የኢትዮጵያና የኤርትራ አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ሕዝብ ግንኙነት
ማክሰኞ፣ ሰኔ 17 2017
ኢትዮጵያን በትግራይ ክልል በኩል ከኤርትራ ጋር በሚያዋስነዉ ድንበር ግራና ቀኝ የሚኖሩት የሁለቱ ሐገራት ዜጎች 'የህዝብ ለህዝብ' የተባለ ግንኙነት መጀመራቸዉ ተነገረ።የሁለቱ ሐገራት ሕዝብ ግንኑነት የአዲስ አበባና የአሥመራ መሪዎች ግንኙነት በጠብና በፍቅር በተለዋወጠ ቁጥር እየደፈረሰ ይጠራል።የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ግንኙነት መሻከሩ በግልፅ በሚነገርበት ባሁኑ ወቅት ግን ሳላንበሳ ዉስጥ «የሠላም» የተባለ መርሐ ግብር ባለፈዉ ዕሁድ መደረጉ ተነግሯል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲነት ያገደዉ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ግንኑነቱን እንደሚደግፍ አስታዉቋል።
በትግራይ እና ኤርትራ በኩል ባሉ አስተባባሪዎችተነሳሽነት ባለፈው እሁድ በዛላንበሳ ከተማ የተደረገው በድንበር አካባቢዎች የሚገኙ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች የተገናኙበት መርሀግብር ከትግራይ እንዲሁም ከኤርትራ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በኤርትራ ታዋቂ የሚባሉ አክቲቪስቶች እንዲሁም ሌሎች በርካቶች የታደሙበት እንደነበረ ተገልጿል።
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓመተምህረትም እንዲሁ በትግራይ ራማ በኩል እንዲሁም በኤርትራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ የሁለቱ ዜጎች ሰላማዊ ግንኙነት የሚያስጀምር የተባለ መርሀግብር ማድረጋቸው ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምተናል።
እነዚህ 'ፅምዶ' በሚል ስያሜ በድንበር አካባቢዎች የሚደጉ ግንኙነቶች በጦርነቶች ምክንያት ቆሞ የቆየ የሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ሰላማዊ ግንኙነት ለመመለስ ያለመ ነው ተብሎ በአስተባባሪዎች በኩል ይገለፃል። የትግራይ ክልል ራማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና ባለፈው ሳምንት የተደረገው የህዝብ ለህዝብ የተባለ ግንኙነት ካቀናጁት መካከል የሆኑት አቶ ሓዱሽ ጎበዛይ፥ በሁሉቱ ህዝቦች መካከል ያለው መራራቅ ለመፍታት ያለመ ግንኙነት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በትግራይ በኩል ባለው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር አካባቢዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግንኙነቶች እየተደረጉ እንዳለ እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግድ ጭምር እንደሚታዩ ከመረጃ ምንጮቻችን ሰምተናል። እነዚህ ግንኙነቶች ህወሓት የኤርትራ እና ትግራይ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማለት እውቅና የሰጠው ሲሆን፥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም ከሌሎች ከትግራይ ጋር የሚዋሰኑ ህዝቦች እንዲቀጥል እንደሚሰራ ገልጿል። የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል "ፓርቲያችን ህወሓት በዚህ ወቅት በኤርትራ እና ትግራይ ህዝቦች መካከል እየታየ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም ተመሳሳይ ግንኙነት ከሌሎች ጎረቤት ህዝቦች ጋር ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ አስፈላጊ የተባለ ጥረት እንደምናደርግ ለማረጋገጥ እንወዳለን" ብለዋል።
ይህ 'ፅምዶ' በሚል ስያሜ የሚደረግ ግንኙነት ከጀርባ ህወሓት የሚገፋው፣ የሀገሪቱ ሕግ በጣሰ መልኩ ከሌላ ሀገር ጋር የሚደረግ ግንኙነት በማለት አስተያየቶች የሚሰጡ ሲሆን ይህ የማይቀበሉት በራማ በኩል የተደረገው የድንበር አካባቢ ህዝቦች ግንኙነት አስተባባሪው እንዲሁም የድንበር ከተማዋ ራማ ነዋሪው አቶ ሓዱሽ ጎበዛይ፥ እየተደረገ ያለው የድንበር ነዋሪዎች ማሕበራዊ ግንኙነት ነው፣ ይህ ሕጋዊ እና ተቋማዊ ለማድረግ መንግስት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙርያ ያነጋገርናቸውየሕግ ባለሙያው አቶ ዳዊት ገብረሚካኤል በበኩላቸው "ሕገመንግስታችን መሰረት አንድ ክልል ከሌላ ሀገር የመገናኘት ስልጣን የለውም። ክልሎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ሊገናኙ ይችላሉ፣ ከዚህ ውጪ ከሌላ ሀገር ጋር ግን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ብቻ ነው የሚደረገው። ይሁንና አሁን እየተደረገ ያለው ግንኙነት በይፋ አንድ የክልል አስተዳደር ከሌላ ሀገር ጋር አይደለም። ይህ 'ፅምዶ' እየተባለ እየተደረገ ያለው ግንኙነት በአክቲቪስቶች የተጀመረ፣ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ድንበር አካባቢ ያለ ህዝብ የወረደ ነው። ይህ ህዝብ ደግሞ ተመሳሳይ ሆኖ ይሁንና በፖለቲከኞች አሻጥር የተራራቀ ነው። ይህ የህዝቦች ግንኙነት የሚከለክል ሕግ የለም" ይላሉ።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና ህወሓት የኤርትራ ጦር የትግራይ ግዛቶች ይዘው ይገኛሉ፣ ከያዝዋቸው አካባቢዎች ይውጡ ሲሉ ቆይተዋል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ሲወያዩ በትግራይ ሕገመንግስታዊ ጥሰቶች እየታዩ ነው ሲሉ ሲከሱም ተደምጠዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር