመኪና አደጋ ሞቱ
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 14 ከፍ ማለቱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ትምህርትና ሰልጠና ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ይበልጣል መርሻ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ እንደገለፁት ተሽከርካሪው ከበየዳ ወደ ደባርቅ ሠዎችንና እህል ጭኖ ሲጓዝ ትናንት ከረፋዱ 3፡30 አካባቢ በደባርቅ ወረዳ ልዩ ሥሙ “አበርጊና” በተባለ ቦታ ላይ ሲደርስ ተገልብጦ 12 ሰዎች ወዲያውኑ ሞተዋል።ሆኖም ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል 2 ሰዎች ዛሬ በመሞታቸው የሟቾቹ ቁጥር 14 ደርሷል። ሌሎች በርካቶችም ቆስለዋል። ተጨማሪ ምርመራዎች እየተደረጉ ቢሆንም ለመኪናው መገልበጥ ምክንያት ነው ያሉትን ኃላፊው ኢንስፔክተር ይበልጣል ዘርዝረዋል።
«የመኪና አደጋው ምንድነው መጀመሪያ የሚበቃውን ያክል ጭኗል።በዚያ ላይ ከ50 በላይ ሰው ሲጨመርበት ሌላ ችግር ሆነ ሲቀጥል ደግሞ ልጁ(ሾፌሩ) ለአካባቢው እንግዳ ነው ።ሾፌሩ ከወደ ጎጃም እንደመጣ ነው ያለኝ መረጃ።ስለዚህ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ነገሮቹ ተደራረቡና አደጋው እንዲከሰት ሆኗል። አስራ ሁለት የሞቱ አሉ።39 ቁስለኛ ፤አብዛኛው ከባድ ነው አሁን ትናንት ከባድ ጉዳት ከነበራቸው ሁለቱ ሞተዋል።የሟቾቹ ቁችር ከ12 ወደ 14 ጨምሯል። »
ህብረተሰቡ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመጠቀም ይልቅ ዋጋው ዝቅ ባለና ብዙ ሰዎች በሚያሳፍር የጭነት መኪና የመሄድ ልምድ እያዳበረ በመሆኑ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም እንደሚገባ ኢንስፔክተር ይበልጣል ማሳሰባቸውን ዓለምነው መኮንን ከባህር ዳር ዘግቧል።
መቅዲሾ ሶማሊያ ከ70 በላይ የአሸባብ አባላትን መግደሏን አስታወቀች
ከ70 በላይ የሶማሊያውን የአሸባብ ቡድን አባላት መግደሏን ሶማሊያ አስታወቀች። የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ መሠረት ታጣቂዎቹ የተገደሉት በብሔራዊው ጦርና በአካባቢ ሚሊሽያዎች የጋራ ዘመቻ ነው።በደቡብ ማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ ሂርሸበሌ በተባለው አካባቢ በተካሄደው በዚህ ዘመቻ ከቡድኑ ሚሊሽያዎች ግድያ በተጨማሪ በርካታ የጦር መሳሪያዎች ሲያዙ፣ ታጣቂዎቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎች ደግሞ እንዲወድሙ ተደርጓልም ተብሏል። የሟቾቹን ቁጥር በነጻ ምንጭ ማረጋገጥ እንዳልቻለ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ውጊያው በተካሄደበት ስፍራ በርካታ አስከሬኖች አይተናል ብለዋል። አንዳንድ ምንጮች እንዳሉት ዘመቻው አልሸባብ ባለፉት ጥቂት ቀናት ለፈጸመው ጥቃት አጸፋ ነው። አሸባብ የቦምብን ጨምሮ ሌሎች ጥቃቶችን በዋና ከተማዋ መቅዲሾና በሌሎችም ግዛቶች አካሂዷል። ምንም እንኳን ቡድኑ ከዋና ከተማይቱ የተባረረ ቢሆንም በሶማሊያ የገጠር አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ ነው። የሶማሊያ ጦር በአሁኑ ጊዜ የከፈተው ዘመቻ በየአካባቢው ሚሊሽያዎች በአፍሪቃ ኅብረት ኃይልና በዩናይትድ ስቴትስ የአየር ጥቃት የታገዘ ነው።
ፖርት ሱዳን 46 ሰዎች በአውሮፕላን አደጋ ሞቱ
ሱዳን ውስጥ 46 ሰዎች በአውሮፕላን አደጋ ሞቱ። አደጋው የደረሰው አንድ የሱዳን አንቶኖቭ ወታደራዊ የማጓጓዣ አውሮፕላን ትናንት ለሊት ኦምዱርማን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ትልቁ ወታደራዊ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ፣ዋዲ ሴይድ አቅራቢያ በመከስከሱ መሆኑን የአካባቢው መንግሥት አስታውቋል። አውሮፕላኑ የወደቀበት ቦታ ከካርቱም ወጣ ብሎ የሚገኝ የመኖሪያ አካባቢ ነው። አውሮፕላኑ ገና አየር ማረፊያውን ለቆ እንደተነሳ በደረሰው በዚህ አደጋ የሞቱት ወታደሮችና ሰላማዊ ሰዎች ናቸው። 10 ሰዎችም ቆስለዋል። የዓይን ምስክሮች በወቅቱ ከባድ ፍንዳታ መስማታቸውንና በአካባቢው የነበሩ ቤቶች ላይ ጉዳት ሲደርስ ማየታቸውን ተናግረዋል። አንድ ወታደራዊ ምንጭ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በስተሰሜን ምዕራብ የደረሰው የዚህ አደጋ መንስኤ የቴክኒክ ችግር ሳይሆን አይቀርም። አደጋው ከመድረሱ አንድ ቀን አስቀድሞ የሱዳንን ጦር የሚወጋው ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ፣ኢልዩሽን የተባለ ሩስያ ሰራሽ አውሮፕላን በደቡብ ዳርፉር ዋና ከተማ ኒያላ ውስጥ ተኩሶ መጣሉን ተናግሮ ነበር።ቡድኑ እንዳለው አውሮፕላኑ በውስጡ ከነበሩት ሠራተኞች ጋር ወድሟል።
ዶሀ የሩስያና የየዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች ነገ ኢስታንቡል ውስጥ ሊወያዩ ነው
የሩስያና የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች ከሶስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ ኢስታንቡል ቱርክ ውስጥ እንደሚነጋገሩ ሩስያ አስታወቀች። የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ዛሬ እንደተናገሩት ነገ ኢስታንቡል ውስጥ የሚካሄደው ውይይት በተለይ ከኤምባሲዎቻቸው ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች መፍትሄ በመፈለግ ላይ ያተኮረ ነው። ሚኒስትሩ ዛሬ ኳታር ውስጥ በሰጡት መግለጫ ፣ውጤቱም ሁለቱ ሀገራት በፍጥነትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ወደፊት እየተጓዙ መሆኑን የሚያሳይ ይሆናል ብለዋል። በባይደን አስተዳደር ሁለቱ ሀገራት አንዳቸው የሌላኛቸውን የኤምባሲ ሠራተኞች አባረው ነበር።
ላቭሮቭና የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሮብዮ ከአንድ ሳምንት በፊት ሳውዲ አረብያ ዋና ከተማ ሪያድ ውስጥ በተገናኙበት ወቅት ኪቭ በሌለችበት በዩክሬኑ ጦርነት ላይ ለመነጋገር መስማማታቸው ይታወሳል። ባለፈው ወር ስልጣን ከያዙ ወዲህ የዩናይትድ ስቴትስን የውጭ ፖሊሲ የቀየሩት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩስያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በመቅረብ ከሶስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሞስኮ ጋር በከፍተኛ ልዑካን ደረጃ ንግግር ለማስጀመር መቻላቸው የዓለም ትኩረት ስቧል።
ናይሮቢ የሩዋንዳ ማሳሰቢያ
በሩዋንዳ ላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ መጣል፣ ኪንሻሳ ከአማጺው M23 ጋር የሰላም ንግግር እንድታካሂድ የሚያበረታታ አይደለም ስትል ሩዋንዳ አሳሰበች። ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ሐሙስ ማዕቀብ የጣለችባቸው የሩዋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴታ ጀምስ ካባሬቤ ሩዋንዳ ላይ ማዕቀብ ሲጣል የኮንጎው ፕሬዝዳንት ሩዋንዳ ዒላማ ውስጥ መግባቷን ሲያዩ በማናቸውም ድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይሆኑም ብለዋል። ካባሬቤ በዚህ በትናንቱ ንግግራቸው የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት ስለጣለባቸው ማዕቀብ ግን ያሉት ነገር የለም። የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት የፖል ካጋሜ የቅርብ አጋር ካባሬቤ ከ1990ዎቹ አንስቶ በኮንጎ የሩዋንዳ ድጋፍ እንዲጠናከር ቁልፍ ሚና በመጫወት ስማቸው ይነሳል። ብሪታንያ የሩዋንዳው ግጭት እስኪቆምና የሩዋንዳ ወታደሮችም ከኮንጎ ግዛት ሙሉ በሙሉ እስኪወጡ ድረስ ለሩዋንዳ ከምትሰጠው ድጋፍ የተወሰነውን እንደምታቆምና ዲፕሎማሲያዊ ማዕቀብ እንደምትጥልም ትናንት አስታውቃለች። የአውሮጳ ኅብረት በበኩሉ ኪጋሊ ከአማጽያን ጋር ባላት ግንኙነት ምክንያት ከሩዋንዳ ጋር ያደረገውን የማዕድኖች ስልታዊ ስምምነት እንደገና እፈትሻለሁ ብሏል። ሩዋንዳ ግን ለአማጺው ቡድን M23 የጦር መሣሪያና ወታደሮችን ትስጣለች መባሏን ታስባብላለች። በሩዋንዳ ይደገፋሉ የሚባሉት የM23 አማጽያን ባለፉት ወራት ምሥራቅ ኮንጎ የሚገኙ ሁለት ትላልቅ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር