የኤሉክትሪክ ዋጋ የሚጨምረዉ ለትርፍ አይደለም፣ ሕዳሴ ግድብም ተጠናቅቋል-ባለሥልጣን
ሐሙስ፣ ነሐሴ 1 2017
ኢትዮጵያ ውስጥ ለአራትዓመታት በየሦስት ወሩ እየጨመረ የሚሄደው የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸጫ ዋጋ ማሻሻያ "ትርፍን ታሳቢ ያደረገ አይደለም" ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።የኤሌክትሪክ ሽያጭ ተመን "አሁንም ከዋጋው በታች ነው" ያለው ተቋሙ፤ "ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ሕዝብ በማይጎዳ መልኩ" የተሻሻለ ነው ሲል ዛሬ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የሕዳሴ ግድብ ካለምንም የውጭ ብድር በመንግሥት እና ሕዝብ ተሰርቶ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለው ግድቡ የሚመረቅበት ጊዜ ይፋ ከሆነ ወዲህ በግብጽ በኩል በምርቃቱ ላይ እክል ለመፍጠር "ከፍተኛ ሩጫ አለ" ሆኖም "ውጤቱን ሊቀይሩት አይችሉም" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቅርቡ ይፋ ያደረገው የኃይል መሸጫ ዋጋ ተቋሙ የኃይል ማመንጫዎችን፣ ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለመገንባት፣ ጥገናዎችን ለማከናወን የሚያወጣውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል አለመሆኑን ዛሬ ሐሙስ ገልጿል። እንደ ማሳያም ተቋሙ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድሮት የነበረው የ260 ቢሊዮን ብር ዕዳ በመንግሥት መዞሩን ጠቅሷል። የተቋሙ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንዳሉት "የኤሌክትሪክ ኃይል ለሕዝብ ይቀርብ የነበረው በኪሳራ ነበር"
"የምናቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል አሁንም ከዋጋው በታች መሆኑን ነው የሚያሳየው። አሁን ያደረግነው ጭማሪ ምንም ትርፍ ሳይታሰብበት ዋጋን ብቻ እንዲመልስ ታሳቢ በማድረግ ነው የተሠራው።"
የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ 20 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ የማምረት አቅሙ 7 ሺህ 910 ሜጋ ዋት መሆኑን ገልጿል። በዚህ ምክንያት 46 በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኤሌክትሪክ የማያገኝ ከመሆኑም በላይ መቆራረጡ አሁንም ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ያለ የጋራ ችግር ነው ብለዋል ኃላፊው።
"ችግር አለ እውነት ነው። ይህንን ለመቅረፍ በጋራ እየሠራን ነው።"
43 የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ማማዎች በስርቆት ምክንያት መውደቃቸው፣ በፀጥታ ችግር ምክንያት ተንቀሳቅሶ መገንባት፣ መጠገን አለመቻል ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት መሆናቸውም በዚሁ ወቅት ተጠቅሷል። የሕዳሴ ግድብ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ደጋግመው ስለሰጡት ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ አድርገናል የሚል አስተያየትም ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
"በዋናነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል ለዚህ ግድብ መሳካት። አብዛኛውን ተቋሙ [ኤሌክትሪክ ኃይል] ተበድሮ ሲሠራ የነበረው ከንግድ ባንክ በመበደር ነው። ያን ብድር ዕዳ መክፈል ባለመቻላችን መንግሥት እንዳላ የተቋሙን ወደ 260 ቢሊየን ብር አጠቃላይ የተቋሙን ዕዳ ሲወስድ ወደ መንግሥት ዞሯል። ስለዚህ ግድቡ የተገነባው በመንግሥት ነው።"
የግድቡ የመመረቂያ ጊዜከተገለፀ ጀምሮ በግብጽ በኩል "እክል የመፍጠር" እንቅስቃሴ መኖሩንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ተናግረዋል።
በዓመቱ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ወይም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጭ (ለኬንያ እና ለጅቡቲ) ገበያ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 75 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ተቋሙ አስታውቋል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ