የክርስቲያን ዴሞክራት የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት እና የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ስምምነት
ረቡዕ፣ መጋቢት 3 2017ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ የደረሱት የጀርመን ምርጫ አሸናፊ እህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች በምርጫው ሦስተኛ ደረጃ ካገኘው ከሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ SPD ጋር ጥምር መንግስት ለመመስረት ትልቅ እርምጃ ላይ ደርሰናል ሲሉ አስታውቀዋል። የአሸናፊዎቹ እህትማማች ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስ ንግግሩ ባለቀበት ባለፈው ቅዳሜ እንዳሉት ሁለቱ ወገኖች በሦስት ዋና ዋና ፖሊሲዎች ላይ ተስማምተዋል።
እነርሱም የምርጫው ዋና ትኩረት የነበሩት ፍልሰት ፣ ፋይናንስ የስራ ገበያና ኤኮኖሚ ናቸው። የበርሊኑ የመጀመሪያ ደረጃው ንግግር ሲያበቃ ሜርስ እንደተናገሩት ሁለቱ ወገኖች ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ከጀርመን ድንበሮች ለመመለስ አቅደዋል።«ከአውሮጳ ሀገራት ጎረቤቶቻችን ጋር በመተባበር በጋራ ድንበሮቻችን ላይ የተገን ጥያቄ ማመልከቻዎችን እንቀበልም። ሕገወጥ ስደትን ለመቀነስ ማናቸውንም ሕገ መንግስታዊ እርምጃዎች ለመውሰድ እንፈልጋለን። ጥምሩ መንግስት ከሚመሰረትበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ የድንበር ቁጥጥርን በከፍተኛ ደረጃ እናጠናክራለን። የድንበር ቁጥጥሩንም የተገን ጥያቄን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ እንጠቀምበታለን።»በጀርመን ምርጫ አሸናፊው ፓርቲ የሚመሰርተው መንግስት ከፊቱ ምን ይጠብቀዋል ?
ከዚህ ሌላ ፓርቲዎቹ በቅርቡ የተሻሻለው የጀርመን የዜግነት ሕግ እንዲቀጥልም ተስማምተዋል። በፍልስት ጉዳይ ላይ የተለያየ አቋም የነበራቸው ሁለቱ ፓርቲዎች በመጀመሪያ ደረጃ ንግግራቸው ለተስማሙባቸው ስለነዚህ ጉዳዮች የጠየቅናቸው ለበርካታ ዓመታት ጀርመን የኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊው የምጣኔ ኃብትና አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ ዓላማቸውን ምን እንደሆነ ተናግረዋል። ቀጣዩ የጀርመን መራኄ መንግስት እንደሚሆኑ የሚጠበቀው ሜርስ በርካታ ፈተናዎች የተጋረጡበትን የጀርመንን ኤኮኖሚ የማነቃቃት እቅድ አላቸው። ከዚሁ ጋር ቀረጥ በመቀነስ በተለይ መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል የኑሮ ጫና ለማቅለል የዋጋ ቅነሳዎችን ለማድረግም አቅደዋል። እነዚህና ሌሎችም አሁን በሚሰናበተው መንግስት ተግባራዊ ያልሆኑ ማበረታቻዎችም በስምምነቱ ውስጥ ተካተዋል እንደ ዶክተር ጸጋዬ።
የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ተባባሪ መሪ እና በጀርመን ፓርላማ የፓርቲው አባላት ቡድን መሪ ላርስ ክሊንግቤል እንደሚሉት የሠራተኞች ዝቅተኛ ክፍያ በሰዓት 15 ዩሮ ወይም 16 ዶላር እንዲሆን ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ጥምር መንግስት ለመመስረት ወደ ድርድር የሚሸጋገሩት ሁለቱ ፓርቲዎች ተጣምረው መንግስት ለመመስረት ከበቁ እንደሚሰናበተው መንግስት ሁሉ ለዩክሬን የሚሰጡትን እርዳታ የመቀጠልና እቅድ አላቸው። ከዚሁ ጋር በተለይ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአትላንቲክ ወዲያ ማዶ ያለውን ግንኙነት ካናጉ በኋላ ፣የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ወደፊት ተጠናክሮ መቀጠሉ ያጠራጠራቸው ሜርዝ የጀርመንን ጦር ኃይል ለማጠናከርም ይፈልጋሉ።የጀርመን ምርጫ 2025 ፋይዳ ተግዳሮቶቹና አስተምህሮቱ
በጎረቤቶቻቸው በሜክሲኮና በካናዳ ላይ የታሪፍ ጭማሪ ዛቻቸውን የቀጠሉት ትራምፕ ከዚያ ቀጥሎ ቀደም ሲል ሲዝቱ እንደከረሙት ትኩረታቸውን ከአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ትራምፕ እንዳሉትም በታሪፍ ጭማሪው አቋማቸው ከጸኑ ጀርመን ብዙ ተግዳሮቶች ሊገጥሟት ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዶክርት ጸጋዬ ያስረዳሉ። ይህን ተከትሎም ጀርመንን ጨምሮ የኅብረቱ አባል ሀገራት የአጸፋ እርምጃዎችን መውሰዳቸው እንደማይቀር ይገመታል።
ወደፊቱ የሚመሰረተው የጀርመን ጥምር መንግሥት ለዩክሬን የሚሰጠው እርዳታ እንዲቀጥልና የመከላከያ ወጪን ለመጨመር እንዲሁም ለመሰረተ ልማት ግንባታ አስፈላጊ ለሆኑ ወጪዎች ገንዘብ ለማግኘት ጥብቅ የሆነውን የጀርመንን ሕገ መንግስታዊ የእዳ ህጎች ለማላላትም ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህን ማሻሻያ በፓርላማው ለማሳለፍ ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ስለሚያስፈልግ ደግሞ በንግግሩ ላይ ያልተሳተፉት የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ድጋፍ ያሻቸዋል። ይህን ድጋፍ ለማግኘት ደግሞ ተጣምረው መንግስት ለመመስረት በዝግጅት ላይ ያሉት ፓርቲዎች ብዙ የማግባባት ስራ ይጠብቃቸዋል።የአሸናፊዎቹ ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግስት ሜርስ ለመንግስት ምስረታ የሚያካሂዱትን ድርድር እስከ መጪው ፋሲካ የመጨረስ ግብ አላቸው።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ