የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ የአስመራን መንግሥት በትጥቅ ለመታገል ዝግጅት ላይ ነኝ አለ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 22 2017
የኤርትራን መንግሥት ለመጣል ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አንዱ እንደሆነ የገለፀው "የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ" ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ የትጥቅ ትግል ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ።
አፋር ክልል ሰመራ ከተማ ውስጥ ጽ/ቤት መክፈታቸውንና አዲስ አበባ ላይም ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ የገለፁት የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ ቃል ዐቀባይ አሊ መሐመድ ዑመር "የኢትዮጵያ መንግሥት የመንቀሳቀስ እና የመናገር ዕድል ሰጥቶናል" ብለዋል።
ቃል ዐቀባዩ ባለፈው ሳምንት በዋናነት በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ እና ጅቡቲ የሚገኙ አፋሮችን በሚመለከት እና በአካባቢው ቀጣናዊ ኹኔታዎች ዙሪያ ጠለቅ ያለ ውይይት ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መደረጉንና ድርጅታቸውም መሳተፉን ገልፀዋል።
"የኤርትራ አፈር ብሔራዊ ጉባኤ" የሥራ አስፈጻሚ አባል እና ቃል ዐቀባይ አሊ መሐመድ ዑመር ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ አፋር ክልል ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መቀመጫውን ካናዳ ካደረገ ካን-ጎ አፋር ከተባለ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ ውስጥ ያለውን አፋር ታሪኩን፣ የአካባቢውን ቀጣናዊ ደኅንነት እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ በተደረገ ጉባኤ ላይ መሳተፋቸውን ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
የአፋርን ሕዝብ የተመለከቱልዩ ልዩ ገዳዮች በስፋት ውይይት እንደተደረገባቸውም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
"ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ላይ ያደረግነው ውይይት እንዳለ ሆኖ በመቀጠል ደግሞ በ25 ጁላይ እ.አ.አ ሰመራ ላይ ሕዝባዊ ጉባኤ አድርገን ነበር"።
"የኤርትራ አፈር ብሔራዊ ጉባኤ"ከ11 ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ 2014 ስዊድን ውስጥ ተመሥርቶ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ኤርትራ ውስጥ ስላለው "ፈታኝ" ያሉት ኹኔታ ሲያስገነዝብ፣ ሲሰባሰቡም መቆየታቸውን የገለፁት የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና ቃል ዐቀባይ፣ አሁን ወደዚህ የመጡበት ምክንያት ምን እንደሆነም አስረድተዋል።
"አሁን ደግሞ ወደዚህ [የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና] መጥተን እዚህ ካለው የእኛ ሕዝብ እና ድርጅቶች ጋር አብረን ሆነን የትጥቅ ትግል ለማድረግ ዝግጅት እያደረግን ነው"።
2018 ላይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት መሪዎች በኩል ታይቶ የነበረውን መቀራረብ በበጎ ተመልክተን ድጋፋችንንም ሰትተን ነበር ያሉት እኒሁ ግለሰብ፣ እንቅስቃሴው ሕዝባዊና ሕጋዊ መሠረት ይዞ እንዳይቀጥል የኢሳይያስ አፈወርቂ መንግሥት ባለመፈለጉ ስለመሰናከሉ መረጃ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ከፕሪቶሪያ ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት [የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ሕወሓት] በኋላ ዳግም የሻከረው የሀገራቱ ግንኙነት ወደ ጦርነት እንዳያመራ ሥጋታቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ኤርትራ የጦር ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እያስጠጋ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
"ድንበር ላይ ኃይለኛ እንቅስቃሴዎች በከባድ መሣሪያ የታገዘ ሠራዊት አቅርቧል [የኤርትራ መንግሥት] ቡሬ አካባቢ። ስለዚህ አሁንም ወደ ጦርነት የመግባት እና ኢትዮጵያን ሰላም የመንሳት ፍላጎቱ እንደቀጠለ ነው"።
የኤርትራን መንግሥት በኃይል ለመጣልእንደሚንቀሳቀስ በይፋ ያስታወቀው ብርጌድ ንሓመዶ የተባለው የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅት ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ውይይቶችን ሲያደርግ መሳተፋቸውን የገለፁት "የኤርትራ አፈር ብሔራዊ ጉባኤ" የሥራ አስፈጻሚ አባል እና ቃል ዐቀባይ አሊ መሐመድ ዑመር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸውም ነግረውናል።
"አፋር ክልል እንደ አፋር እንደፈለግን የመንቀሳቀስ መብታችን አለ። የኢትዮጵያ መንግሥት የመንቀሳቀስ፣ የመናገር ዕድል ሰጥቶናል። ቢሮም ሰመራ ከፍተናል። አሁን ደግሞ አዲስ አበባ ጽ/ቤት ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንገኛለን። ስለዚህ ጥሩ ግንኙነት አለን [ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር]።"
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተደረገው ውይይት "የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት"ም ተሳትፏል ያሉት አቶ አሊ ዑመር "በኤርትራ የሥርዓት ለውጥ እንዲኖር" በጋራ እንደሚሠሩም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ከፕሪቶሪያው ዘላቂ የግጭት ማቆም ምምነት ወዲህ እና በተለይ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሕልውናዋ ጉዳይ መሆኑን ለዓለም ማሳወቋን ተከትሎ ይበልጥ የሻከረ መስሏል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ