የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማህበር ጥያቄ
ዓርብ፣ ሰኔ 27 2017በማህበሩ ላይ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ
የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ማህበር በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ገደብ ተጥሎበታል ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መለሰ ባታ፤ ለማህበሩ ከእንቅስቃሴ ታግዶ እስካሁን መዝለቅ የተለያዩ ምክንያቶች መጠቀሳቸውን ጠቁመዋል፡፡ “ከላይ ጫና መጥቶብኛል በሚልና አንዳንድ ምክንያቶችንም በመጥቀስ ነው ማህበሩ የታገደው” ያሉት አቶ መለሰ ማህበራቸው ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴው ለመመለስ ግን አሁንም እየታገለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለማህበሩ መታገድ የሲቪል ባለስልጣኑ የሰጠውን አስተያየት አቶ መለሰ አልተቀበሉትም
“በምክንያትነት የተቀመጠው ተጨባጭ ጉዳዩ ከኛ አንጻር ውሃ የሚያነሳ አይደለም፤ ሀሰተኛ ማህተም ተጠቅማችኋል ጠቅላላ ጉባኤ አላካሄዳችሁም የሚል ነው” በማለት መሰል ቴክኒካል ችግሮች እንኳ በማህበሩ ውስጥ ብስተዋሉ አንድ ማህበር ሲታገድ በየደረጃው ማስጠንቀቂያ እንኳ ይሰጣል እንጂ በቀጥታ ማህበሩን ከስራ ማስቆም በአግባብነት የሚወሰድ አይደለም የሚለውን አስቴየት ሰጥተዋል፡፡ ማህበሩ ስህተቱን የሰራው ከአንድ ዓመት በፊት ነው በሚል ክሱ መቅረቡንም የገለጹት አቶ መለሰ ማህበሩ ስህተቱን በሰራበት በዚያ ወቅት መቅጣት ወይም እርምጃ መውሰድ አሊያም የማስተካከያ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ ሲገባ ዛሬ ላይ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ባነሱበት ሰዓት የተወሰደው እርምጃ አግባብነቱን እና የቀረበውን ክስ ተጨባጭነቱንም ማህበሩ እንዳልተቀበለው አስረድተዋል፡፡
የማህበሩ በትላልቅ ውይይቶች ላይ አለመጋበዝ
በመሰል ጉዳዮች ሳቢያ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከጤና ባለሙያዎች ጋራ ውይይት ስያደርጉም በመድረኩ ያልተሳተፈው የባለሙያዎቹ ማህበር በመድረኩ ባለመገኘቱ ቅሬታ እንደተሰማው የገለጹት የማኅበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ብገኙ ግን ሊያነሷቸው የሚችሉትን ጥያቄዎች ጠቁመዋል፡፡ “እንደ ተቋም ስንቋቋምም የማለሙያውን ጥያቄ ቀለል ባለ መልኩ ለመንግስት የማቅረብና ማህበሩን ጠንካራ እና ተሰሚ ማድረግ ነበር” ያሉት አቶ መለሰ እንደ ማህበር ሊያነሱ የሚችሉትም ጥያቄ የባለሙያውን ወቅታዊ አንገብጋቢ የዳቦ ጥያቄ በአጭር በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ እቅድ መልስ የሚያገኝበት ተጨባጭ ሃሳብ ላይ ልሰጥ የሚችለውን መልስ ነው በማለት ጥያቄ የሚያነሳውን አካል ማህበር ከተሳትፎ ማገድ ለጥያቄው የተሰጠው አነስተኛ ስፍራን ያሳያል በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
የባለሙየዎቹ ጥያቄ ተመልሷልን?
ማህበሩ እስካሁን ባለው ሂደት በመንግስት በኩል የባለሙዎቹን ጥያቄ በውል መገንዘብ መቻሉ እንደበጎ እምርታ ቢታይም ጥያቄው ግን በተገቢው ሁኔታ ተመልሷል የሚል እምነት የለውም፡፡ “የጥያቄውን አግባብነት ሁሉም (ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የጤና ሚኒስቴሩ) እንደተረዱት እናስባለን” ያሉት አቶ መለሰ ነገር ግን “ጥያቄውን ለመፍታት የተከሄደበት” ባሉት መንገድ ደስተኛ አለመሆናቸውንና ባለሙያዎቹ ተጨባጭ መልስ አግኝተዋል በሚለው እምነት የለም ነው ያሉት፡፡
በተለየ መልኩ ከዚህ በፊት ከመምህራን እና ጤና ባለሙያዎች የተነሳውን የደመወዝ ጥያቄን በተመለከተ ትናንት ከህዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ይህን ብለዋል፤ “እዳውን ተቀብለናል እኛ ዋጋ ከፍለን ልጆቻችን እንዳይለምኑ እናድርግ” በማለት ቅድሚያ ጠቅላላ አገራዊ እድገቱ ላይ እንዲተኮር እንደሚሹ አስረድተዋል፡፡
የባለሙያዎቹን ጥያቄ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እያደረጉት ነውን?
የጤና ባለሞያዎቹ ጥያቄንበተመለከተም የጥያቄውን አግባብነት ያረጋገጡት ዐቢይ፤ ጥያቄውን ለፖለቲካ ዓላማ ለማዋል ያሹት ግን ስለመኖራቸው ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት የጤና ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ መለሰ፤ “እኛ የጋበዝነው የፖለቲካ አካል የለም” በማለት ባለሙያው ሌላ አካል ይህን መጠቀሚያ ለማድረግ ብጥር እንኳ ተጠያቂ መሆን እንደማይገባውና የጤና ባለሙያውን ጥያቄ ወደሌላ አቅጣጫ መውሰድ አግባብነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡
ማህበሩ ከእንቅስቃሴ በተገታበት ባሁን ወቅት የባለሙያዎች እስር አልቆመም የሚሊት አቶ መለሰ ማህበሩ አሁንም ቢሆን ከሲቪል ባለስልጣኑ ጋር በመነጋገር ወደ መደበኛ ስራውን መመለስ እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡ “ቴክኒካዊ ችግሮች ተፈጥረዋል ከተባለ ከባለስልጣኑ ጋር ተነጋግረን ለመፍታት ዝግጁ ነን” በማለትም ተቋሙን ለማስቀጠል የትኛውም ጫና ተቋቁመው መቀጠል እንደሚፈልጉም ገልጸዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ስለሚያቀርበው የተጣለበት የእንቅስቃሴ ገደብ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በተለይም ከባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በስልክ እና በጽሁፍ ያቀረበላቸው ጥያቄ ለዛሬ መልስ አላገኘም፡፡ የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴን ከሚመሩት የጤና ባለሙያዎች ማካከል ከሰሞኑ በባህርዳር የታሰሩት ዶ/ር ዳኒኤል ፈንታነህ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲል ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት አሚኔስቲ ኢንተርናሽናል ጠይቋል፡፡ ከዚህ በፊት ዶ/ር ማህሌት ጉዑሽን ጨምሮ የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳት ዮናታን ዳኛው ታስረው ከተለቀቁት መካከል መሆናቸው ይታወሳል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ