የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለዕዳ ሽግሽግ ድርድር እንዲዘጋጁ ገንዘብ ሚኒስቴር አሳሰበ
ረቡዕ፣ መጋቢት 17 2017ገንዘብ ሚኒስቴር “ዋና ዋና” ላላቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኢትዮጵያ ከኦፊሲያል አበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር ሥምምነት ላይ መድረሷን ተከትሎ መንግሥት ለዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ስለሚያደርገው ጥረት ማብራሪያ ሰጥቷል። ማብራሪያውን የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ናቸው።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ ማብራሪያው ሲሰጥ መገኘታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ መጋቢት 17 ቀን 2017 በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይፋ ያደረጋቸው ምስሎች አሳይተዋል።
ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር በተጣጣመ መንገድ ከአበዳሪ መንግሥታት ጋር ለሚደረገው የመግባቢያ ሥምምነት ድርድር እንዲዘጋጁ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ማሳሰባቸውን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ ጉዳይ ላለፉት አራት ዓመታት ሲጠበቅ የነበረ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሁለት ዓመታት በፊት ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ ነበራቸው። ኢትዮጵያ በ2014 ብቻ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ከፍላለች። የዕዳው መጠን እና የመክፈያ ጊዜ መደራረብ ሀገሪቱን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ጥሏታል።
ዐቢይ በመጋቢት 2015 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት “በሚቀጥሉት ስድስት ሰባት ወራት ተስፋ የምናደርጋቸው መሸጋሸጎች አሉ” ቢሉም በጠቀሱት ጊዜ ውስጥ አልተከወነም።
ቢያንስ “በመርኅ ደረጃ” ከኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር ከሥምምነት ለመድረስ መንግሥታቸው ሁለት ዓመታት መጠበቅ ነበረበት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 11 ቀን 2017 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሲሰጡ የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና በማቃለል ረገድ “አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያመጣ” ለውጥ መኖሩን ተናግረዋል።
ከመንግሥታቸው “የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የዕዳ ሽግሽግ ለማካሔድ ባለፉት ወራት” ድርድር ሲያካሒድ መቆየቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አሁን ወደ መቋጫው ደርሷል” ሲሉ ተደምጠዋል። “በዕዳ ሽግሽግ ኢትዮጵያ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ save አድርጋለች” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የ8.4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የዕዳ አከፋፈል ለማሸጋሸግ ከኦፊሴያል አበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር “በመርኅ ደረጃ” ከሥምምነት ላይ መድረሷን ገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው አርብ አስታውቋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ሥምምነቱ “ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት” መንግሥታቸው በሚያደርገው ጥረት “ትልቅ ምዕራፍ” እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በሰኔ 2016 የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ዕዳ በአጠቃላይ 66.8 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የገንዘብ ሚኒስቴር ሰነድ ያሳያል። ከዚህ ውስጥ 29 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚሆነው የውጪ ዕዳ ነው። ገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ጥር ይፋ ባደረገው ሰነድ መሠረት 52 በመቶው የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ 28.31 በመቶ የመንግሥታት የቀረው የግል አበዳሪዎች ድርሻ ነው።
ዓለም ባንክ በታኅሳስ 2016 ይፋ ያደረገው ሰነድ በአንጻሩ በጎርጎሮሳዊው 2023 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጪ ዕዳ ክምችት 33 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መድረሱን አሳይቷል። በዓለም ባንክ ሰነድ የተጠቀሰው አሃዝ ከገንዘብ ሚኒስቴር በአራት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የላቀ ነው። በሰነዱ መሠረት ኢትዮጵያ ዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተበደረችው 14 ቢሊዮን ዶላር ከውጪ ዕዳዋ ወደ 48 በመቶ ድርሻ ይይዛል። ከምዕራባውያን እና ቻይናን ከመሳሰሉ ሀገራት የተበደረችው ከውጪ ዕዳዋ 35 በመቶ ገደማ ድርሻ አለው።
ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የተበደረችው ገንዘብ የሚከፈልበት ወለድ “ዝቅ ያለ” ከመሆኑ ባሻገር የልማት ድርጅቶች በመሆናቸው አከፋፈሉን በተመለከተ መደራደር ይቻላል። ይሁንና ኢትዮጵያ ከመንግሥታት የተበደረችው “የወለድ ምጣኔው ከፍ ያለ” እንዲሁም “ጥብቅ የሆኑ የመክፈያ ጊዜያት” ያሉት በመሆኑ ፈታኝ ያደርገዋል።
ኢትዮጵያ በመርኅ ደረጃ ከሥምምነት የደረሰችበት የዕዳ ሽግሽግ በቀጥታ የሚመለከተው ከመንግሥታት የተበደረችውን ነው። ቻይናን ጨምሮ የኢትዮጵያ አበዳሪ መንግሥታት “ጊዜያዊ የዕዳ ክፍያ እፎይታ” ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ እና የአበዳሪዎች ኮሚቴ “በመርኅ ደረጃ” የደረሱበት ሥምምነት በመግባቢያ ሥምምነት የበለጠ ተብራርቶ መደበኛ እንደሚሆን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ተግባራዊ የሚሆነው ከእያንዳንዱ የአበዳሪዎች ኮሚቴ አባላት ጋር በሚፈጸም የሁለትዮሽ ሥምምነት ይሆናል። ይህ ኢትዮጵያ ለአራት ዓመታት ገደማ የጠበቀችው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲሆን ምን ያክል ጊዜ ሊወስድ ይችላል? የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው። ዶክተር ቀልቤሳ “በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም” ይበሉ እንጂ ሒደቱ ያለበት ደረጃ “በጣም አዎንታዊ” እንደሆነ ያምናሉ።
የፓሪስ ክለብ አባል በሆኑ እና ባልሆኑ የኢትዮጵያ አበዳሪዎች መካከል “ጥሩ መናበብ አለ” የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ ኮሚቴውን በተባባሪ ሊቀ-መንበርነት የሚመሩት ፈረንሳይ እና ቻይና “ኢትዮጵያን ለመርዳት ጥሩ ፍላጎት” እንዳላቸው ተናግረዋል። ይህ አንድም ከራሳቸው ከአበዳሪዎቹ ጥቅም የሚመነጭ ነው።
ያበደሩት “ገንዘብ እንዲከፈላቸው የሚፈልጉ ከሆነ ሀገሪቱ ለመክፈል የምትችልበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ማድረግ ይኖርባቸዋል” የሚሉት የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪው በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የደሐ ሀገራትን የዕዳ ጫና ለማቃለል የተጀመረው ጥረት እንዲሳካላ ከአበዳሪዎች ዘንድ ያለው “ዓለም አቀፍ ቁርጠኝነት” ተጨማሪ ገፊ ምክንያት እንደሚሆን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ እና የአበዳሪዎች ኮሚቴ የተስማሙበት የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ከሚያበድርበት የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር ጋር የተያያዘ ነው።
በአይ.ኤም.ኤፍ. መርሐ-ግብር ማዕቀፍ ኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሥራ ላይ በሚቆይበት ጊዜ መክፈል የሚጠበቅባትን 3.5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ክፍያ የሚቀንስላት ድርድር ከውጪ አበዳሪዎቿ ጋር ታካሒዳለች። ድርድሩ የሀገሪቱን የዕዳ ጫና በሒደት ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ ጭምር የታቀደ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር መግለጫ ይጠቁማል።
በመግለጫው መሠረት ከአበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር የተደረሰው ሥምምነት በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ2023 እስከ 2028 ባሉት ዓመታት ለኢትዮጵያ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የዕዳ ክፍያ እፎይታ ይሰጣል።
በኢትዮጵያ እና በአበዳሪዎቿ መካከል “የተወሰኑ አከራካሪ ሁኔታዎች መፈጠራቸው አይቀርም” የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ “መንግሥት [ከዕዳው] የተወሰነ እንዲሰረዝለት ሊፈልግ ይችላል” የሚል ዕምነት አላቸው። ሀገሪቱ ለተበደረችው ገንዘብ የምትከፍለው ወለድ፤ የመክፈያ ጊዜ እና ሌሎች “ቴክኒካል ነገሮች” በኢትዮጵያ እና በአበዳሪ መንግሥታት መካከል በሚደረግ ድርድር “ሥምምነት ላይ ለመድረስ ጊዜ ይወስዳሉ” በማለት ዶክተር ቀልቤሳ ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል።
በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል እንደ ቻድ ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ እንዲደረግላት ጥያቄ ያቀረበችው ጥር 26 ቀን 2013 ነበር። በቻይና እና በፈረንሳይ ተባባሪ ሊቀ-መንበርነት የሚመራው የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ የተቋቋመው በመስከረም 2014 ነው።
ዛምቢያ እና ጋና ዘግይተው መርሐ-ግብሩን የተቀላቀሉ ሲሆን የአራቱ ሀገሮች የብድር ሽግሽግ ጥያቄ በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሦስቱ ሀገሮች ከኦፊሴያል አበዳሪዎቻቸው ጋር የመግባቢያ ሥምምነቶች ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ በአንጻሩ የጦርነት እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዳፋ ተጨምሮበት ዘገምተኛው የቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ አንዳች ውጤት ላይ ለመድረስ ላለፉት አራት ዓመታት ሲጓተት ቆይቷል።
ሒደቱ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የብድር መርሐ-ግብር እንደ ቅድመ-ሁኔታ ያስቀመጠ በመሆኑ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርጋቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አሁን ለደረሰበት አስተዋጽዖ እንዳለው ዶክተር ቀልቤሳ ይናገራሉ። “ከብዙ መጓተት በኋላ አንድም እዚህ ላይ የተደረሰው ባለፈው ዓመት በተለይ መንግሥት [የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች] ተግባራዊ ወደ ማድረግ በመግባቱ ነው” የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ ማሻሻያዎቹ ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ለሕዝቡ አስቸጋሪ ቢሆኑም “ለአበዳሪዎች ትንሽ መታመኛ ሰጥቷቸዋል” የሚል ዕምነት አላቸው።
ኢትዮጵያ እና የኦፊሴያል አበዳሪዎቿ የደረሱበት ሥምምነት ከሌሎች የንግድ አበዳሪዎች በተለይም ከቦንድ ባለቤቶች ጋር የሚደረገውን ድርድር እንደሚደግፍ የገንዘብ ሚኒስቴር እምነቱን ገልጿል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ኢትዮጵያ በ2007 የሸጠችውን ቦንድ ባለቤት ለሆኑ የግል አበዳሪዎች የሚከፍለውን ወለድ በታኅሳስ 2016 አቁሟል።
የዐቢይ መንግሥት፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የቦንድ ባለቤቶች ኢትዮጵያ የገጠማት የዕዳ ጫና የመክፈያ ጊዜ በማራዘም የሚፈታ የአጭር ጊዜ የገንዘብ እጥረት ወይስ የወሰደችውን ብድር ለመቀነስ የሚያስገድድ የመክፈል ችግር በሚለው ረገድ መሠረታዊ ልዩነቶች አሏቸው።
በተለይ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በቦንድ ባለቤቶች መካከል ያለው ልዩነት ዶክተር ቀልቤሳ “ተጽዕኖ ይኖረዋል” ቢሉም የተጀመረውን የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ሒደት “ሙሉ በሙሉ ያደናቅፋል” ብለው አያስቡም። “ዕዳዎች እና የመክፈያ ጊዜዎች በሚደራረቡበት ጊዜ የመክፈል አቅሟ ይወርዳል” የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ አሁን የተጀመረው ሒደት ለቦንድ ባለቤቶች “በጣም ጥሩ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
እሸቴ በቀለ
ፀሀይ ጫኔ