የየካቲት 17 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ የካቲት 17 2017ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የማራቶን ውድድሮች በወንድም በሴትም ፉክክር ድል ተቀዳጅተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል በግስጋሴው ቀጥሎ በ11 ነጥብ ልዩነት ተከታዩ አርሰናልን ርቋል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው አርሰናል በገዛ ሜዳው በዌስትሐም መሸነፉ በዋንጫ ተፎካካሪነቱ ላይ ጋሬጣ ደቅኗል ። ቀጣይ ጨዋታው ሦስተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ኖቲግንሀም ፎረስት ሜዳ ነው ። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽ እና ተከታዩ ባዬር ሌቨርኩሰን ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል ። ላይፕትሲሽ ከታችኛው ዲቪዚዮን ባደገው እና ወራጅ ቀጣናው ግርጌ ላይ በሚገኘው ሐይደንሀይም ተፈትኖ አቻ ወጥቷል ። በመጀመሪያው ግጥሚያ በውድድሩ ማብቂያ ላይ በዩጋንዳ አቻቸው የተሸነፉት ሉሲዎቹ በመልሱ ግጥሚያ ረቡዕ ይፋለማሉ ።
አትሌቲክስ
በጃፓን ኦሳካ፣ ደቡብ ኮሪያ ዴጉ እና በስፔን የሴቪያ ማራቶን ሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተቀዳጅተዋል ። በተለይ በጃፓን ኦሳካ የማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ በበላይነት አጠናቅቀዋል ።
በሴቶች የማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት ብቃታቸውን አስመስክረዋል ። አትሌት ዋጋነሽ መካሻ (2:26:33) በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች ። አትሌት አፈራ ጎድፋይ እና ኩባ ዓለሙ በዋጋነሽ በ7 እና 10 ሰከንዶች ተቀድመው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።
በወንዶች ተመሳሳይ ሩጫ ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት ይሁንልኝ አዳነ የራሱ ምርጥ ሰዓትን በ(2:05:37)በማስመዝገብ የቦታውን ሰዓት ጭምር አሻሽሎ ነው በአንደኝነት ያጠናቀቀው ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አብዲሳ ቶላ የጃፓኑ ሯጭ ርዮታ ኮንዶን በ13 ሰከንዶች ተከትሎ ሦስተኛ ደረጃ (2:05:52)አግኝቷል ። አትሌት ጌትነት ሞላም ሌላኛው ጃፓናዊ ክዮሃይ ሆሶያን ተከትሎ በአምስተኛነት አጠናቅቋል ። የየካቲት 10 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ትናንት በተከናወነው የኮርያ -ዴጉ ዓለምአቀፍ የማራቶን ሩጫ ፉክክርም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸንፈዋል ። በሴቶች ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መሠረት በለጠ (2:24:08) በመሮጥ አንደኛነት አጠናቃለች ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ትእግስት ግርማ ከባህሬኗ ሯጭ ሩት ጄቤት ለጥቂት በ2 ሰከንዶች ተበልጣ ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ሩት ጄቤት ውድድሯን ያጠናቀቀችው (2:25:43) በመሮጥ ነው ።
በወንዶች ተመሳሳይ የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አዲሱ ጎበና (2:05:22)እና ደጀኔ መገርሣ (2:05:59)ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። በዚህ ፉክክር፦ ታንዛኒያዊው ጋብርኤል ጌአይ (2:05:20)በመሮጥ አንደኛ ወጥቷል ።
በስፔን የሴቪያ ማራቶንም ኢትዮጵያውያን ድል ተቀዳጅተዋል ። አትሌት ሰለሞን ባረጋ በመጀመሪያ ጊዜ የማራቶን ውድድሩ (2:05:15) በመሮጥ አሸንፏል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አዲሱ አትሌት ተስፋሁን ( 2:06:27) ሮጦ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ።
በሴቶቹ ተመሳሳይ ርቀት ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አንቺንአሉ ደሴ (2:22:17) በመሮጥ አሸንፋለች ። የፈረንሣይዋ አትሌት ማኖን ትራፕ እና ኬንያዊቷ ሲንቲያ ኮስገይ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሁነዋል። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ትእግስት ገዛኸኝ ሞሮኮያዊቷ ኮታር ቦውላይድን ተከትላ በአምስተኛ ደረጃ (2:24:25) አጠናቃለች ።
እግር ኳስ
የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) ከዩጋንዳ አቻው ጋር ካምፓላ ውስጥ ባደረገው የመጀመሪያ ግጥሚያ በዩጋንዳ ቡድን የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል ። መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ በሁለቱም በኩል አንድም ግብ አልተቆጠረም ነበር ። ሁለቱ ግቦች የተቆጠሩት በ89 እና 93ኛው ደቂቃዎች ላይ ነበር ። ለዩጋንዳ ቡድን 89ኛው ደቂቃ ላይ ይና ናሙሌሜ፤ እንዲሁም መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አብቅቶ በጭማሪው 3ኛ ደዲቃ ላይ ፋዚላ ኢክዋፑት ሁለተኛውን አስቆጥረዋል ። አዲስ አበባ ውስጥ ረቡዕ የመልስ ጨዋታ ይኖራል ።
ፕሬሚየር ሊግ
ትናንት ወደ ኤታድ ስታዲየም ያቀናው ሊቨርፑል ማንቸስተር ሲቲን በገዛ ሜዳው ጉድ አድርጎታል ። ማንቸስተር ሲቲ ምንም እንኳን በገዛ ሜዳው ሽንፈት ቢገጥመውም በኳስ ይዞታ ግን ከሊቨርፑል በልጦ ታይቷል ። በተለይ ጄሬሚ ዶኩ በክንፍ በኩል በኳስ ጥበቡ እና በፍጥነቱ ተከላካዮችን ሲያስጨንቅ አምሽቷል ። ሊቨርፑሎች ሁለት ግቦችን ካስቆጠሩ በኋላ እጅግ ወደ ኋላ ተመልሰው በብርቱ መከላከላቸው እና በመልሶ ማጥቃት ላይ ማተኮራቸው ማንቸስተር ሲቲን እንደጎዳው ገልጧል ። ጄሬሚ ዶኩ በተለይ የሊቨርፑል ተከላካይ አሌክሳንደር አርኖልድን በኳስ ጥበብ፤ በተክለ ሰውነት እና ድንገት አፈትልኮ በማለፍ ሲያንገላታው አምሽቷል ። የየካቲት 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ለሊቨርፑል ሞሐመድ ሣላኅ እና ዶሚኒክ ሶቦስላይ በ14ኛው እና 37ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፈዋል ። ሞሐመድ ሣላኅ የትናንቱን ጨምሮ እስካሁን 25 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ በኮከብ ግብ አግቢነት ይመራል ። የኒውካስል አጥቂ አሌክሳንደር ይሳቅ ሞሐመድ ሣላኅን በመከተል እንደ ማንቸስተር ሲቲው ኧርሊንግ ኦላንድ 19 ኳሶችን አስቆጥሮ ሁለተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ነው ። ሊቨርፑል አሌክሳንደርን ለማስመጣት ፍላጎት ቢኖረውም ኒውካስትል በጠየቀው የ190 ሚሊዮን ዶላር ግድም የመልቀቂያ ክፍያ ግን እንደማይስማማ ተገልጧል ። ሊቨርፑል ይህን ያህል እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ አንድ ተጨዋች ላይ ብቻ ማፍሰስ እንደማይፈልግም ተጠቅሷል ።
በፕሬሚየር ሊጉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ሊቨርፑልን በ11 ነጥብ የሚከተለው አርሰናል ቅዳሜ ዕለት በገዛ ሜዳው በዌስትሐም 1 ለ0 መሸነፉ በዋንጫ ተፎካካሪነቱ ላይ ጋሬጣ ደቅኖበታል ። ቀጣይ ጨዋታው ሦስተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ኖቲግንሀም ፎረስት ሜዳ ነው ። ትናንት በኒውካስል የ4 ለ3 ሽንፈት ያስተናገደው ኖቲግንሀም ፎረስት 43 ነጥብ አለው ። አርሰናል 53 ነጥቦችን ሰብስቧል ። ቅዳሜ ዕለት በአስቶን ቪላ 2 ለ1 የተሸነፈው ቸልሲ ነገ ማታ ከሳውዝሐምፕተን ጋር ይጋጠማል ። ዎልቭስ ከፉልሀም፣ ክሪስታል ፓላስ ከአስቶን ቪላ እንዲሁም ብራይተን ከቦርመስ ጋርም ነገ ይጫወታሉ ። የጥር 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ቡንደስ ሊጋ
የጀርመን ቡንደስ ሊጋን በ58 ነጥብ የሚመራው ባዬርን ሙይንሽን ትናንት አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 4 ለ0 ድባቅ መትቷል ። በ50 ነጥብ የሚከተለው ባዬር ሌቨርኩሰን በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት ሆልሽታይን ኪዬልን 2 ለ0 አሸንፏል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ42 ሦስተኛ፣ ቬርደር ብሬመንን 5 ለ0 ያንኮታኮተው ፍራይቡርግ በ39 ነጥብ አራተኛ፣ ሳንክት ፓውሊን 2 ለ0 ያሸነፈው ማይንትስ በ38 አምስተኛ ሆነው ይከታተላሉ ። ከታችኛው ዲቪዚዮን ካደገው ሐይደንሀይም ጋር ትናንት ሁለት እኩል የተለያየው ላይፕትሲሽ ከማይንትስ በግብ ክፍያ ተበልጦ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሐይደንሀይም ቦሁም እና ሆልሽታይን ኪዬል ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ።
የተለያዩ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች
ነገ እና ከነገ በስትያ የተለያዩ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ። በስፔን ዓመታዊ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ውድድር (copa del rey)፦ ነገ ባርሴሎና አትሌቲኮ ማድሪድን ያስተናግዳል ። ከነገ በስትያ ደግሞ ሪያል ማድሪድ ከሪያል ሶሴዳድ ሳን ሠባስቲያን ጋር ይጫወታል ። የመልስ ጨዋታዎች ሳምንት ይኖራሉ ።
በጣሊያን ዋንጫ (Coppa Italia)የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ፦ ኢንተር ሚላን ነገ ማታ ላትሲዮ ሮምን ያስተናግዳል ። በበነጋታው ደግሞ፦ ጁቬንቱስ ከኢምፖሊ ጋር ይጋጠማል ። ቀደም ባሉ ጨዋታዎች ቦሎኛ አታላንታን 1 ለ0፤ ኤሲ ሚላን ኤኤስ ሮምን 3 ለ1 አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል ። በአውሮጳ የኔሽን ሊግ እግር ኳስ የምድብ አንድ መሪ ኦስትሪያ እና ተከታዩ ጀርመን ነገ ማታ ይጋጠማሉ ። ምድቡን የኦስትሪያ ቡድን በ3 ነጥብ ይመራል፣ ጀርመን እና ኔዘርላንድ በ1 ነጥብ ይከተላሉ ። የስኮትላንድ ቡድን ያለምንም ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። የጥር 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በጀርመን ፖካል (DFB)ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ፦ ነገ ማታ አርሜኒያ ቢሌፌልድ ቬርደር ብሬመንን ይገጥማል ። በበነጋታው ረቡዕ ደግሞ በቡንደስሊጋው ተደጋጋሚ ሽንፈት የገጠመው ላይፕትሲሽ ከቮልፍስቡርግ ጋር ይጫወታል ። ቀደም ሲል በነበሩ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች፦ ሽቱትጋርት አውግስቡርግን 1 ለ0 እንዲሁም ባዬር ሌቨርኩሰን ኮሎኝን 3 ለ2 አሸንፈዋል ።
የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር አዲስ ለሚመሠረተው መንግሥት ጥሪ
የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር (DFB) አዲስ ለሚመሠረተው የጀርመን መንግሥት ባለ ዐሥር ነጥብ ጥያቄዎችን አቅርቧል ። ከጥያቄዎቹ መካከል፦ በፌዴራል መራኄ መንግሥት ስር የስፖርት ሚንስትር ዴኤታ ይኑር፣ ለትርፍ ላልተመሠረቱ ቡድኖች የቀረጥ እፎይታ ይደረግ እና በስፖርቱ የከባቢ አየር ጥበቃ የበለጠ ትኩረት ይሰጠው የሚሉት ነጥቦች ይገኙበታል ። ግዙፉ ማኅበር 24,000 ቡድኖች እና ወደ 8 ሚሊዮን ግድም አባላትን ያቀፈ ነው ።
የሜዳ ቴኒስ
የ44 ዓመቷ የሜዳ ቴኒስ የዓለማችን ድንቅ ተጨዋች ቬኑስ ዊሊያምስ የፊታችን እሁድ ሕንድ ውስጥ በሚከፈተው የኢንዲያን ዌልስ ውድድር ተካፋይ እንደማትሆን ዐሳወቀች ። አሜሪካዊቷ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች በውድድሩ እንደምትሳተፍ አዘጋጆቹ በድረ ገጻቸው ይፋ አድርገው ነበር ። ሆኖም ቬኑስ ስለውድድሩ አስቀድሞ ስላልተነገረኝ እና ሌላ ጉዳይ ስላለኝ በእሁዱ ግጥሚያ አልሳተፍም ብላለች ። ቬኑስ በእሁድ ውድድር ለ10ኛ ጊዜ እንድትሳተፍ አዘጋጆቹ ሁኔታዎችን አመቻችተውላት እንደነበር ተዘግቧል ። ሚያሚ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት ከተደረገው ውድድር ወዲህ ሴሬና ተወዳድራ ዐታውቅም ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር