የኢትዮጵያውያን የባህልና ስፖርት ፌስቲቫል በሲያትል
ረቡዕ፣ ሰኔ 25 2017
አምና እዚህ አትላንታ ጆርጂያ ተካሄዶ የነበረው፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ዐውድ ትርዒት ዘንድሮ ወደ ሲያትል አምርቷል። ፌስቲቫሉ፤ በየዓመቱ በጉጉት ከሚጠበቁት የእግር ኳስ ውድድሮች በተጨማሪ ፣በተለያዩ ባህላዊ ትርዒቶች፣ ኢትዮጵያውያንን ከመላው ዓለም በአንድ ስፍራ አሰባስቦ ለአንድ ሳምንት ያህል ይዘልቃል።
የመክፈቻ ስነ ሥርዓቱ
ይህንን ፌስቲቫል አዘጋጅታ እንግዶቿን የተቀበለችው ሲያትል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ግዛት የፓስፊክ ሰሜን ምዕራብ ክልል ውስጥ በሕዝብ ብዛት ቁጥሯ የምትታወቅ ደማቅ ከተማ ናት። በሲያትል፣ የመክፈቻው ስነስርአት ምን ይመስል እንደነበር፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ዐቢይ እንደሚከተለው ገልጸውታል።
«በሲያትል ከተማ የያዝነው ስቴዲየም፣ ከሲያትል ዳውንታውን ከ30 እስከ 25 ደቂቃ ወጣ ብሎ ያለ፣ የሕዝብ ትምህርት ቤት ነው። በጣም ግሩም፣ ጥሩ የሆነ አዲስ የተሰራ ስቴዲየም ውስጥ ነው ያዘጋጀነው። የምንሠራው ከሁለቱ የሲያትል ዳሸን እና የሲያትል ባሮ ቡድኖች ጋር በመተባበር ነው። በመክፈቻው ስነስርአት ላይ፣ 32ቱም ቡድኖች ተገኝተው፣ የክብር እንግዶችም ተገኝተው፣ የኮሚኒቲ የመሪዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት አገልጋዮች በሙሉ በተገኙበት ተከፈተ።»
የኢትዮጵያን ባህልና ቅርስ ለማስተዋወቅና አዎንታዊ አስተሳሰብን ለመገንባት የቋቋመው፣የኢትዮጵያውያን ባህልና ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፣ መቻቻልና በጋራ መሥራትን መመሪያው አድርጓል። የዘንድሮው በዓል የተዘጋጀውም « ኢትዮጵዊነት አንድነት'» በሚል መርህ ነው።
ልዩ የድሮን ትርዒት
ይህንኑ የፌዴሬሽኑ መርህ መሰረት ያደረገና በተለይ ደግሞ የሰላም አስፈላጊነትን ያመለከተ፣ የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎችንም የዘከረ ልዩ የድሮን ትርዒት በዝግጅቱ ላይ መቅረቡን አቶ ዐቢይ ተናግረዋል።
«ይኼ የድሮን ትርዒት፣ ስለሰላም፣ስለ ዝግጅታችን፣ በጂጂ ላይ ያተኮረና በበለጠ ደግሞ የቀድሞ ነገሥታትን፣ ኢትዮጵያን ያኮሩ፣ ኢትዮጵያን የጠበቁ መሪዎቻችንን የሚያሳይ የድሮን ትርዒት ነበር።የአክሱም ሐውልትን፣ የላሊበላን፣ የፋሲል ግንብን፣ እንደዚሁም ሌሎችም የሚታዩበት በጣም ግሩም የሆነ፣ ደማቅ የመጡትን ሰዎች በሙሉ የሚያስደስት የድሮን ትርዒት ተደረገ።»
የኢትዮጵያ ቀን
ከዚህ በተጨማሪ፣ ፌዴሬሽኑ የፊታችን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም በሚያካሄደው፣ የኢትዮጵያ ቀን ላይ ከኢትዮጵያና ከዩናይትድ ስቴትስ የተጋበዙ አርቲስቶች የሚሳተፉበት የሙዚቃና የባህል ትርዒት እንደሚያካሂድ ይጠበቃል። ፌዴሬሽኑ ባለፉት ዓመታት፣ ባዘጋጃቸው የስፖርትና የባህል ፌስቲቫሎች ላይ፣ የተለያዩ ዕውቅ ኢትዮጵየውያንን፣ በዝግጅቱ ላይ እንዲገኙ በክብር እንግድነት ይጋብዛል።
ከነዚሁ ተጋባዥ እንግዶች መኻከል፣ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን፣ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ አትሌት ምሩፅ ይፍጠር፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ሙላቱ አስታጥቄና አባባ ተስፋዬ ሣህሉ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። ዘንድሮስ?
«ከኢትዮጵያ የመጡት የክብር እንግዳ፣ አቶ ዘነበ አርጋው፣በልዩ ስም ቮልቮ የሚባሉት፣ የቀድሞ የአየር ኃይል የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች፣ ለብሔራዊ ቡድን ከመጫወታቸው በፊት ደግሞ፣ ወደፊት የሚባል እና መድን ድርጅት ውስጥ፣ ለረጅም ዓመት በተጫዋችነትም በአሠልጣኝነትም የሚታወቁ ናቸው»
የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌዴሬሽን፣ የዛሬ 42 ዓመት፣ አራት ቡድኖችን ይዞ ነበር የተመሰረተው። እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ1984፣ ቴክሳስ ሂውስተን ውስጥ ፌዴሬሽኑን የመሰረቱት እነዚህ ቡድኖች ሂውስተን፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ዳላስና አትላንታ ናቸው።
ታሪኩ ኃይሉ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ