የውጭ ዜጎችን የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት የሚያደርገው ረቂቅ ሕግ ተስፋ እና ሥጋት
ዓርብ፣ ሚያዝያ 24 2017
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ዜጎችየማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ መሆን የሚችሉበትን ውሳኔ ትናንት አሳልፏል። ውሳኔው የውጭ ዜጎች ሰፊ "ካፒታል በሥራ ላይ እንዲያውሉ ለማበረታታት፣ የቤት ልማት እና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማነቃቃት" እንደሚረዳ ታምኖበታል።
ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ውሳኔውን በተስፋም በሥጋትም ተመልክተውታል። "የውጭ ቤት አልሚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ባነሰ ዋጋ፣ በተሻለ ጥራት በመገንባት የቤት ችግርን ያቃልላሉ" የሚለው በጎ ምልከታ የተሰጠው አተያይ ነው።
በአንጻሩ የውጭ ዜጎች "የተሻለ ቴክኖሎጂ፣ ሀብት እና ልምድ ያላቸው በመሆኑ ኢኮኖሚው ይዋጣል፣ ይህም የሀገር ባለቤትነት ላይ ፓለቲካዊ ጥያቄ ይፈጥራል" የሚል ሥጋት እንደሚያስከትል የጠቀሱም አሉ።
ዋናው ጉዳይ ተግባሩን በጥንቃቄ መምራቱ ነው፣ አወንታዊ የባለሙያ ምልከታ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ሚያዚያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም "የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን" ውሳኔ አሳልፎ፣ ረቂቅ አዋጅን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶቷል። "የዜጎችን የመሬት ይዞታ የማግኘትና የመጠቀም መብት በማያጣብብ መልኩ" ይተገበራል የተባለው ይህ የመንግሥት ውሳኔ በአወንታም፣ በሥጋትም ሀሳብ እየተሰጠበት ነው።
የኢኮኖሚ አማካሪእና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ ገበያን ክፍት አድርጉ የሚለው ጥያቄ በተለያየ ጊዜ ሲጠየቅ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ውሳኔውን በበጎ ተመልክተውታል። ዋናው ነገር ተግባሩን በጥንቃቄ የመምራቱ ጉዳይ መሆኑን በማስታወስ።
"ሁልጊዜ መሬትህን ወይም ሀገርህን ዘግተህ መኖር አትችልም። ስለዚህ የውጭ ዜጎች ወይም የቢዝነስ ተቋማት የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲያፈሩ ማድረግ አሁን ጊዜው ይመስላል። ምክንያቱም ብዙ ነገር ከፍተናል"።
"የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦትሚዛን ለማስጠበቅ" ይረዳል የተባለለት ይህ ውሳኔ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ታምኖበታል። የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ግን የተለየ ምልከታ አላቸው።
"ያለ ብድር እና እርዳታ ዓመታዊ በጀታችን እንኳን የማይሞላልን ሀገር እንደሆንን የ25 ዓመት ጉዟችን ወደኋላ ያሳያል እና ትንሽ ጉዳቱ ያመዝና [ውሳኔው] ብየ ነው የማምነው"
የማይንቀሳቀስ ንብረት ምንድን ነው?
የንብረት መብትን የሚመለከተው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 "የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥት እና የሕዝብ ብቻ ነው" ይላል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ "መንግሥት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል" ሲልም ደንግጓል። ድንጋጌው የውጭ ዜጎችን ያካትት እንደሆን ግን ያለው ነገር የለም። የኢኮኖሚ አማካሪ እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ እንደሚሉት ይህ ውሳኔ በተለይ ከቤት ልማት አንጻር እጅግ ጠቃሚ ነው።
"አንዱ የምንጠብቀው በተለይ የውጭ ሀገር የቤት አልሚዎች ባነሰ ዋጋ፣ በተሻለ ጥራት፣ የቤት ልማት ዘርፉን ያነቃቃሉ [ብለን ነው] ። ስለዚህ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ እንዲያቀርቡ የሚያደርጉበት ብልሃት ይኖራቸዋል"።
የውጭ ዜጎችን የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት የሚያደርገው ውሳኔ ላይ ያሉ ሥጋቶች
ሀገሪቱ ያላትን አጠቃላይ ሀብትበማሳደግ እና ኢኮኖሚውን በተሻለ ለማንቀሳቀስ የሚጠቅም "ወረት ለመፍጠር" ያግዛል የሚሉት አቶ ሽዋፈራሁ ሽታሁን፣ መሰል ቁልፍ የመንግሥት ውሳኔዎች ከቁስ ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡ የኢኮኖሚ መብትና ሉዓላዊነት አንፃር መታየት አለበት የሚል መከራከሪያ አላቸው።
"በቀጥታ የውጭ ዜጎች የሚንቀሳቀስም የማይንቀሳቀስም ሀብት እንዲያፈሩ የሚፈቅደው ነገር ኢኮኖሚያችን በሂደት መዋጡ አይቀርም። ምክንያቱም እነሱ በንጽጽር ቴክኖሎጁው ላይ፣ ሀብቱ ላይ የተሻለ ሠርተዋል። ከእኛ የተሻለ ዕድል አላቸው። ስለዚህ ምጣኔ ሐብታችንን ውጠውት የሀገር ባለቤትነት [ስሜት] ላይ ሌላ ፓለቲካዊ ጥያቄ እና መውገርገርን ያስከትላል"።
"የማይንቀሳቀስ ንብረት የመሬት ይዞታ መጠቀሚያ መብት እና መሬት ነክ ሀብት ሲሆን - ለንግድ፣ ለመኖሪያነት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለማህበራዊ እና ለሌሎች አገልግሎት ለሽያጭ ለኪራይ አገልግሎት እንዲውል የተገነባ ሕንፃ እና ተጓዳኝ ግንባታዎችን የያዘ ንብረት ነው" የሚል ትርጓሜ ያለው ነው፡፡
ሶሎሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ