የየካቲት 10 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ የካቲት 10 2017በዓለም የአትሌቲክስ ውድድር መድረኮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለድል በቅተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሰባት ነጥብ ልዩነቱን ያስጠበቀው ሊቨርፑልን ትናንት ዎልቭፍስ እጅግ ፈትኖታል ። በርካታ ተጨዋቾቹን በሕመም እና ጉዳት ማሰለፍ ያልቻለው ማንቸስተር ዩናይትድ በታዳጊ ተጨዋቾቹ ተጋጥሞ በጠበበ የግብ ልዩነት ተሸንፏል ። የማንቸስተር ሲቲው አዲሱ ተሰላፊ ዖማር ማርሙሽ በ19 ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽን እና ተከታዩ ባዬር ሌቨርኩሰን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ በሚገኘው ቦሁም ጉድ ሁኗል ።
አትሌቲክስ
በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተከናወኑ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተቀዳጅተዋል ። የካቲት 9 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በተካሄደው የኦርሌን ኮፐርኒከስ የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ፉክክር አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ የቦታውን ክብረወሰን አሻሽላ አሸንፋለች ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት ለድል በበቁበት የፓላንድ የሩጫ ፉክክር አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለድል የበቃችው 3:53.92 በመሮጥ የራሷን ክብረወሰን በማሻሻል ነው ። የገባችበትም ሰአት የቦታው ፈጣን ተብሏል ።
የሁለት ጊዜያት የዓለም ባለድል አትሌት ጉዳፍ በ1500 ሜትር የቤት ውስጥ ፉክክር ታሪክ ፈጣን ሴት አትሌቶች ተርታ ሦስተኛዋ ሆና ተመዝግባለች ። ከሷ በመቀጠል የዓለም ፈጣኑ ሰአት ሆኖ የተመዘገበው በአገሯ ልጅ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ (3:55.17)ጀርመን ካርልስሩኸ ውስጥ ከ11 ዓመታት በፊት የተያዘው ሰአት ነበር ። በትናንቱ የኦርሌን ውድድር፦ አትሌት ብርቄ ሃየሎም 3:59.82 በመግባት ሁለተኛ ደረጃ ስታገኝ፤ አትሌት ወርቅነሽ መሰለ ደግሞ በ4:02.19 ሦስተኛ ሆና አጠናቃለች ። አትሌት ሣሮን በርኸ ፖላንዳዊቷ ቬሮኒካ ሊዛኮቭስካ እና የብሪታንያዋ ሬቪ ዋልኮት-ኖላን ተከትላ ስድስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።
ብርቱ ፉክክር በታየበት የወንዶች የ1500 ሜትር ውድድር አትሌት ቢኒያም መሐሪ 3:35.70 ሮጦ በመግባት ሁለተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ። የብሪታንያው ሯጭ ኤሊዮን ጊልስ ከአንድ ሰከንድ እጅግ ባነሰ ሽርፍራፊ ሰከንድ ለጥቂት አንደኛ ወጥቷል ። ስዊድናዊው ሣሙኤል ፊልስትሮም በበኩሉ የሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የየካቲት 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
እዛው ፖላንድ ኦርሌን ውስጥ በተከናወነው የሴቶች 800 ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል ። አትሌት ፅጌ ዱጉማ 2:00.04 በመግባት በአንደኝነት አጠናቃለች ። የአገሯ ልጅ አትሌት ሀብታም ዓለም ደግሞ 2:00.61 ሮጣ በሁለተኛ ደረጃ አጠናቃለች ። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት ግርማ ፖላንዳዊቷ አና ዌልጎሽ እና ጣሊያናዊቷ ኢሎይሳ ሶይሮን ተከትላ አምስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።
በስፔን ፋክሳ ካስቴሎን የ10 ሺህ ሜትር የጎዳና ፉክክርም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች አሸንፈዋል ። በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር ከአንድ እስከ ሦስት ድሉ የኢትዮጵያውያቱ ሁኗል ። በአንደኛነት ያጠናቀቀችው አትሌት መዲና ኢሳ የፈጀባት ጊዜ 29 ደቂቃ ከ25 ሴኮንድ ነው ። በዚህ ውድድር አትሌት ልቅና አንባው ሁለተኛ ፤ አትሌት ዓይንአዲስ መብራቱ ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል ።
በወንዶቹ ፉክክር፦ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ 26ደቂቃ ከ31ሴኮንድ በመሮጥ የቦታውን አዲስ ክብረወሰን በማስመዝገብ አሸንፏል፥ በርቀቱም የግል ምርጥ ሰዓቱ ሁኖ ተመዝግቦለታል ። አትሌት ኩማ ግርማ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። አትሌት መልክነህ አዘዘ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን አጠናቅቋል ።
ፕሬሚየር ሊግ
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች፦ መሪው ሊቨርፑል ትናንት በትግል ዎልቭስን 2 ለ1 አሸንፏል ። በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቀጣና ጠርዝ 17ኛ ላይ የሚገኘው ዎልቭስ ሊቨርፑልን በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ፈትኖ ታይቷል ። መደበኛ ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት የነበሩት 25 ደቂቃዎች ለበርካታ የሊቨርፑል ደጋፊዎች አስጨናቂ ነበሩ ።
እንዲያም ሁኖ የሊቨርፑል የመሀል ተከላካይ አንበሉ ቪርጂል ቫን ጂክ የተፈጠረውን ምቾት የማይሰጥ ሁኔታ እናስተካክላለን ብሏል ። የትናንቱ ውጤት ምንም እንኳን ሊቨርፑል የዘንድሮ ዋንጫን ለማንሳት በሚያደርገው ግስጋሴ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ባይኖረውም ረቡዕ ከአስቶን ቪላ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ግን በተጨዋቾቹ ሥነ-ልቦና ላይ ብርቱ ጫና ማሳረፉ አይቀርም ። ሊቨርፑል ከቆዩ ልምዶቹ አንጻር አንድ ጊዜ በተጨዋቾቹ ውስጥ የሥነልቦና መረበሽ ከተከሰተ ለማስተካከል እጅግ አስቸጋሪ ነው ሲሆን ነው የሚታየው ። የጥር 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሊቨርፑል ፕሬሚየር ሊጉን በ60 ነጥብ ይመራል፥ ተከታዩ አርሰናል በሰባት ነጥብ ተበልጦ በ53 ይከተላል ። ሊቨርፑል ረቡዕ ዕለት አስቶን ቪላን ማሸነፍ ከቻለ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ዐሥር ከፍ በማድረግ በቡድኑ ውስጥ መረጋጋት ይፈጥር ይሆናል ። ቪላ ፓርክ ውስጥ የሚጠብቀው አስቶን ቪላ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይመስልም ። በዚያ ላይ ሊቨርፑል ባለፈው ከኤፍ ኤ ካፕ አራተኛ ዙር ውድድር በፕሌይማውዝ በአስደንጋጭ ሁኔታ ሲሰናበት የተጎዳው ጆ ጎሜዝ አይሰለፍም ። አሰልጣኝ አርኔ ስሎት በጉዳት የተነሳ ወደ ቪላ ፓርክ የሚያቀኑት ያለ ኮዲ ጋክፖ እና ቴይለር ሞርቶን ጭምር ነው ።
በሌላ የትናንት ግጥሚያ፦ ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ቶትንሀምን ሆትስፐር ስስታዲየም ውስጥ ገጥሞ 1 ለ0 ተሸንፏል ። በ13ኛው ደቂቃ ላይ በጄምስ ማዲሰን የተቆጠረችው ብቸኛ ግብ ቶትንሀም ሆትስፐር ሦስት ተጨማሪ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሎታል ። ማንቸስተር ዩናይትድ አሁን በ29 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ወራጅ ቀጣና ውስጥ ከሚገኙት ኢፕስዊች ታወን፤ ላይስተር ሲቲ እና ሳውዝሐምፕተን ቢያንስ የአራት ጨዋታዎች ድል፦ ማለትም 12 ነጥብ ልዩነት አለው ።
አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ላይስተር ሲቲን በሜዳው 2 ለ0 በማሸነፉ ነጥቡን 53 አድርሷል ። በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት በፉልሀም የደረሰበት የ2 ለ1 ሽንፈት በ47 ነጥቡ ተወስኖ ከመሪው ሊቨርፑል በ13 ነጥብ ልዩነት እንዲርቅ አስገድዶታል ። አጀማመሩ ላይ የዘንድሮ የፕሬሚየር ዋንጫ ብርቱ ተፎካካሪ የነበረው ማንቸስተር ሲቲ ምንም እንኳን ኒውካስትልን 4 ለ0 ድል ቢያደርግም ነጥቡ 44 ነው ። ማንቸስተር ሲቲ ዳግም የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን ከእንግዲህ አንድም ሽንፈት ሳይገጥመው ሊቨርፑል አራት ጨዋታዎችን መሸነፍ አለበት ። ያ የመሆን እድሉ እጅግ አናሳ ነው ። ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲሱ ፕሬዚደንት ምን ይጠበቃል? አንድ ለአንድ፥ ቃለ መጠይቅ
የግብ አዳኞችን የማፍራት ዕድሉ ግን የሰፋ ይመስላል ። የማንቸስተር ሲቲው አዲሱ ተሰላፊ ዖማር ማርሙሽ ከኒውካስትል ጋር በነበረው የቅዳሜ ግጥሚያ፦ በ19 ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል ። በ43 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ ብራይተንን በገዛ ሜዳው 3 ለ0 ኩም ማድረግ ችሏል ።
የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር
ከጥር 27 ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ የተካሄደው የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር ላይ ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ ስፖርተኞች ከዕድሜያቸው በታች መሳተፋቸው አነጋጋሪ ሁኗል ። የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ያነጋጋራቸው ስፖርተኞች እና ባለሞያዎችም ይህንኑ ተናግረዋል ። በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የውድድር ዴስክ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳርጌም በውድድሩ የዕድሜ ማችበርበር ችግር መከሰቱን አረጋግጠዋል ። የመስማት የተሳናቸውን ዘርፍ ጨምሮ በ12 የስፖርት ዘርፎች ውድድሩ መካሄዱም ተገልጧል ።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽን ከተከታዩ ባዬር ሌቨርኩሰን ጋር ቅዳሜ ዕለት ተጋጥሞው ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። 55 ነጥብ አለው፥ ባዬር ሌቨርኩሰንን በስምንት ነጥብ ይበልጣል ። አይንትራኅት ፍራንክፊፉርት በአንጻሩ ሆልሽታይን ኪዬልን 3 ለ1 አሸንፎ ከባዬርን ሌቨርኩሰን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ዝቅ አድርጓል ። በ37 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ ከአውግስቡርግ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል ።
ቡንደስሊጋውን የባዬርን ሙይንሽን አጥቂ ሔሪ ኬን በ21 ከመረብ ያረፉ ኳሶች በኮከብ ግብ አግቢነት ይመራል ። በ15 ግቦች ሁለተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ወደ ማንቸስተር ሲቲ አቅንቶ እዚያም የግብ ቀበኛ መሆን የቻለው የቀድሞው የአይንትራኅት ፍራንክፉርቱ ዖማር ማርሙሽ ነው ። ከአንድ ወር በፊት በ72 ሚሊዮን ዶላር ዝውውር ወደ ማንቸስተር ሲቲ ያቀናው ዖማር ማርሙሽ በ19 ደቂቃዎች 3 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ድንቅ ተጨዋች ነው ። የባዬርን ሌቨርኩሰኑ ፓትሪክ ሺክ በ14 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ሦስተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ነው ። በ29 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቦሁም የ2 ለ0 ሽንፈት ቀምሶ ተመስልሷል ።
ሻምፒዮንስ ሊግ
ነገ እና ከነገ በስትያ ስምንት የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ። ሊቨርፑል በ21 ነጥብ በመሪነት ባርሴሎና በ19 ነጥብ በሁለተኛነት ወደ ጥሎ ማለፉ አስቀድሞ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል ። በነገው ዕለት በሚኖረው የመልስ ግጥሚያ፦ የጀርመኑ ባዬርን ሙይንሽን የስኮትላንዱ ሴልቲክን አሊያንትስ አሬና ውስጥ ያስተናግዳል ። 84 ከመቶ እንደሚያሸንፍ ግምት የተሰጠው ለባዬርን ሙይንሽን ቡድን ነው ። የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ከሆላንዱ ፌዬኖርድ፣ የስፔኑ ቤኔፊካ ከፈረንሣዩ ሞናኮ፣ የጣሊያኑ አታላንታ ከቤልጂየሙ ክለብ ብሩጅ ጋር የሚጋጠሙት ነገ ማታ ነው ። ረቡዕ ዕለት ደግሞ፦ ዩጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ያስተናግዳል ። የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ጋር ይጋጠማል ። የፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ ፓርክ ደ ፕሪንስ ስታዲየም ውስጥ ሌላኛው የፈረንሣይ የሊግ አንድ ተጋጣሚ ቡድን ብሬስትን ያስተናግዳል ። የሆላንዱ ፒኤስቪ አይንድሆቨን ከጣሊያኑ ጁቬቱስ ጋር ይጋጠማል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ