እንወያይ፤ የኢትዮጵያና ኤርትራ የቃላት ጦርነት ወዴት ያመራል?
እሑድ፣ የካቲት 23 2017
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከዚህ ቀደም ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ የባሕ ተጠቃሚነት መወያያ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባው፤ ይህ በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆን አንዳለበት ገልጸዋል። የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሑሴንም «የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ትክክለኛው ጊዜ በአጼ ሚኒሊክ ጊዜ እንደነበር ጠቅሰው በአጼ ሃይለስላሴ፣ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን ያልተሳካው ይህ ጉዳይ የሚሳካበት ጊዜ አሁን አው» ሲሉ ተደምጠዋል።
በቅርቡ የቀድሞው ፕሬዝዳንት እና የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ "ልዩ መልዕክተኛ" ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በአልጀዚራ ላይ ያጋሩት ጽሁፍ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአሁኑ ወቅት በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ እና በአማራ ክልል ውስጥ ሚሊሺያ እንዲፈጠር አድርገዋል በማለትም የከሰሱም ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን እያስገቡ መሆናቸውን በጽሁፋቸው ወቅሰዋል።
ይህንን ክስ በተመለከተ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ምንጭ ከውጭ እንደመጣ ማድረግ እና ኤርትራን መሸሸጊያ የሚያደረግ ነው በማለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ድርጊቱን ተቃውመው ጽፈዋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት «ባለፉት ወራት በአሥመራ ላይ ምክንያት የለሽ እና የተጠናከረ የትንኮሳ ዘመቻ ከፍቷል» በማለትም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ፤ ቀጣናውን "የከበቡት" ችግሮች "መፍለቂያ እና ማዕከል ናት" ሲሉ የከሰሱት ሚኒስትሩ አገራቸው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል።
የኤርትራ መንግሥት የቀድሞ የሠራዊት አባላት ወደ የክፍሎቻቸው ለዳግም ሥልጠና እንዲመለሱ እና ሌሎችም ከአገር ለመውጣት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች እንዳጠበቀ በኤርትራ ውስጥ እና በውጪ ሀገራት የሚገኙ የአገሪቱ ዜጎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ መመሪያ መሠረት ከ60 ዓመት በታች የሚገኙ በኤርትራ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ ዜጎች ተመዝግብው ወደ ማሠልጠኛ እንዲገቡ፤ እንዲሁም ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ደግሞ ተገቢውን ፈቃድ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳያገኙ ከአገር እንዳይወጡ ትዕዛዝ መተላለፉንም ታውቋል።
በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተነፈገው በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ከኤርትራ መንግስት ጋር ግኑኝነት እያደረገ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህን አስመልክተው የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር የአሁኑ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ሚኒስትር ዶክተር አብርሃ በላይ በቅርቡ ለፋና ብሮድካስቲንግ የትግርኛ ክፍል በሰጡት መግለጫ «ሻዕብያ ለትግራይ ሕዝብ ዕርባና ይኖረዋል ብሎ ማሰብ አደለም ለቀድሞዎቹ ትውልዶች የአሁኑ ትውልድም ይህ እንዳልሆነ በአይኑ አይቶታል። ስለሆነም የሚደረገው ግኑኝነት ለሰላም ሊሆን አይችልም። ፕሪቶሪያ ላይ ስንስማማ «ሻዕብያ» ምላሹኮ ይታወቅ ነበር። በሐገራችን ሰላም እንዳይኖር የሚሰራ፤ ሰላም በመፈጠሩም የተናደደ፤ አጀንዳዎቼን አልጨረስኩም ብሎ የሚያምን ሃይል ነው። ከ«ሻዕብያ» ጋር የሚደረግ ግኑኝነት እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን እጃቸውንም መሰብሰብ አለባቸው።» ብለዋል።
እየተጋጋመ ያለው የኢትዮጵያና የኤርትራ የቃላት ጦርነት ወዴት ያመራ ይሁን? የዛሬ የውይይታችን ርዕስ ነው።
የማዳመጫ ማዕቀፉን በመጫን ሙሉ ዝግጅቱን እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጋብዛለን።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር