የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ወዴት እያመራ ነው?
ረቡዕ፣ መጋቢት 10 2017ኢትዮጵያ «የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንድታከብር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግ» ስትል ኤርትራ መጠየቋ ተነገረ ። የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፦ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈት ጥረት እያደረገች እንደሆነ እና ሀገሪቱ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ላይ ጣልቃ እየገባች ነው የሚል «ሐሰተኛ» ያሉት ክስ በኢትዮጵያ በኩል መኖሩን ስለመግለጻቸውም ተጠቅሷል ። ኤርትራ ይህንን ያለችው አስመራ ውስጥ ተቀማጭ ለሆኑ አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እና ሀገሪቱ ዕውቅና ለሰጠቻቸው የተባበሩት መንግስትታት ተቋማት ኃላፊዎች በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ማብራሪያ በተሰጠበት ወቅት ነው ተብሏል ። ኤርትራ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰሞኑን በተደጋጋሚ መግለጫ እያወጣች ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት በኩል ለዚህ በግልጽ የተሰጠ ምላሽ ወይም አስተያየት የለም ።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለ ኢትዮጵያ ምን አሉ?
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ አስመራ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እና ሀገራቸው «ዕውቅና ለሰጠቻቸው የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት አመራሮች» በኤርትራ ላይ ተከፍቷል ስላሏቸው ሐሰተኛ ክሶች ማብራሪያ መስጠታቸውን የሀገሪቱ የማስታወቅያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በ ኤክስ ዐሳውቀዋል።
የሚኒስትሩ ማብራሪያ ኤርትራ በኢትዮጵያ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀች ነው የሚለው፣ የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት እና የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻትን የተመለከቱ ሦስት ጉዳዮች መሆናቸውም ተጠቅሷል።
«የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት አለ የሚል ወይም የሚያመለክት አካል ይህን የሚያደርገው ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮች ኤርትራን ተጠያቂ ለማድረግ ነው» ያሉት የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የሀገሪቱ «መከላከያ ሠራዊት ሕዳር 2022 [የሰሜን ጦርነት] ግጭቱ ካበቃ በኋላ ወደ ኤርትራ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ድንበር እንዲሰማራ ተደርጓል።»
የኤርትራው ከፍተኛ ባለሥልጣን ስም ባይጠቅሱም እነዚህ «ውንጀላዎች በቀድሞ የሕወሓት አባላት የተነዙ ናቸው» ስለማለታቸው የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ባጋሩት መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳይ ተንታኝ አስተያየት
«ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘች ጀምሮ እንደ ሀገር እንዲሁም፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ቀድሞ አብሮ እንደነበረ ሕዝብ ሊመሰገን የሚችል ግንኙነት ሊመሰርቱ ይገባ ነበር» ያሉ ስማቸውን ከመጥቀስ ተቆጥበው ሐሳባቸውን ያጋሩን አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳይች ተንታኝ፤ «ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል መልካም ግንኙነት ቢታይም የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በግጭት ማቆም ስምምነት የቋጨው የፕሪቶሪያ ስምምነት የነበረውን በጎ ግንኙነት ቀልብሶታል» ብለዋል። ግን ለምን?
«የጦርነቱ አካል እንደነበረ አንድ አገረ መንግሥት [ኤርትራ]፣ በስምምነቱ ወቅት በተወሰነ ደረጃም ተሳትፎ ሊኖረው እንደሚገባ - በመርህ ደረጃ ይጠበቅ ነበር። እሱን አላየንም ።»
የኤርትራ መንግሥት «የፕሪቶሪያ ስምምነትን የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ አድርጎ ስለሚመለከተው በዚህ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለውም» ያሉት የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር «በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በሕወሓት መካከል እየተካሄደ ባለው የውስጥ ፍትጊያ የኤርትራ መንግሥት ምንም አይነት ሚና የለውም» ስለማለታቸውም ተገልጿል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወዴት እያመራ ነው? ብለን የጠየቅናቸው ተንታኙ ሁለቱ ሀገራት አንደኛው ላንዳቸው «መልካም ሊሆኑ የሚገባ ግን መልካም ያልሆኑ ጎረቤቶች ናቸው» ብለዋል።
«ግንኙነታቸውን ወደ መሻከር፣ አሁን ደግሞ በቅርቡ እንዳየነው ወደ መካሰስ ያደላ ቅርጽ እንዲይዝ ያደረገው ነገር ምንድን ነው ብለን ከጠየቅን በተጨባጭ ይሄኛው ነው ምክንያቱ ብሎ መናገር አይቻልም።»
ተንታኙ እንደሚሉት ኤርትራ ሕወሓት ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ አለመደረጉ የፈጠረባት ቁጭት፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት ተሳታፊ አለመደረጓ እና የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎትና ያንን ተከትሎ እየተራመዱ ያሉ አቋሞች ግንኙነታቸውን ወደ መሻከር የገፉ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ምልከታቸውን ጠቅሰዋል። ተጀምሮ የነበረው የሀገራቱ በጎ ግንኙነት እንዲቀጥል የሚቸግረው ምንድን ነው ለሚለውም ምላሽ ሰጥተዋል። «በሁለቱም መንግሥታት መካከል የጀብደኝነት፣ የጦረኝነት ባሕል ነው ያለው። የሰለጠነ ፖለቲካን የማራመድ ልምድ የላቸውም ሁለቱም ሀገራት።»
የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ፤ የኤርትራ ሥጋት
ኤርትራ ኢትዮጵያ «በዲፕሎማሲያዊ ሥልትም» ይሁን «በወታደራዊ ኃይል» ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የገለፁት «የባህር በር እና የባህር ኃይል መንደር» የማግኘት ፍላጎት ያላት መሆኑን በመጥቀስ በዚህ «የተሳሳተ እና ያለፈበት» ሲሉ በገለፁት መሻት ሀገራቸው ግራ መጋባቷን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ «ኤርትራ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የሚመለከታቸው» ያሉት አካላት «ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንድታከብር ጫና እንዲያደርጉ» ስለመጠየቃቸው ተዘግቧል። ኢትዮጵያ ግን ባለችበት ቀጣና የባሕር በር የማግኘቱን ጉዳይ ከሕልውና ጋር አገናኝታ ገፍታበታለች።
ኤርትራ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰሞኑን በተደጋጋሚ መግለጫ እያወጣች ትገኛለች። በዚህ ዙሪያ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት በኩል በግልጽ የተሰጠ ምላሽ ወይም አስተያየት የለም። ከኤርትራ በኩል እየቀረበ ስላለው ክስ የኢትዮጵያን መንግሥት አቋም ለመጠየቅ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ብንደውልም ስልካቸው አይነሳም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቃል አቀባይ ክፍል በኩል የለሁለቱን ሀገራት ወቅታዊ ግንኙነት በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጥ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የተጠየቀ ሲሆን፣ ግንኙነቱ በመልካም ኹኔታ ላይ እንደሚገኝ ማሳወቁ ይታወሳል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ