የኦነግና የኦፌኮ የአርማ ዉዝግብ
ሐሙስ፣ ሰኔ 2 2014የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ለኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) በፃፈው ደብዳቤ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጃዋር መሃመድ የኦነግን አርማ በተደጋጋሚ መጠቀማቸውን በመንቀፍ ወቀሳ አቀረበ፡፡
በኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ፊርማ እና ማህተም የወጣው ደብዳቤ እንዳመለከተው አቶ ጃዋር መሃመድ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በህጋዊነት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተመዘገበበትን አርማ በተለያዩ መድረኮች ያለአግባብ ከህጋዊነት ውጭ እየተጠቀሙበት ነው ይላል፡፡
ከትናንት በስቲያ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ተፈርሞበት እና በድርጅቱ ማህተም የወጣውና ለኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የተጻፈው ደብዳቤ፤ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጃዋር መሃመድ የኦነግ አርማን አለአግባብ በመጠቀም ይከሳል፡፡ እንደ ኦነግ ማመልከቻ የኦፌኮ ባለስልጣን አቶ ጃዋር መሃመድ የፓርቲውን አርማ መጠቀም ያቆማሉ ተብሎ ቢጠበቅም ባለማቆማቸው ደብዳቤውን ለመጻፍ መገደዳቸውንም አክለው አብራርተዋል፡፡
ኦነግ በደብዳቤው የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የፓርቲያቸው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጃዋር መሃመድ የኦነግን አርማ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ እንዲያደርጉም ጠይቋል፡፡
ደብዳቤው በማህበራዊ መገናኛ መሰራጨቱን ተከትሎ የኦሮሞ የነጻነት ትግል አርማ ነው ያሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሚጠቀመውን አርማ ማንም ቢጠቀም መከልከል የለበትም በሚል በማህበራዊ ሚዲያ አስተያየታቸውን ያንጸባረቁ በርካቶች ናቸው፡፡ አቶ ለሚ ግን በዚህ ላይ ምላሽ ሲሰጡ አቶ ጃዋር የራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲ አርማ መጠቀም የሚችሉ የፓርቲ አመራር በመሆናቸው ነው ደብዳቤው የተጻፈው ይላሉ፡፡
ከኦሮሞ ነታነት ግንባር የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ለኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ መድረሱን ለዶይቼ ቬለ ያረጋገጡት የኦፌኮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲም ለጊዜው በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ አቶ ሱልጣን የተላከው ደብዳቤ በፓርቲ ሳይሆን በግለሰብ ስም መላኩን ገልጸው፤ ኦፌኮ በአጭር ጊዜ አቋሙን እንደሚገልጽም አመልክተዋል፡፡
ስለጉዳዩ የተጠየቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ከዚህ ጋር ተያይዞ የደረሰው ክስና ማመልከቻ አለመኖሩን ገልጿል፡፡ የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ዮሴፍ መርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አርማ እና ስያሜ በቦርዱ አንቀጽ 86 ላይ በተደነገገው መሰረት ምላሽ እንደሚያገኝ ግን በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር