የኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ከ1997 ምርጫ ወዲህ ከወዴት አለ?
እሑድ፣ ግንቦት 10 2017የኢትዮጵያ ሦስተኛ የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ከተካሔደ 20 ዓመታት ደፈነ። ግንቦት 7 ቀን 1997 የተካሔደው እና ከ27 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ድምጽ የሰጡበት ምርጫ ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ከተካሔዱት ሁሉ ጠንካራ የተቃዋሚዎች ተሳትፎ የታየበት ነው። ኢሕአዴግ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለመክፈት መወሰኑ፤ ተቃዋሚዎች ተበታትነው ከመወዳደር ይልቅ ጥምረቶች መመሥረታቸው፤ የጋዜጦች እና መጽሔቶች መስፋፋት ለታየው ጠንካራ የምርጫ ውድድር አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ያዘጋጃቸው የነበሩ እና የመንግሥት ባለስልጣናት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ፊት ለፊት ያደረጓቸው ክርክሮች በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ መተላለፋቸው በድምጽ ሰጪዎች ዘንድ መነቃቃት ፈጥረዋል። የሲቪክ ማኅበራት ስለ ምርጫ ያከናወኗቸው የአድቮኬሲ ሥራዎች ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል።
ይሁንና የምርጫው ሒደት የተጠናቀቀው በመንግሥት ደም አፋሳሽ እርምጃ እና በተቃዋሚዎች እስር ሆኖ በበጎ የሚታወስ አልሆነም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ መንግሥት ለአንድ ወር ሰልፍ እና ከቤት ውጪ የሚደረግ ሕዝባዊ ስብሰባ የሚያግድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን ጸጥታ አስከባሪዎች ሰኔ 1 ቀን 1997 በወሰዱት እርምጃ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እስር እና በውስጣቸው የተከሰተው መከፋፈል ከ1997 በኋላ በተካሔዱት ምርጫዎች ላይ ጭምር ያጠላ ተጽዕኖ ነበረው።
ከ20 ዓመታት በኋላ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ እና ተቃዋሚዎች የሚገኙበት ሁኔታ ግን እጅግ የተራራቀ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብልጽግና ፓርቲ 15 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት አስታውቋል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)ን በብልጽግና ፓርቲ የተካው “ለውጥ” ካነቃቃቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት አሁን የመከፋፈል ዕጣ ገጥሟቸዋል። በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ሰባተኛውን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ በ2018 ታካሒዳለች ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለት እንግዶች የተሳተፉበት የእንወያይ መሰናዶ የኢትዮጵያን የፓርቲ ፖለቲካ ህልውና ከ1997 ወዲህ እና በሚቀጥለው ዓመት ሊካሔድ ከታቀደው ምርጫ አኳያ ይዳስሳል። ዶክተር ብዙነህ ጌታቸው በሰሜን አየርላንድ ዋና ከተማ ቤልፋስት በሚገኘው ኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህር ናቸው። ዶክተር አዲሱ ላሽተው በካናዳ ማክማስተር ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር እና በብሮኪንግስ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙ ናቸው።
ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ