የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ላይ ላነሱት ወቀሳ ምላሽ ሰጠ
ሐሙስ፣ ግንቦት 21 2017የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው "ኢትዮጵያ በሰከነ ዲፕሎማሲ፣ ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ተባብሮ መሥራት ላይ ያተኮረ መርህ" እንደምትከተል የገለፁት የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ራሷን የቻለች ሀገር የሆነችበትን 34ኛ የነጻነት በዓል አስመልክቶ ሰሞኑን ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ለሰነዘሩት ትችት ማብራሪያ ተጠይቀው ሲመልሱ ነው።
ኢትዮጵያና ኤርትራ ዳግም ጦርነት ይገጥሙ ይሆን? የፕሬዝደንት ኢሳያስ መልዕክት፣ የፖለቲካ ተንታኝና የፖለቲከኛ አስተያየት
ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ "የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት ጦርነት" ማወጃቸውንና ብልጽግና ፓርቲንም በዚህ ወኪልነት ከሰዋል። "የውኃ፣ የቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት" እና መሰል ጉዳዮች ጦርነት ለመቀስቀስ የሚነሱ ጉዳዮች መሆናቸውንም በንግግራቸው ገልፀው ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው እንዳሉት ግን ኢትዮጵያ "የሰከነ ዲፕሎማሲን" ከማራመድ በቀር ነገሮችን አታባብስም።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ተጠይቀው ሌላው ምላሽ የሰጡበት ጉዳይ የባህር በር የማግኘቱን የኢትዮጵያን ፍላጎት የተመለከተው ነው። ኢትዮጵያ ይህን ጥያቄዋን "ሕጋዊ፣ ፍትሐዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ብቻ" እንደምታስፈጽመውም አብራርተዋል።
"ይህ ጥያቄ በአመዛኙ ሕዝቡ የሚስማማበት፣ ከኢትዮጵያ መፃዒ የኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት ጋር የተሳሰረ መሆኑን በሀገራችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገራት ዘንድ የኢትዮጵያ ጥያቄ ሕጋዊ እና አግባብ ያለው መሆኑን ግንዛቤ የተያዘበት ወቅት ላይ ነን"።
"700 ኢትዮጵያውያን ከምያንማር ተመልሰዋል"
መንግሥት እስካሁን በምያንማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 700 ኢትዮጵያዊያንን ማስመለሱንም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ተናግረዋል። ይሁንና ይህ ጥረት እየተደረገ እንካን ጉዳዩን "በቸልታ በመመልከት አሁንም ይህ ሕገ ወጥ ጉዞ አልቆመም" ብለዋል። አልፎም ከውጭ ጉዳይ ውክልና አለን በማለት እና በሚኒስትሮች ስም የሚያጭበረብሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች መኖራቸው እንደተደረሰበት አመልክተዋል።
ማሕደረ ዜና፣ የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትችትና ነቀፋ የዳግም ጦርነት ዝግጅት ይሆን?
የሕንድና ፓኪስታንን ግጭት በተመለከተ የኢትዮጵያ አቋም
በሕንድ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍሰሐ ሻውል ከሳምንት በፊት የሕንድ እና የፓኪስታንን ግጭት በተመለከተ ለግጭቱ ፓኪስታንን ተጠያቂ ያደረጉበትን ቃለ መጠይቅ በተመለከተ መብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው፣ ኢትዮጵያ ከሁለቱም ሀገራት ጥሩ ግንኙነት ያላት መሆኑን፣ በሀገራት መካከል የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በገለልተኛነት እና በፍትሐዊነት እንዲፈቱ የማገዝ፣ ግጭቶችም በሰላም መፈታት አለባቸው የሚል አቋም የምታራምድ መሆኗን እና የገለልተኝነትን መርህ ማራመድ አሁንም የፀና አቋም መሆኑን ግልጽ አድርገዋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ