የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የጤና ተቋማት ጉዳይ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2014በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሁኔታ ላይ ባለመሆናቸዉ ኅብረተሰቡ ለከፋ ጤና ችግር መጋለጡን የአካባቢው ነዋሪዎችና ባለስልጣናት ተናገሩ። የብሔረሰብ አስተዳደሩ በህወሓት ኃይሎች በተያዘበት ወቅት አካባቢዉ ላi የሚገኙ ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ባርናባስ ባደረጉት ጥረት የአካባቢው ሆስፒታል በከፊልም ቢሆን ጉዳት እንዳልደረሰበት ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሓት ኃይል በሰቆጣ ከተማ ተደጋጋሚ ወረራ በማድረግ ከፍተኛ የማህበራዊ መስጫ ተቋማት ማውደሙን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በተለይ በከተመው የሚገኙት 4 ጤና ኬላዎችና አንድ ጤና ጣቢያ መቶ በመቶ መውደማቸውን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አሸብር ግርማ አመልክተዋል። ሥራ የሚያስጀምር ሁኔታ ባለመኖሩ ወደ ስራ መግባት እንዳልተቻለ ደግሞ የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ ቢምረው ተናግረውናል።
ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጤና ተቋማት ስራ የሚጀምሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተጠይቋል ግን ምላሽ ባለመኖሩ ተላላፊና ተላላፊ ያልሁኑ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ሰጋት መኖሩን አስረድተዋል። የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና የምዕራብ ካናዳ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባርናባስ በጦርነቱ ወቅት ተቋማት እንዳይዘረፉና እንዳይወድሙ ጥረት ማድረጋቸውንና በዚህም መሰረት ሆስፒታሉ የከፋ ጉዳት አልደረሰበትም ብለዋል። በጤና ተቋማቱ ዝርፊያና ውድመት ተሳትፎ አለው ስለተባለው የአገው ብሔራዊ ሸንጎና የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተቋማቱን ስራ ለማሰጀመር እንቅስቃሴ አላደረገም ስለተባለው ስሞታ አስተያየት ለማካተት ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ